የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የአፋር ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ እና የአፋር ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ

በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ በኢመደኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው ወርቁ እና በአፋር ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አህመድ በኩል ተፈጽሟል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ በዋናነት የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረግና ተጋላጭነቱን መቀነስ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን እና ምርጥ ተሞክሮችን ማጋራት፣ መሰረታዊ የሳይበር ደህንነት ምክረ ሃሰቦችን ማቅረብ፣ የሳይበር ደህንነት ተቋማዊ መዋቅሮችን መንደፍ፣ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ምዘና ማካሄድ አንዲሁም በተቋሙ የኤሌክትሮኒክስ ደህንነት ላይ ምክረ ሀሳብን ማቅረብ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም የክልሉን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት እና ኢርፒ (enterprise resource planning) አውቶሜሽን ሲስተሞችን ማልማት፣ የተቋሙን የሰነድ፣ የካዳስተር እና የመሬት አያያዝ መረጃ ስርአቱን ማዘመን፣ የተቋሙን ዳታ ሴንተር መገንባት፣ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ እና የአቅም ግንባታ ዘርፎችን ማጎልበት ስምምነቱ ላይ የተካተቱ ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች እንደሆኑ በፊርማ ስነ-ሥርአቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡

የኢመደኤ /ዋና ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው ወርቁ እንደገለጹት ኢመደኤ በዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል ያለው፣ ከሌሎች ባላድርሻ አካላት ጋር በጥምረት የሚሰራ እና በራስ አቅም የበለጸጉ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን የክልሉን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኤጀንሲን በዚሁ ዘርፍ ለማገዝ ብቃትም አቅምም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የአፋር ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው ተቋማቸው ከተመሰረት የአንድ ዓመት ቆይታ ብቻ እንዳለው ገልጸው ከኢመደኤ ጋር ያደረጉት ስምምነት ለክልሉም ሆነ ለኤጀንሲያቸው የሚያበረክተው አስተዋጾዖ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም አንደ ኢመደኤ ካለ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ከሚሠራ፣ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ፣ የሰው ሀይል እና እውቀት ከያዘ ተቋም ጋር መስራታቸው በክልላቸው የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የጎላ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ አቶ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

በኢመደኤ የሳይበር ቢዝነስ ልማት ማዕከል ኃላፊ አቶ ሄኖክ አዱኛ በበኩላቸው ኢመደኤ ከዚህ ቀደም ሀገራዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ ፕሮጀክቶችን የማበልጸግ፣ የማማከር እና የክትትል ስራዎች ሲሰራ እንደነበር አውስተው በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረሰውን ስምምነትም ኤጀንሲው በውጤታማነት አንደሚያጠናቅቅ ተናግረዋል፡፡

Most Viewed Assets