ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በተለያዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዋናነት የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት፣ የሳይበር ደህንነት ስጋት፣ የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት እና የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥርን መሰረት አድርገው ዝረዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም በጀት አመት በመጀመሪያው አጋማሽ በሀገራች 2,145 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች የተፈፀሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 2,049 ምላሽ የተሰጠባቸው እና የተቀሩት በሂደት ላይ እንዳሉ አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም በመንፈቅ ዓመቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀም 91.5 ከመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል ፡፡

የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነትን መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይደርስ ነበር ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸዉን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ማድረጋቸዉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፤ ሚዲያ ተቋማት፤ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ፤ ሚኒስቴር መስራቤቶች ፤ የክልል ቢሮዎች ፤ የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

በሃገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት ስለተከሰቱ የጥቃት አይነቶች እና ኢላማዎች ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ በነዚህ ወራት በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፤ ማልዌር፤ የመሰረተ ልማት ቅኝት (Scan)፤ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS)፤ ሰርጎ መግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸዉ እንደነበሩ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም በተለያዩ ዘርፎች በሚገኙ 64 ተቋማት (27 የመንግስት እና 37 የግል) በተደረገ የተጋላጭነት ዳሰሳ ከተደረገባቸው የዌብ፣ የኔትዎርክ መሰረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች 340 የሳይበር ደህንነት የተጋላጭነትን የአደጋ ደረጃ (Vulnerability risk level) ክፍተት መገኘቱን እና መድፈን መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በተጨማሪም አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 2,158 የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎች 297 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው የተለዩ ቴክኖሎጂዎች በመሆናቸው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት አደጋ ደረጃ ለማመላከት በተመረጡ ሦስት ዘርፎች (የሚድያ ተቋማት፣ የፀጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ቁልፍ መሰረት ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት) ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትን እና ተጋላጭነትን በማጣመር መሰራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማዳኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክትሩ የሳይበር ጥቃት መከላከል ላይ ሊሰሩ ስለሚገቡ ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን እንደ ሃገር የሀገሪቱን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚሰራዉ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻውን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ከእነዚህ የጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ጥቃቶቹ ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ፣ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን እንደነበረም አብራርተዋል፡፡

በዚህም ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችል አስራ አምስት ቢሊዮን ብር ከኪሳራ ማዳን ተችሏል ሲሉ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡