ተግባር እና ሃላፊነት

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሀገራችንን የኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማቶች ከጥቃት ለመከላከል ብሔራዊ ጥቅሞችን እንዲያስጠብቅ በሚል ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ 1999 . በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 130/1999 መሠረት ተቋቋመ፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ የመጣውን የሳይበር ወንጀል ለመከላከል እና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የኤጀንሲውን ተግባርና ኃላፊነት እንደገና ማሻሻል በማስፈለጉ በሚኒስትሮች ምከር ቤት ደንብ ቁጥር 250/2003 እንዲሁም በቅርቡ በአዋጅ ቁጥር 808/2006 ተሻሽሎ ፀድቋል፡፡

ኤጀንሲው የሚከተሉትን ተግባር እና ሃላፊነቶችን ያከናውናል

  • የቁጥጥር እና ክትትል ስራ
  1. ኢንፎርሜሽንና ኮምፒውተርን መሰረተ ያደረጉ ቁልፍ መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ብሄራዊ የፖሊሲ፣ የህግ፣ የስታንዳርድ እና ስትራቴጂ ረቂቆችን በበላይነት በመምራት ያዘጋጃል፤ ሲጸድቁም ተፈጻሚነታቸውን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤
  2. የክሪፕቶራፊ ግራፊ ምርትን እና ዝውውርን ይቆጣጠራል፤ አስፈላጊውን መስፈርት በማውጣት የአጠቃቀም ስርዓት ይዘረጋል፣ የክሪፕቶግራፊ መሰረተ ልማት ያበለጽጋል፤ ይዘረጋል፤
  3. ብሔራዊ ሩት ሰርተፍኬት ሰጪ ባለስልጣን ሆኖ ያገለግላል፤
  4. መንግስታዊ እና የግል ተቋማት ሃገራዊ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲና ስታንዳርድ ማእቀፎችን ተከትለው የየራሳቸው ፖሊሲና ስታንዳርድ ቀርጸው ስራ ላይ እንዲያውሉ ያደርጋል፤ አፈጻጸማቸውን ይቆጣጠራል፤
  5. ወደሃገር የሚገቡና ከሀገር የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች፣ የመረጃ አነፍናፊዎችና የጥቃት ቴክኖሎጂዎች በሀገር ደህንነት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ከመከላከል አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመቆጣጠር፤
  6. ኢንፎርሜሽን ወይም ኮምፒተርን መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማቶች ደህንነት ዙሪያ የትምህርት እና ስልጠና ፕሮግራሞች በመቅረጽ በራሱ ማሰልጠኛ ማዕከል ወይም ከሌሎች ጋር በመተባበር የመስጠት፤

  • የማልማት እና የማበልጸግ ስራ
  1. በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ የኢንፎርሜሽን እና ኮምፒተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች ደህንነት ምርቶችንና አገልግሎቶችን የማበልጸግ እና ስራ ላይ  እንዲውል የማድረግ፤
  2. ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች የሳይበር ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት መሰረተ-ልማቶችንና ስርዓቶችን የመዘርጋት፤
  3. በመንግስት ውሳኔ መሰረት ለውጭ አጋር ሃገራት የደህንነት ምርትና አገልግሎት የማቅረብ፤
  4. ሃገራዊ አቅም ባልተፈጠረባቸው ክፍተቶች ደህንነታቸው የተጠበቁ የኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት መሰረተ-ልማቶችን እና ስርዓቶችን የማበልጸግና የመዘርጋት፤

  •  የኦፕሬሽን ስራዎች
  1. አገራዊ የኮምፒዩተር ድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከልን ያደረጃል፤ በበላይነት የመምራት፤
  2. ኢንፎርሜሽንና ኮምፒተርን መሰረት ባደረጉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ወይም ስርአቶች ላይ ወይም በዜጋች ስነ ልቦና ላይ የሚሰነዘሩትን የሳይበር እና ኤሌክትሮማግኔቲክ ጥቃቶችን ለመከላከል አስፈላጊ አጸፋዊ እርምጃ የመውሰድ፣
  3. በማንኛውም ወቅት የኢንፎርሜሽን እና ኮምፒተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ኦዲት የማድረግ፣ መስፈርቶችን ላላሟሉ መሰረተ ልማቶች ሰርአቶቻቸውን ከሳይበር ጥቃቶች በበቂ መንገድ እንዲከላከሉ የሚያስችሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን ማሳወቅ እና አፈፃፀማቸውን የመከታተል፤ መመዘኛውን አሟልተው ለተገኙ ተቋማትም የደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የመስጠት ወይም እነዚህን ተግባራት እንዲያከናውኑ ለሌሎች ተቋማት ውክልና የመስጠት፣
  4. ለአንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለደህንነት ፍተሻ እና ለግምገማ የሚያገለግል የላብራቶሪ ማዕከል የማቋቋም፣
  5. የሳይበር ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሂደት ለፖሊስና ሌሎች በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ትብብር የማድረግ፣ ድጋፍ የመስጠት፤