ኢትዮጵያ እና እስራኤል በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2013፡- ኢትዮጵያ እና እስራኤል በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከእስራኤል ምክትል ደህንነት ሚኒስትር ከሆኑት ጋዲ ይቫርካን ጋር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ስለሚያደርጉት የትብብር ስራ ውይይት አድርገዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለዘመናት የቆየ የወንድማማችነት ግንኙነት እንዳላቸው የገለፁት የእስራኤል ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን ትኩረት በሚያሻው የሳይበር ደህንነት ዘርፍ ሀገራቸው ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል።

የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በአለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን ያስቀመጡት ሚኒስትሩ ኢትዮጲያ ለዘርፉ የሰጠችውንም ትኩረት አድንቀዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የነበራቸውን ጠንካራ ግንኙነት በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በተለይም ሰው ሀይልን ከማልማትና በዘርፉ ፍላጎት እና ተሰጥኦ ያላቸዉን ታዳጊዎች አቅም ለማሳደግ እና ለማብቃት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም እምቅ አቅሞችን በማበልፀግ ረገድ ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ በስፋት የሚሰሩባቸው አበይት ጉዳዮች እንደሆኑ ዶ/ር ሹመት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሀገራችን ወደ ዲጂታልይዜሽን በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚወስደው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁለቱ ሀገራት በጋራ ይሰራሉ ብለዋል።

የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በማደረጃት ሀገራዊ አቅሞችን ለማልማት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በሚያከውናቸው ስራዎች ላይ የእስራኤል መንግስት የባለሙያ ድጋፍ እና እውቀትን የማጋራት ስራ ላይ ድርሻ እንደሚወስድም ዋና ዳይሬክተሩ ከምክትል የደህንነት ሚኒስቴር ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ወቅት ገልጸዋል ።