Untitled Basic Web Content

   ረቂቅ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው "ሳይበር" ምንድን ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2011፡-ሳይበር የሰው ልጅ የእርስ በርስ ግንኙነቱ ማደግ የፈጠረው ረቂቅ የቴክኖሎጂ ውጤት እና መሰረተ-ልማት፣ የመረጃ እንዲሁም የሰዎች መስተጋበር የሚገለጽበት ፈጠራ ነው፡፡

የሳይበር ምህዳር የምንለው የተለያዩ የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማቶች ማለትም ኮምፒውተሮች ፣ራውተሮች፣የኮምፒውተር ኔትዎርኮች፣ወ.ዘ.ተ. ተሳስረው የፈጠሩት ምናባዊ ዓለም ሲሆን በዚህ ምህዳር ውስጥ ኢንፎርሜሽን ይቀመጣል፣ይሰራጫል፣እንዲሁም ይተነተናል፡፡

የሳይበር ምህዳሩን አንዳንዶች በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሰው ልጅ የተቆጣጠረው አምስተኛው ግዛት በማለት ይጠሩታል፡፡  ይህም ከየብስ ፣ ውሃ ፣ የአየር እንዲሁም የውጫዊው የህዋ ግዛት መካከከል በመመደብ፡፡

የሳይበር ምህዳር፡ የብዙዎቻችን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ አካል ከሆነም ውሎ አድሯል፡፡ ይህ ሲባል ለስራ ፣ለትምህርት ፣ ለመዝናኛ ከመጥቀምም አልፎ ለተለያዩ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ማሳለጫ አድርገን የምንጠቀምበት ዋነኛ መሳሪያ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ አልፎ የምህዳሩ እውን መሆን የኢንፎርሜሽን ዋጋ ከምንጊዜውም በላይ እንዲጨምር ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡

  • የሳይበር ምህዳር አካላት

የሳይበር ምህዳር የምንለው ኮምፒውተሮች ብቻ የሚፈጥሩት ሳይሆን የተለያዩ አካላት ተሳስረው እውን ያደረጉት ምህዳር ነው፡፡ እነዚህ የሳይበር ምህዳር አካላት ከላይኛው የምህዳሩ ክፍል እስከ ታችኛው ድረስ በ4 ዋና ዋና ክፍለች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

  • የውስጠኛው የምህዳሩ ክፍል፡ የሳይበር ምህዳር እውን እንዲሆን መሰረት የጣለው አካላዊ ወይም ፊዚካል ደረጃ የምንለው ነው፡፡ ይህም የተለያዩ ማሽኖች፣ኮምፒውተሮች፣ኬብሎችና የመሳሰሉ አካላት ጥምረት ነው፡፡
  • ሁለተኛው የሳይበር ምህዳር ውስጥ የሚቀመጠው፣ የሚተነተነው እና የሚሰራጨው ኢንፎርሜሽን ነው፡፡
  • ሶስተኛው የሳይበር ምህዳር ክፍል ለኢንፎርሜሽን መፈጠር፣ መተንተንና መሰራጨት መሰረት የሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት ፕላትፎርሞች ናቸው፡፡
  • እንዲሁም የመጨረሻው እና ውጫዊ ክፍሉ፡ የሳይበር ምህዳሩን የሚጠቀመው፣ ኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂውን የሚያንቀሳቅሰው የሰው ልጅ የሳይበር ምህዳር ውጨኛው ክፍል ነው፡፡

  • የሳይበር ምህዳሩ ልዩ ባህሪያት

  • ያልተማከለ ወይም ልዩ የተማከለ አስተዳደር የሌለው ሲሆን ይህም ለቁጥጥር አዳጋች እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
  • ለግለሰቦች እና ለቡድኖች ከፍተኛ ሃይል የሚሰጥ ሲሆን የግለሰቦች እና ቡድኖች አስተሳሰብ፣እምነት እና እሴቶችን ማንጸባረቅ የሚያስችላቸው ነው፡፡
  • የጎንዮሽ እና ትስስራዊ ሃይል የሚያበረታታ ነው፡፡
  • ዓለም አቀፋዊ እና ድንበር የለሽ ነው፡፡
  • እውቀት መረጃና ምናባዊነት ላይ ያተኩራል
  • ለደካሞች ልዩ ተጠቃሚነትን የሚሰጥ ነው
  • ሁሉም ጋር የደራሽነት አቅም ያለው፡፡
  • በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭ የሆነ ፍልስፍናዊ ባህሪ ያለው ነው፡፡

በእነዚህ ልዩ ባህሪያት ምክንያት ምህዳሩ ለተጠቃሚዎች መልካም እድሎችን ይዞ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለየ መልክ እየያዘች ከመምጣቷ ባሻገር  የእውቀት እና የኢንፎርሜሽን ማህበረሰብ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ መልካም እድሎች ካመጧቸው ቱሩፋቶች ጎን ለጎን ምህዳሩ የተለያዩ የደህንነት ስጋቶችን ይዞ መጥቷል፡፡ እነዚህን ስጋቶች ለመቋቋምና ምህዳሩ ያለውን መልካም ጎኖች አሟጦ ለመጠቀም ሃገራት የደህንነት ስትራቴጂዎች ከቴክኖሎጂ፣ ከሰው ልጆች እንዲሁም ከኢንፈርሜሽን ደህንነት አስተዳደር እና አሰራር ስርዓቶች አንጻር ቀርጸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከስትራቴጂዎች  መካከልም የኢንፎርሜሽን ደህንነት ገዥ ሰነዶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡