የኢትዮጵያ የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አመራሮች በኢመደኤ የሥራ ጉብኝት አደረጉ
Nested Applications
Asset Publisher
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አመራሮች በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በመገኘት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝታቸው የኢመደኤን ኢትዮ-ሳይበር የተሰጥኦ ማዕከል፣ የምርትና አገልግሎት ማሳያ ኤግዚብሽን ማዕከል እንዲሁም የተቋሙን የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ለአመራሮቹ ባደረጉት ገለጻ ተቋሙ ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በኢመደኤ "ከእኔ አይቅር" በሚል መርህ እያንዳንዱ አባል የራሱን አበርክቶ ለማሳረፍ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የኢትዮጵያ የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሰራተኞችም በተሰማሩበት የስራ መስክ ለውጥ ማምጣት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ተቋም ለመገንባት አቅደው መስራት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ኢንስቲትዩቱን በተለያዩ ዘርፎች ለማገዝ ኤጀንሲው ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ሹመቴ ተናግረዋል፡፡
በኢመደኤ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ለኢንስቲትዩቱ አመራሮች ስለኢመደኤ አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ፣ ኢመደኤ ስለሚሠራቸው ቁልፍ የሥራ መስኮች፣ በለውጥ ሂደት ስለተከናወኑ ተግባራት እና ተቋሙ ስለተሰማራበት የሳይበር ምህዳር ምንነት ገለጻ አድርገዋል፡፡
በኢመደኤ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ አመራሮች በጉብኝቱ መደሰታቸውን እና በቀጣይ በተቋማቸው ማምጣት ለሚፈልጉት የለውጥ ሥራ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ያገኙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡