Skip to Content
 • Drop an Email contact@insa.gov.et
 • Get in Touch +251-113-71-71-14
ደህንነቱ የተጠበቀ ሳይበር ለሰላም ፣ ለልማትና ዲሞክራሲ
Back

ሃሰተኛ አድራሻ (Fake Account) ምንነት እና የሚያስከትላቸው ጉዳቶች

 

ማህበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጾችንና አፕልኬሽኖችን በመጠቀም በማህበራዊ ኔትወርኮች ለመሳተፍ፣ መረጃዎችን ለማጋራትና ለመፍጠር/ለመጻፍ፣ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ምህዳር ሲሆን ይዘቶቹም የተፈጠሩት ከተጠቃሚዎቹ ተሳትፎና በሚለቋቸው መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምህዳሩ ድረ-ገጾችን መሰረት ያደረገ ማህበራዊ ‘‘ኦን ላይን'' የመረጃ መለዋወጫ መድረክ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ኮምፒውተሮች በግለሰቦች ቤት በስፋት እየተገኘ መምጣቱን ተከትሎ ማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የመልዕክት ልውውጦች ለመጀመሪያ ጊዜ በ1988 ስራ ላይ የዋሉ ሲሆን በ1990ቹ ውስጥም በሰፊው ግልጋሎት ላይ ይውሉ ነበር፡፡

የመጀመሪያው ማህበራዊ ድረ-ገጽ እ.ኤ.አ በ1997 የተፈጠረው ሲክስ ዲግሪሰ (Six Degrees) ሲሆን ተጠቃሚዎቹን መረጃዎቻቸውን እንዲጭኑና ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር ጓደኝነት እንዲፈጥሩ ያስቻለ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1999 የተፈጠሩት የብሎጊንግ ሳይቶች ማህበራዊ ሚዲያን በሰዎች ዘንድ ጠልቆ እንዲገባና ሰፊ ተጠቃሚ እንዲኖረው እንዲሁም በፍጥነት እያደገ እንዲመጣ አስችለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2005 ፍሬንዲስተር፣ ማይ ስፔስ እና ሊንክድ ኢን እንዲሁም ምስሎችን በማጋራት ቀዳሚ ምርጫ የነበሩት ፎቶ በኬት እና ፍሊከር ዝነኛ ሆነው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የዩቲዩብ  መምጣት የማህበራዊ ሚድያን ተፈላጊነት በእጅጉ ከፍ ያደረገው ሲሆን ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙበት አዲስ መንገድ ፈጥሯል፡፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ፌስ ቡክ እና ቲውተር በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ደግሞ የማህበራዊ ሚድያን ጥቅምና ግልጋሎት ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ብዛት ያላቸውና እጅጉን የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃ መጋራትን መነሻ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን በዋነኝት ኪነ-ጥበብ፣ ቢዝነስ፣ መዝናኛ፣ ፖለቲካ፣ ጤና፣ ሀይማኖት፣ ቴክኖሎጂና የተለያዩ ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች/መስተጋብሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸውና በዋነኛነት ከሚጠቀሱ ማህበራዊ ድረ-ገጾች መካከል ፌስ ቡክ፣ ቲውተር፣ ዩቲዩብ፣ ኢንስታ ግራም፣ ጎግል ፕላስ፣ ሊንክድ ኢን፣ ፒንትረስት እና ስናፕ ቻት ይጠቀሳሉ፡፡

አንድን ገጽ ማህበራዊ ሚዲያ ነው ብለን ከመፈረጃችን በፊት ሊያካትታቸው የሚገቡ መገለጫዎች እንዳሏቸው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተጠቃሚ አድራሻ (User accounts)፣ የተጠቃሚ የመረጃ ገፅ  (profile pages)፣ ጓደኞች (friends)፣ ተከታዮች (followers)፣ ቡድን (groups)፣ ሀሽ ታግስ (hashtags)፣ የዜና ምንጭ (news feeds)፣ ግላዊነት (personalization)፣ ማሳወቂያ (notifications)፣ መረጃዎችን ማሻሻያ (information updating)፣ ማስቀመጥ ወይም መለጠፍ (saving or posting)፣ ስሜትን/ውዴታንና አስተያየት መስጫ አማራጮች (like buttons and comment section)፣ መከለስና ድምፅ መስጫ ስርዓቶች (review, rating or voting systems) በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡   

 

የማህበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታዎች

ማህበራዊ ሚዲያ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን እነዚህንም ጥቅሞች ከማህበራዊ፣ ከፖለቲካዊና ከኢኮኖሚያዊ አስተዋፆዎች አንጻር ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በማህበራዊው ዘርፍ ማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ህብረተሰቦችንና ባህሎች እያቀራረበ የሚገኝ ሲሆን በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ካሉ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ግለሰቦች ጋር እጅግ ርካሽ በሆነ ወጪ ትስስርና ቅርበትን መፍጠር ያስቻለ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘትና ግንኙነቶችን ቀልጣፋ ማድረግ አስችሏል፡፡ በተለይም መሰል ሚድያዎች በህብረተሰቡ ዘንድ የአንድን ሀገር ባህልና ታሪክ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ሰብዓዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን በቀላሉ ማሳየት እንዲችሉ፣ በጎ ፈቃደኛ እና እርዳታ በቀላሉ እንዲያሰባስቡና ደጋፊዎችና ተከታዮችን በሰፊው እንዲያፈሩ ማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ አስተዋጽኦን አበርክቷል፡፡ ለዚህም በዋነኛነት ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ደጋፊ ያለውን ዩኒሴፍን እና ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የቲውተር ተከታይ ያለውን ዩ. ኤን.ኤች.አርን  መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነሱ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ፣ የአሜሪካ ቀይ መስቀል፣ ዶክተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ በማፍራት ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅና ድጋፍና ትብብር ለማግኘት አስችሏቸዋል፡፡   

ከዚህም በተጨማሪ ማህበራዊ ሚዲያ በአንድ ሀገር ውስጥ በውስን ማህበረሰብ ዘንድ ያሉ ችግሮችን በማሳየት የአብዛኛውን ህብረተሰብ ድጋፍ በማግኘት ችግሩን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች እና በአንድ ሀገር ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ ለመቆም የሚደረጉ ቅስቀሳዎችን ለማስተላለፍ በሰፊው ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ለአብነትም ሙስናን ለማጋለጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት እንደ "iReport"  ያሉ ገጾች  ዋነኛ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡  

በኢኮኖሚ ዘርፍ ማህበራዊ ሚዲያ ወጪ ቆጣቢ ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ፣ የንግድ ትስስሮችን ለመፍጠር፣ የስራ ዕድሎችን ለማመቻቸት እንዲሁም የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም አማራጭ የብድር ተቋማትን፣ የዋጋ መጠንን በማሳየት ለገበሬዎችና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ የዓለም ባንክ አካል የሆነው አለም አቀፉ የፋይናንስ ህብረት በጽሁፍ መልእክት ከገበሬዎች ጋር ያካሄዳቸው ፕሮጀክቶች ለዚህ እንደ ዋነኛ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መብዛታቸውንም ተከትሎ ሀገራት ከዘርፉ እያገኙ ያሉት ገቢም እጅጉን መጨመሩ ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ይህ ሚዲያ ዘልማዳዊውን የግብይት ዘይቤ እጅጉን በመቀየር የቢዝነስ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኙባቸውን እና ሰፊ ትስስር የሚፈጥሩበትን መንገድ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ከመደበኛ ሚዲያ ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ ገቢ እየሆነ ይገኛል፡፡ ከቢዝነስ ተቋማት ጎን ለጎንም ማህበራዊ ሚድያዎችም ከማስታወቂያዎች የሚያገኙት ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ቢ.አይ.ኤ የተሰኘና በማርኬቲንግና በማስታወቂያ ስራዎች ጥናት፣ ማማከር እና ግምት ላይ የተሰማራ ተቋም ባወጣው ሪፖርት መሰረት ማህበራዊ ሚዲያዎች ከማስታወቂያ የሚያገኙት ትርፍ እ.ኤ.አ በ2017  11 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይጠቁማል፡፡  

 

የማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ገጽታዎች

ማህበራዊ ሚዲያ ከበጎና ከፍተኛ አስተዋጽኦን ከሚያበረክቱ ጠቀሜታዎቹ ጎን ለጎን ለአሉታዊ እንቅስቃሴዎች ጠቀሜታ ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ሚድያው ህብረተሰቡ ላይ ስነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶች የሚያስከትሉ እንቀስቃሴዎች ሲካሄዱበት ይታያል፡፡ ለአብነትም መሰል ሚድያዎችን በመጠቀም አይ.ኤስ.አይ.ኤስ የተባለ የሽብር ቡድን 30 ሺ ተዋጊዎችን ከአንድ መቶ ሀገራት ማሰባሰብ ችሎ እንደነበር ዲፌንስ ዋን የተሰኘው ድረ-ገጽ አስነብቧል፡፡ ቡድኑ በተጨማሪም የሽብር ስጋቶችን ለመፍጠር፣ ፕሮፖጋንዳውን በተለያዩ ሀገራት ለማስረጽ እንዲሁም የቁሳቁስ፣ የእውቀትና የቴኪኒክ ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀምበታል፡፡ አይ ኤስን ጨምሮ ሌሎች የሽብር ቡድኖች መሰል ማህበራዊ ሚድያዎችን መረጃን ለመለዋወጥና ለማስተላለፍ፣ የውይይትና የቅስቀሳ መድረክ አድርጎ መጠቀምን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች በዋናነት ይጠቀሙታል፡፡

በሌላም በኩል ግለሰቦች ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሰፊ ሰአት በማሳለፍ በስራ ውጤታማነት ላይ እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብርን በማዳከም ረገድ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖን ያስከትላል፡፡ ለአብነትም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ጓደኞች በኔትዎርኩ ውስጥ ያላቸው ቢሆንም በአካባቢያቸው ካሉም ሆነ በኔትወርክ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ያላቸው የአካል ግንኙነት እጅጉን ውስን የሚሆንበት ጊዜ ይታያል፡፡ ተያይዞም ቢቢሲ እ.ኤ.አ መስከረም 20/2017 ባወጣው ሪፖርት መሰረት ብዙ ሰአት ማህበራዊ ሚድያን በመጠቀም ምክንያት  ከማህበረሰቡ እየተነጠሉ መምጣት የስነ- ልቦናዊ እና አካላዊ ችግሮችን እንደሚያስከትል ገልጿል፡፡   

ማህበራዊ ሚዲያ የግል ሚስጥራዊነትን (Privacy) እያዳከመ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010  ኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ እና ማክስ ፕላንክ የሶፍትዌር ሲስተም የተባሉ ተቋማት ያወጡት መረጃ እንደሚያመለክቱት ግለሰቦች በብዛት ሚስጥራዊ ከማያደርጉት የጓደኞች የስም ዝርዝር ብቻ በመነሳት ስለ መለያቸው፣ የትምህርት ደረጃ፣ የትውልድ ከተማና መገኛ አድራሻን ጨምሮ የተለያዩ ግላዊ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ማህበራዊ ድረ-ገጾች በተደጋጋሚ የሚለቁትን ማሻሻያ ተጠቃሚዎች በየጊዜው ተከታትለው አለማደሳቸውን ተከትሎ የግል ሚስጥራዊ መረጃቸው ለሌላ አካል ተገላጭ ይሆናል፡፡ ተያይዞም አንዳንድ የማህበራዊ ድረ-ገጾች መገለጫዎች ግለሰቦች የማይፈልጓቸው መረጃዎች ያለፈቃዳቸው ይፋ እንዲወጡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ለዚህም "ታግ" በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ተጠቃሚዎች "ታጊንግ" ምርጫን ካላጠፉ ሌሎች ተጠቃሚዎች በሚያዎጡትና ከግለሰቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎች ውስጥ ታግ ሊደረጉና ግላዊ መረጃዎቻቸው ሊወጡ ይችላሉ፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በቀን ከ3 ሰአት በላይ መቆየትና ከ120 በላይ መልዕክቶችን መላክ የጤና ችግር እንደሚያመጣ ዌስተርን ሪዘርፍ የተሰኘው የህክምና ት/ቤት ያወጣው ጥናት ያሳያል፡፡ እንደ ጥናቱ ገለጻ የዚህ የጤና እክል መለያዎች ድብርት፣ ደካማ የእንቅልፍ ሁኔታ፣ ዝቅተኛ የትምህርት ውጤታማነትን ጨምሮ እራስን የማጥፋት ደረጃ ይደርሳል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ስጋት ወይም ቀውስ እየሆነ የመጣው የሃሰተኛ አድራሻዎች (Fake accounts) መበራከት ነው፡፡

 

ሃሰተኛ አድራሻ (Fake Account) ምንድን ነው?

ሃሰተኛ አድራሻ በሁለት አይነት መልኩ የሚገለጽ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የትክክለኛውን ግለሰብ አድራሻ (Account) በመጥለፍ (Hack) ግለሰቡን ሆኖ መረጃዎችን ማስተላለፍ ሲሆን፤ ሁለተኛው የግለሰቦችን ስም በማስመሰል (Impersonation) የማህበራዊ ድረ-ገጽ አድራሻ (Accounts) በመክፈት መረጃዎዎችን ማስተላለፍ ነው፡፡ የሁለተኛው አይነት ሃሰተኛ አድራሻ በመሰረቱ የማንነት ስርቆት (Digital Identity Theft) ይባላል፡፡

በቅርቡ ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፌስቡክ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በዓለማችን እስከ 4 ቢሊዮን የሚሆን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች/አካውንት እንዳሉ የገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህ መሀል 270 ሚሊዮን የሚሆኑት ሃሰተኛ አድራሻዎች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች/አካውንቶች እንዳሉ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚከፈቱ ሃሰተኛ አድራሻዎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በግለሰቡ፣ በማህበረሰቡ እንዲሁም በሀገር ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ  ጉዳቶች ያስከትላሉ፡፡  ይህ ችግር በአገራችንም በግለሰቦች፤ በታዋቂ ሰዎች፤ በፖለቲካ አመራሮች እና በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ሲደርስ ይስተዋላል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ላይ የተከሰተውን የማንነት ስርቆት ማንሳት እንችላለን፡፡ የአትሌቱን ታዋቂነት በመጠቀም ሃሰተኛ የፌስቡክ አድራሻ የከፈተው ግለሰብ ከ80 ሺህ በላይ ተከታዮችን በማፍራት፤ በአትሌት ኃይሌ ስም የተለያዩ መረጃዎችን ሲያሰራጭና ሲቀበል ቆይቷል፡፡ ይህም በአትሌት ኃይሌ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ጫና ፈጥሮበት እንደነበር አትሌት ኃይሌ ይናገራል፡፡ ይህም የግለሰቡን ነጻነት አደጋ ላይ ከመጣል ጀምሮ ለህይወቱ ስጋት ሊሆን ወደሚችልበት ሁኔታ ሊያመራ ይችል እንደነበር ገልጿል፡፡ ሆኖም አትሌት ኃይሌ የደረሰበትን የማንነት ስርቆት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ችግሩ ሊፈታለት እንደቻለ ይናገራል፡፡

የፌስቡክ ተቋም ይህን ዓለም አቀፋዊ ችግር ለመፍታት ያስችለው ዘንድ የማንነት ስርቆት ተፈጽሞብኛል የሚል ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት ለፌስቡክ ሪፖርት ማቅረብ የሚችልበት ፎርም ያዘጋጀ ሲሆን፤ ይህንን ፎርም ተጠቅሞ ሃሰተኛ አድራሻውን ማዘጋት ይቻላል፡፡

በሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበሩ ሕጎች ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር በበቂ ሁኔታ ተጣጥመው የማይሄዱ እና የኮምፒውተር  ወንጀልን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ ለመመርመርና ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍትህ ለማቅረብ የሚያስችሉ ባለመሆናቸው፤ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ ለመመርመርና ኤሌክትሮኒክ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚያስችል የኮምፒውተር ወንጀል ሕግ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

በኮምፒውተር ወንጀል ሕጉ አንቀጽ 11 መሰረት ማንኛውም ድርጊት ኮምፒውተርንና የኮምፒውተር ስርአትን፤ ዳታ እንዲሁም ኔትዎርክን የወንጀል ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ወይም ሌሎች ወንጀሎችን ለመፈጸም እነዚህን ጥቅም ላይ ያዋለ እንደሆነ ወይም ህገ-ወጥ ይዘት ያላቸውን ነገሮች በእነዚህ አማካኝነት ያሰራጨ ወይም ያከማቸ እንደሆነ ተግባራቱ የኮማፒውተር ወንጀል ተብለው ይፈረጃሉ ሲል ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም የሀሰት አድራሻ በመጠቀም የሰውን ማንነት መስረቅ ወንጀል እንደሆነና ከ5 አመት ባላነሰ እስራት እንደሚያስቀጣም ሕጉ አስቀምጧል፡፡ በሕጉ መሰረት የሀሰት አድራሻ መፍጠር እና በፈጠሩት አድራሻ ንግግሮችን፣ ጹሁፎችን ወይንም ምስሎችን ማስተላለፍ ሁለት የተለያየ ቅጣት እንዳለው በአንቀጽ 11 እና 12 ላይ አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንን ጥንቃቄና ሀላፊነት የተሞላበት በማድረግ ከዘርፉ የሚገባንን ጠቀሜታ ማግኘት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ሃላፊነት ሲሆን፤ ነገር ግን ሃሰተኛ አድራሻ ከተፈጸመብን ወዲያውኑ ለፖሊስ ማመልከትና ችግሩን መፍታት ይጠበቅብናል፡፡  

በሌላም በኩል ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ማህበራዊ ሚዲያን አዎንታዊና ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም እንችላለን፡፡

 • የግል ሚስጥርን ብሎም መረጃን በከፍተኝ ጥንቃቄ መያዝ፤
 • በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንጋራቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ መመርመር፤
 • በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንጠቀመውን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም እና በሂደት መቀነስ፤
 • ወላጆች የታዳጊ ልጆችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና የጓደኞቻቸውን ዝርዝር ማጤንና መከታተል፤
 • ወላጆች የቤተሰብ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደንቦችን ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ፤
 • ታዳጊ ልጆችን በማህበራዊ ሚዲያ ጠንቅና ጠቀሜታ ዙሩያ ማስተማር፤
 • ከማያውቁትና አጠራጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ለማውራት ፍቃደኛ አለመሆን፤

   ሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም

ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

ራዕይ

 • በ2017 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብቃት ያለው እና በሀገሪቱ ህዳሴ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ብሄራዊ የሳይበር ሴኪዩሪቲ ተቋም እውን ማድረግ፡፡   

ተልዕኮ

 • የአገሪቱን ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፡፡

እሴቶች

 • ተዓማኒነት
 • ሁሌም መማርና ማደግ
 • ልዩነት መፍጠር 
 • ተጠያቂነት

Web Content Display Web Content Display

 
 
INSA

ያግኙን ያግኙን

ስልክ: +251-11-371-71-14
ፖ.ሣ.ቁ: 124498
ኢሜል: contact@insa.gov.et
ፋክስ: +251-11-320 40 37
አድራሻ: አዲስ አበባ,ኢትዮጵያ