Asset Publisher

ሳይበር

ሳይበር የሰው ልጅ የእርስ በርስ ግንኙነቱ ማደግ የፈጠረው የቴክኖሎጂ ውጤት ሲሆን በመሰረተ-ልማት፣ በመረጃ፣ በግለሰቦች እንዲሁም  በማኅበረሰብ መስተጋበር ዕውን የሆነ ነው፡፡

የሳይበር ምህዳሩ በዋናነት የተለያዩ የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማቶች ማለትም ኮምፒውተሮች፣ የኮምፒውተር ኔትዎርኮችና ሲስተሞች እንዲሁም ሌሎች መሰል መሳሪያዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተሳስረው የፈጠሩት ምህዳር ሲሆን ሌሎች መሰረተ ልማቶችና ፊዚካላዊ አካላት በዘመናዊ መልኩ እንዲሰሩና የተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሳይበሩ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው። በመሆኑም እነዚህ መሰረተ ልማቶችና ፊዚካላዊ አካላት የሳይበር ምህዳሩ አንድ ክፍል እየሆኑ ነው፡፡ የኢንፎርሜሽንእና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለአንድ ሀገር ህልውና ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንደ መሆናቸው የተለያዩ ቡድኖችና ሀገራት የጥቃት ኢላማ ሊያደርጓቸውና የሳይበር ጥቃት ሊሰነዝሩባቸው ይችላሉ። ስለሆነም እነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘረውን የሳይበር ጥቃት መከላከልና የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ ጉዳይ ሆኗል። ይህ ሁኔታ በተለይም በአደጉት ሀገራት በጉልህ የሚታይ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም የሳይበር ተጠቃሚነቷ ከማደጉ ጋር ተያይዞ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶች እየጨመረ መምጣቱ ለሳይበር ደህንነት ተገቢ ትኩረት መስጠት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያሳየናል።