ለኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች የአመራርነት ጥበብ ሥልጠና ተሠጠ

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በአመራርነት ጥበብ ዙሪያ የግማሽ ቀን ሥልጠና ሰጠ፡፡

ሥልጠናውን ያስጀመሩት የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ተቋሙ ትኩረት ከሚሰጥባቸው የትኩረት መስኮች አንዱና ቀዳሚው የሰው ኃይል ልማት መሆኑን አውስተው ዛሬ የሚሰጠው ሥልጠናም የአመራሩን ብቃት ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ሥልጠናው በተለይም ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባ ለመወጣት የሚያግዝ እንደሆነና በቀጣይም በተለያየ ደረጃ ለሁሉም ሠራተኞች እንደሚሰጥ ዶ/ር ሹመቴ ገልፀዋል፡፡

በአመራርነት እና አነቃቂ ንግግሮች የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ "የአመራርነት ጥበብ" በሚል ርዕስ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በገለጻቸው "ጥበብ ለምን አስፈለገ? አመራርነትን የምንገነዘብበት ደረጃ፣ አመራር ማነው?" እና ሌሎች የአመራርነት ክህሎትን የሚያዳብሩ ርዕሰ ጉዳዮችን ከነባራዊ ህይወት ጋር በማገኛኘት አስረድተዋል፡፡

ሀገራችንን ወደተሸለ ደረጃ ለማድረስ ሁላችንም ኃላፊነት ያለን በመሆኑ በተለይም በአመራርነት ደረጃ የምንገኝ ሰዎች በምንሠራው ሥራ ምን ተጠቀምን ሳይሆን ለሀገር እና ለትውልድ ምን አስተዋጽኦ አበረከትን? በሚል መንፈስ ልንሰራም ይገባል ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ አሳስበዋል፡፡

የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጊዜያዊ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ግርማ በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬው ሥልጠና አመራሩ ለሥራው የሚያግዝ ጥሩ ግብዓት ያገኘበት እንደነበረ ገልፀው በቀጣይም በተለያየ አግባብ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡

Most Viewed Assets