ኢመደአ እና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሰሩባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ደህንነቱ የተጠበቀ የመከላከያ ኤሌክትሮኒክስ ምርት ምርምርና ልማት፣ በኤሮስፔስና ዲፌንስ እንዲሁም ኮሚዩኒኬሽን ምርትና አገልግሎት፣ የኤሌክትሮኒክ ጦርነት አቅም ልህቀት፣ እንዲሁም በሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ስልጠናና ድጋፍ ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ስምምነቱን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ እና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው /ማርያም ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በዛሬው እለት የተደረገው ስምምነት ይህንኑ የረዥም ጊዜ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና በሁለቱ ተቋማት ተበትኖ የሚገኝን አቅም በማሰባሰብ በሃገር ደረጃ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ለመስራት ነው ብለዋል፡፡

ኢመደአ ሃገር በቀል የሳይበር ደህንነት ምርቶች ላይ ምርምርና ልማት በማድረግ ረገድ የካበተ አቅምና ልምድ ያለው ሲሆን እነዚህን የምርምርና ልማት ሥራዎች በብዛትና በጥራት በማምረት ወደተግባር በማስገባት በኩል ደግሞ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን ከኢመደአ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን ሶካ አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም የኮርፖሬሽኑን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥና አቅም በመገንባት በኩል ኢመደአ አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ስልጠና እና ማማከር እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው /ማርያም በበኩላቸው ከኢመደአ ጋር በጋራ ለመስራት የተደረገው ስምምነት የመከላከያን የአሰራር ስርአት በማዘመን ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በኤሮስፔስና ዲፌንስ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የኮሚዩኒኬሽን መሰረተ ልማት፣ በኤሌክትሮኒክስ ጦርነት ዘርፍ በኢመደአ የሚካሄዱ የምርምርና ልማት ሥራዎችን በጋራ በመስራትና ወደ ምርት በማስገባት በኩል ኮርፖሬሽኑ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ጌታቸው /ማርያም ገልጸዋል፡፡

ከጋራ ስምምነት የፊርማ ፕሮግራም በተጨማሪ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች የኢመደአን ዲጂታል ኤግዚቢሽን ማዕከልና የኢትዮ ሳይበር ታለንት ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡