10 ጠቃሚ ሳይበር ደህንነት መጠበቂያ ዘዴዎች

 

በይነ-መረብ ከቀረው አለም ጋር በቀላሉ እንድንገናኝ እና አለማችንን እንደ አንድ መንደር ያህል እንድትጠብ የማድረጉን ያህል አጥፊ አገናኞች፣ ትሮጃንስ እና ቫይረ የሚገኝበት ምህዳር ነው፡፡ የመረጃ ስርቆትም ይበልጥ እያደገ እና ተጠቃሚዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ አንድ ክሊክ /click/ በሺዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ኪሳራን ሊያስከትልብን ይችላል፡፡ በመሆኑም ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ከተለያዩ ጥቃቶች ሊጠብቁባቸው የሚችሉባቸውን እውቀቶች ሊያዳብሩ ይገባል፡፡

  1. በግዴለሽነት ሳያስተውሉ ክሊክ ከማድረግ ይቆጠቡ

ክሊክ ማድረግ ስለቻልን ብቻ ክሊክ ልናደርግ አይገባም፡፡ እንደዘበት የከፈትነው  አያያዥ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል፡፡ አደገኛ ትስስር ገጾች /links/ በተለያየ መንገድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ትስስር ገጾችን ከታማኝ ምንጭ የተላኩ ስለመሆናቸው ከመክፈታችን በፊት ልናረጋግጥ ይገባል፡፡

  1. ባለሁለት መንገድ ማረጋገጫ ይጠቀሙ

ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም አስፈላጊ ነው ነገር ግን ይበልጥ ባለሁለት ወይም ዓይነተ ብዙ መንገድ ማረጋገጫ መጠቀም ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህም አጥቂዎች በቀላሉ የይለፍ ቃላችንን ማወቅ ቢችሉ ሌሎች ተጨማሪ የደህንነት መጠበቂያ በመኖሩ አካውንታችን ለጥቃት እንዳይጋለጥ ያደርጋል፡፡

  1. ለፊሺንግ መጨበርበር እንዳይጋለጡ ይጠንቀቁ

በየቀኑ ከ3 ቢሊየን በላይ ሀሰተኛ ኢ-ሜይሎች ይላካሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ትልቁን የሳይበር ደህንነት ሥጋት የሚይዙት የፊሺንግ ጥቃቶች ናቸው፡፡ በፊሺንግ ጥቃት ሰዎች በጣም በምናውቃቸው ጉዳዮች ሊያታልሉን እና አጥፊ ትስስሮችን እንድንከፍት በማድረግ ሥርዓታችን ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ለዚህ መፍትሔው ከማናውቃቸው ሰዎች የሚላኩ ትስስሮችን ማስወገድ ጠቃሚ ነው፡፡

  1. ለሚከፍቱት የዲጂታል አካውንቶች በሙሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ያድርጉ

አካውንት ቁጥራችንን ሞኒተር በምናደርግበት ጊዜ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ልንታዘብ እንችላለን፡፡ ኦንላይን የከፈትናቸውን ስንቶቹን አካውንቶች እናስታውሳለን? ለምሣሌ እንደ ክሬዲት ካርድ ያሉ እና በዲጂታል ሚዲያው በተለያየ ወቅት የከፈትናቸውን የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ልንከታተልና የማንጠቀምባቸውም ከሆነም ልናስወግዳቸው ይገባል ወይም ጠንካራ የይለፍ ቃል ልንጠቀም ይገባል፡፡

  1. በየጊዜው ወቅታዊ ማዘመኛዎችን ይተግብሩ

የደህንነት ስጋቶች ሲኖሩ ክፍተቶች መድፈኛ ሶፍትዌሮች ልንጠቀም እንችላለን፡፡ የሶፍትዌር ዝመና ማንቂያ ማስታወሻዎች /Notification/ ሊያሰለቸን አይገባም፡፡ እነዚህን ማንቂያ ማስታወሻዎች በመከታተል ወቅታዊ ዝመና ለምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች ልንተገብር ይገባል፡፡

  1. ደህንነቱ የተረጋገጠ ግንኙነት መፍጠርዎን ያረጋግጡ

የሳይበር ደህንነት መጠበቂያ ትምህርቶች አሁን ላይ በተሻለ ሁኔታ ህብረተሰቡ እያገኘ ቢሆንም በአግባቡ ሲጠቀምባቸው ግን አይታይም፡፡ የምንጠቀምበት መሣሪያን ደህንነቱ ካልተጠበቀ መሣሪያ ጋር በምናገናኝበት ወቅት ለአደጋ ልንጋለጥ እንችላለን፡፡ በተለይም ምስጢራዊና ጥንቃቄ የሚሹ መረጃዎች የያዙ መሣሪያዎችን በግል በይነ-መረብ ብቻ መጠቀም ይመከራል፡፡

  1. የሞባይል ስልክዎን  ደህንነት ይጠብቁ

የሳይበር ደህንነት ለዴስክቶፕ ኮምፒውተሮቻችን ብቻ የሚደረግ አይደለም፡፡ የእጅ ስልኮቻችን ደህንነት የማረጋገጥ ባህል ልናዳብር ይገባል፡፡ ሁልጊዜም ጠንካራና በቀላሉ ሊገመቱ የማይችሉ የይለፍ ቃላቶችን ልንጠቀም እና ብሉቱዝ በማንጠቀምበት ወቅት ልናጠፋ ይገባል፡፡ የህዝብ ዋይፋይ ተገቢውን ጥንቃቄ ሳናደርግ ከስልካችን ጋር ማገናኘትም ሆነ የተለያዩ ፋይሎችን ማውረድ ለጥቃት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡

  1. ለማህበራዊ ምህንድስና ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ይጠንቀቁ

አጥቂዎች የደህንነት ተጋላጭነት ማግኘት ሲያቅታቸው ሌላ መንገድ መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ አጥቂዎች የማህበራዊ ምህንድስና ዘዴን የሚጠቀሙ ሲሆን ይህ የጥቃት ዓይነት  የሚያነጣጥረው መሣሪያ ላይ ሳይሆን የተጠቃሚውን አእምሮ በማጥቃት የሚጠቀምበትን ሥርዓት እና መረጃ ለመውሰድ ይጥራሉ፡፡ በተለይም በኦንላይን እና በማህበራዊ ሚዲያ ይፋ የሆኑ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ፈጠራ የታከለበት የሳይበር ወንጀል ይፈጸማል፡፡

  1. መጠባበቂያ የመያዝ ባህል ያዳብሩ

የመረጃ ማከማቻ በአሁኑ ወቅት ውድ አይደለም፡፡ አሁን ላይ ጠቃሚ እና ጥንቃቄ የሚሹ መረጃዎችን ያለመጠባበቂያ ማስቀመጥ ቸል የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ መጠባበቂያ ፋይላችንን በመጠባበቂያ መያዣ መሣሪያዎች ወይም ምሥጢራዊ የመረጃ ማስቀመጫ /cloud/ ላይ ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ አጥፊ ቫይረሶች እና አጥቂዎች መረጃዎችን የመጨረሻ ዓላማቸው መስረቅ ብቻ ሳይሆን መረጃዎችን እንዳይነበቡ ወይም እንዲሰረዙ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መጠባበቂያ መያዝ አማራጭ የሌለው ማገገሚያ ነው፡፡

  1.  እኔ ለጥቃት አልጋለጠም የሚል አስተሳሰብን ያስወግዱ

እጅግ አደገኛው  እሳቤ "የሳይበር ጥቃት እኔን አያገኘኝም" ወይም "ደህንነቱ ያልተጠበቀ ድረ-ገጽ አልጠቀምም" ብሎ መዘናጋት ነው፡፡ የሳይበር ወንጀለኞች ማናቸውም ዓይነት ተጠቃሚን ዒላማ አድረገው ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ብህልነት ነው፡፡