በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ደህንነት ዙሪያ ለኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ለሚዲያ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
Asset Publisher
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትብብር በተዘጋጀው ስልጠና ላይ ለክልልና ለተቋማት የኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ለሚዲያ ባለሙያዎች በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ደህንነት ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ፡፡
“ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ርዕስ በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ እንዳሉት የኮሙኒኬሽን ዘርፉን ለማሻሻልና ሃገራዊ መግባባትን ለማዳበር የዘርፉን ባለሙያ አቅም መገንባት ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይም የኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተና ውጤታማ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን የተካፈሉ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊዎች በበኩላቸው በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ደህንነት ዙሪያ በተሰጠው ስልጠና መነሻ ሊሆን የሚችል እውቀትና ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ሰፋ ያለና በተግባር የታገዘ ስልጠና ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በአዳማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው በዚህ ስልጠና የመደመር ትርክትና የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ፣ የሕዝብ ግንኙነት መሰረቶች፣ የአጀንዳ ቀረጻና የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን፣ የሚዲያ አስተዳደርና ለህዝብ የሚደረጉ ንግግሮች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ደህንነት እንዲሁም ሃገራዊ የአደጋ ስጋት ቅነሳና የኮሙኒኬሽን ሚና ላይ ትኩረት ያደረጉ የስልጠና ሰነዶች ቀርበው ውይይት መደረጋቸውን ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው ያመለክታል፡፡