ኢመደኤ ከኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ እና የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው እና የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱም ኢመደኤ የኤጀንሲውን መሰረተ ልማት የማጥናት፣ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ምዘና ማካሄድ፣ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ እና የአቅም ግንባታ ዘርፎችን ማጎልበት፣ የዲጂታል ኮሙዩኒኬሽን ስርዓቶችን መዘርጋት፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት እና አር /Enterprise Resource Planning/ ማልማት፣ የሳይበር ደህንነት ተቋማዊ መዋቅር መንደፍ እንዲሁም ስትራቴጂክ ሮድ ማፕ ዝግጅትን እንደያዘ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢመደኤ ባሉት አቅሞች ተጠቅሞ ሊያዘምናቸው ከሚገቡ ተቋማት አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ሊሆን የሚገባው የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ኤጀንሲው ትልቅ የሀገር መረጃ የያዘ ተቋም እንደመሆኑ የያዘው መረጃ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲቆይ እና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት እንዲኖረው በኢመደኤ በኩል በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በበኩላቸው በተቋማቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓቶች እንዳሉ አውስተው በተለይም እንደወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያሉ ሥርዓቶችን ይበልጥ ለማዘመንና ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ከኢመደኤ ጋር ያደረጉት ስምምነትም የተቋማቸውን የቆዩ ሥርዓቶችን ከማዘመን ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያግዛል ሲሉ አቶ ሙጂብ ተናግረዋል፡፡

በኢመደኤ የሳይበር ቢዝነስ ልማት ማዕከል ኃላፊ አቶ ሄኖክ አዱኛ ኢመደኤ በሚሠራቸው ሥራዎች፣ ከዚህ ቀደም ተቋሙ ሠርቶ ባበረከታቸው ቁልፍ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች ዙሪያና ለኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ሊሠራቸው ባቀዳቸው ሥራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡