ሀገራት በሳይበር ምህዳሩ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ትዉልድ ተሻጋሪ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚገባቸው የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ

Nested Applications

Asset Publisher

null ሀገራት በሳይበር ምህዳሩ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ትዉልድ ተሻጋሪ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚገባቸው የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ

ሀገራት የሳይበር መህዳሩ የፈጠረዉን መልካም አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀምና ተፈላጊዉን ለዉጥ ለማምጣት በትዉልዶች መካከል የአስተሳሰብ ትስሥርና የእዉቀት ሽግግር ማድረግ ወሳኝ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክር አቶ ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።

በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ እየተካሄድ በሚገኘው የጂአይቴክስ (GITEX) አፍሪካ አዉደ ርዕይ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክር አቶ ሰለሞን ሶካ በትዉልድ መካከል የሚፈጠሩ የእዉቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ቀጣይነት ያለዉ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚገባ በመድረኩ አንስተዋል።

"የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ስራ ለሙያዊ ልህቀትና ለኢኮኖሚ ልማት" በሚል የፓናል ዉይይት ላይ የተሳተፉት ዋና ዳይሬክተሩ በይበልጥ እንደ ኢመደአ ያሉ የሳይበር ምህዳር ላይ የተሰማሩ ተቋማት ካለዉ የበቃ የሰዉ ሃይል እጥረት ጋር ተያይዞ ለሰዉ ሃይል ልማት ከፍተኛ ቦታ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢመደአን የሰዉ ሃይል ልማት ሂደቶች በሶስት ትዉልድ ደረጃዎች ከፍለዉ ገለጻ ያደረጉት አቶ ሰለሞን፤ የመጀመሪያዉ ትዉልድ ስለ ሳይበር ጉዳይ በትምህርት ላይ የተመሰረት ብዙ እዉቀት ባይዝም የሀገራዊ ፍላጎቶችን በአግባቡ በመረዳትና በከፍተኛ ሃገራዊ ፍቅር ራሱን ከሁኔታዎች በማጣጣም እንደ ሃገር አቅም ባልተፈጠረባቸዉ ዘርፎች የአመራር ክህሎቱን ተጠቅሞ ለሁለተኛዉ ትዉልድ ግልጽ አመራር በመስጠትና እርሾ ሊሆን የሚችል ሀገራዊ አቅም እንዲፈጠር አስቻይ ሚና የተጫወተ ትዉልድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለተኛዉ ትዉልድ ወይም አብዛኛዉ በተቋሙ ዉስጥ እየሰራ ያለዉ የሰዉ ሃብት ከትምህርት ቤት ካገኘዉ እዉቀት ባሻገር እንደተቋም ለሰዉ ሃይል አቅም ግንባታ ከተሰጠዉ ትኩረት አንጻር የተለያዩ የስልጠና እድሎችን እንዲሁም በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ቀጥታ የተግባር ተሳትፎ በማድረግ የቴክኒካል አቅም እንዲገነቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ወሳኝ የሀገር አቅም የሆነ ትውልድ ሲሆን ከቀደምቶቹ ልምድ በመቅሰምና በመማር ተቋሙን እንደተቋም ሃገርን እንደሃገር በሚያደርጋቸዉ ጥረቶች የተለያዩ አበርክቶዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የዛሬው አቅም ለነገ ዋስትና አይሆንምና ሶስተኛዉ ትዉልድ በተቋሙ የሳይበር ደህንነት ታለንት ልማት ማዕከል የታቀፉ ታዳጊዎችን ያቀፈዉ ትዉልድ ሲሆን ሁለተኛዉ ትዉልድ ላይ ብቻ መንጠለጠለ ተገቢዉን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከባድ ስለሚሆን በታለንት ልማትና ልህቀት ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል። የሰዉ ሃይልን ከትምህርት የተመረቁ አካላትን ብቻ ይዘን የሃገራችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ቀጣይነት ያለዉን የበቃ የሰዉ ሃይል ልማት ማስቀጠል ስለማይቻል ልዩ ተሰጥዖ ያላቸዉን ታዳጊዎች መልምሎ እና እዉቀታቸዉን አጎልብቶ መጠቀም እንደሚገባ አቶ ሰለሞን ሶካ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም የሳይበር ጥቃት ከአለማችን ቀዳሚ ስጋቶች አንዱ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ከምህዳሩ ፍጹም ተለዋዋጭና ኢ-ተገማችነት አንጻር አንድ ሃገር ብቻዉን ምንም ሊፈጥር ስለማይችል ሃገራት በሳይበር ምህዳሩ ላይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።