የሳይበር ጥቃትን ለመመከት ሀገራዊና ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ
የሳይበር ጥቃትን ለመመከት ሀገራዊና ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመመከት ሀገራዊና ቀጠናዊ ትብብርን ማሳደግ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኃላፊ አቶ ሃኒባል ለማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ማሕበር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት 3ኛው ዓለም አቀፍ የሳይበር ደህንነትና ዲጂታል ራንስፎርሜሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ “የሳይበር ደህንነት በቀጠናዊ ትብብር ዓውድ ውስጥ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ በፓናሊስትነት የቀረቡት አቶ ሃኒባል ለማ ባስተላለፉት መልዕክት በሳይበር ደህንነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እና ዲጂታል ትራንሰፎርሜሽንን ለማፋጠን ሀገራዊና ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የሳይበር ደህንነት በባህሪው እጅግ ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ በየጊዜው የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን ለመመከት በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቁልፍ ስትራቴጂ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል ቅንጅታዊና ትብብራዊ ሥራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሃኒባል፤ ከዚህ አኳያ አስተዳደሩ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በጉባዔው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡