ኤጀንሲው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት እየሠራ ይገኛል

ኤጀንሲው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት እየሠራ ይገኛል

  • ከተቋሙ አባላት ጋር ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የውይይት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 06/2013- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ተቋም ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር / ሹመቴ ግዛው የተቋሙን ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ 2013 በጀት ዓመት 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እና መላው አባላት በተሳተፉበት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ኢመደኤ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት የሚያስችለውን ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ስኬት ለሰው ኃይል ልማት፣ ለቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እና ለአሠራር ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ስትራቴጂክ መሠረቶችን በተመለከተም ቴክኖሎጂና የዕውቀት ባለቤትነት፣ መሠረተ ልማት፣ ተቋማዊ ልህቀት፣ ትብብርና ቅንጅት እንዲሁም ፖሊሲ፣ ህግና ስታንዳርድ ማዕቀፎች የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

2013 በጀት ዓመት 6 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በተመለከተም ተቋሙ በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንደቻለ እና በቀጣይም በተለያዩ ምክንያቶች የተንጠባጠቡ ሥራዎችን አጠናቆ ለመጨረስ በትኩረት እንደሚሠራም / ሹመቴ ተናግረዋል፡፡

ከተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች አኳያም የቀጣይ 5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን፣ ተቋማዊ የገፅታ ግንባታና ምቹ የሥራ አከባቢ የመለወጥ ተግባራት መከናወናቸውን እንዲሁም የመዋቅር ክለሳ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

መላው የተቋሙ አባላትም በቀረበው ሪፖርትና በተለያዩ ተቋማዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች አንስተው በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እና /ዋና ዳይሬክተሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

የተቋሙ አባላት በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የውይይት መድረኩ ግልጽና አሳታፊ እንደነበረ ጠቅሰው በተቋማዊ ጉዳዮች ላይም ጥሩ መግባባትና ግንዛቤ የተፈጠረበት ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም አባላቱ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራር ጋር ያደረጉት ውይይት በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የተቋሙ  ዋና ዳይሬክተር / ሹመቴ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የተቋሙ አባላትከእኔ እንዳይቀር በሚል ስሜትየሚጠበቅባቸውን በመወጣት የተቋሙ ተልዕኮ እንዲሳካ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ እና እራሳቸውንም ሆነ ሀገርን የሚጠቅም ሥራ ለመስራት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

መድረኩ ለሦስት ቀናት በየኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ደብረዘይት ሥራ አመራር ማሰልጠኛ ማዕከል የተካሄደ ሲሆን ሪፖርት ከማዳመጥና ውይይት ከማካሄድ ባለፈ በጤናማ አካላዊና አዕምሯዊ አጠባበቅ እንዲሁም የህይወት ክህሎትና የመፈጸም ብቃት ዙሪያ ለሁሉም የተቋሙ አባላት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

Most Viewed Assets