የሰዉ ልጆችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ቀዳሚዉ ስራ ነዉ

የጥቅምት ወር በአለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በመሆን ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን በማከናወን እየተከበረ ይገኛል፡፡
የሳይበር ደህንነት ማለት፡ ኮምፒውተሮችን ፣ ሰርቨሮችን ፣ ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎችን ፣ የኤሌክትሮኒክስ ስርዓቶችን ፣ አዉታረ-መረብ (ኔትወርኮችን) እንዲሁም መረጃዎችን ከመረጃ መንታፊዎች ጥቃት የመከላከል ተግባር ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሳይበር ደህንነት ስጋት ከአለማችን ቀዳሚ ከሆኑ ዓለም አቀፍ ስጋቶች መካከል አንዱ መሆኑን የግሎባል ሪስክስ ሪፖርት እና የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ ያመለክታል፡፡
ስለሆነም የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት ማረጋገጥ የግለሰቦችን የተቋማትን ብሎም የሀገራትን ደህንነት የማስጠበቅ ተግባር በመሆኑ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ተወስዶ መስራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡
በሃገራችንም የሳይበር መሰረተ-ልማቶች ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም እድገቱን በሚመጠን መልኩ የዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰጠዉ ትኩረት አናሳ ሆኗል፡፡
በዚህም በሃገራችን የሚሰነዘሩ የሳይበር የጥቃት ሙከራዎች ከዓመት ዓመት ጭማሪ እያሳየ ይገኛሉ፡፡
ይህንን በየጊዜዉ እየጨመረ የመጣዉን የሳይበር ጥቃት ለመግታት ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ስለ ሳይበር ደህንነት ተገቢዉን ግንዛቤ ማዳበር እና ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ መንገዶች ዉስጥ ሶስት ሳይበር ደህንነት ምሰሶዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ምሰሶዎች ቴክኖሎጂን መታጠቅ ፣ የሳይበር ደህንነት ስርዓት መዘርጋት እና የግለሰቦችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊናን ማሳደግ ናቸዉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንዳሚያመለክቱት ከሆነ ከፍተኛውን የሳይበር ጥቃቶች መጠን የሚይዙት የሰው ልጆች ከሚሰሯቸው ስህተቶች የሚመነጩ በመሆናቸው የሰው ልጆችን የሳይበር ደህንነት ዙሪያ ንቃተ ህሊና ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የሰው ልጆችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ከማሳደግ ባሻገር የተቋማት የአመራሮች ፣ ሰራተኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥምረት መስራት የሳይበር ደህንነትን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋጥ ጉልህ ሚና አለዉ፡፡
እርስዎም ለሳይበር ደህንነት ስጋት ከሚያጋልጡ ተግባራት እና እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ እንዲሁም ከእርስዎ አቅም ዉጪ የሆኑ የሳይበር ደህንነት ስጋት ሲገጥምዎ ለሚመለከተዉ አካል በማሳወቅ በእርስዎ እና በሃገር ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች ይከላከሉ፡፡

Most Viewed Assets