Skip to Content
 • Drop an Email contact@insa.gov.et
 • Get in Touch +251-113-71-71-14
ደህንነቱ የተጠበቀ ሳይበር ለሰላም ፣ ለልማትና ዲሞክራሲ
Back

ማህበራዊ ሚዲያ እና ሕጋዊ ቁጥጥር

ዓለማችን የተለያዩ ዘመናትን እያሳለፈች ቆይታለች፤ ዛሬም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ጥቂቶችን እንኳን ለማስታወስ ያክል አሮጌው፣ መካከለኛውና አዲሱ የድንጋይ ዘመን እንዲሁም የግብርናውና የኢንዱስትሪው ዘመን ተብለው የሚታወቁ የስልጣኔ እርከኖችን ተሻግራለች፡፡ እነዚህ ዘመናት የራሳቸው የሆነ አመክንዮአዊ መጠሪያ አላቸው፤ ይህም ሰዎች ኑሮን ለማሸነፍ ከሚያደርጉት ግብግብና ከሚመዘገበው የሥልጣኔ ነጸብራቅ (ለውጥ) አንጻር የሚሰጥ ሥያሜ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመንም ከእንደዚህ አይነት ሥያሜዎች ነጻ አይደለችም፡፡ በመሆኑም የኢንዱስትሪውን ዘመን (Industrial Age) ሸኝተን  የኢንፎርሜሽን ዘመን (Information Age) ከተቀበልን ብዙ ዘመን አልተቆጠረም"፡፡

የኢንፎርሜሽን ዘመን በባሕሪው ተለዋዋጭ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ለመጥፎም ሆነ ለበጎ ቅርብ ነው፡፡ ከተለያዩ የሕትመትና ብሮድካስት መገናኛዎች መፈልሰፍ ጋር ተያይዞ የጀመረው የኢንፎርሜሽን ዘመን የኢንተርኔት መገናኛዎችን (አውታሮችን) ይዞ ብቅ አለ፡፡ በዚህም ባለንበት ዘመን መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ዕውቀት፣ ሀብት፤ ዕድገት፤ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማት… ብቻ ሁሉም ነገር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ያለንበት ጊዜ ‹‹የኢንፎርሜሽን ዘመን›› የሚል ሥም የተሰጠው፡፡ ለኢንፎርሜሽን ዘመን ጋህድ መውጣት ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የኢንተርኔት መፈልሰፍና እያደገ መምጣቱ ሲሆን በፊት የነበሩ መገናኛዎችን ችላ በማለት ተጠቃሚዎች ወደ ዲጂታል የመገናኛ አውታሮች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢንተርኔት ይዞት ብቅ ካለው የሚዲያ አይነቶች አንዱ ደግሞ ማሕበራዊ ሚዲያ (Social Media) በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡

 

ማህበራዊ ሚዲያ

ማህበራዊ ሚዲያ (Social Media) ሲባል የሁለትና ከዚያ በላይ ኮምፒውተሮችን ቁርኝት ተጠቅሞ የመልዕክት ልውውጥ (ግንኙነት) የሚያሳልጥ ሚዲያ ተብሎ በአጭሩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በግንኙነቱ ሰዎች ከሰዎች ወይም ከድርጅቶች ጋር ሀሳባቸውን በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወ.ዘ.ተ የሚገልጹበት መረብ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ዋና ዋና ተብለው ከሚታወቁ የማህበራዊ ሚዲያዎች መካከል ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስአፕ፣ ተምብለር፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ባህሪያት

ማህበራዊ ሚዲያ ከሌሎች የሚዲያ አይነቶች የሚለዩባቸው የተለያዩ ባህሪያት አሏቸው፡፡ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያክልም፤መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ብዙ ወጭ የማይጠይቁ፣ በጊዜና በቦታ የማይገደቡ፣ የተለየ አቅም የማይፈልጉ … የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም የሚድያ ፎርማቶች (በፅሁፍ፣ በድምጽ፣ በምስል እና በቪድዮ) መልዕክቶችን ማስተላለፍ የሚያስችል ጸባይ አላቸው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የአንድ ወገን (One Way) የመረጃ ፍሰትን ያስቀሩና አሳታፊነትን (interactive) ከፍ ያደረጉናቸው፡፡ከዚህም አልፎ ማህበራዊ ሚዲያው በቀላሉ ማንነትን መደበቅ የሚያስችል (anonymous) ሲሆን በዓለም ላይ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀሰት አካውንቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ የወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ተከታይ በማፍራትም ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታ

ማሕበራዊ ሚዲያ ካበረከታቸው እና በአዎንታዊነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ 19 ላይ እውቅና የተሰጠውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ አስቻይ መድረክ መሆናቸው የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 ም ተመሳሳይ ድንጋጌዎችን የሚያንጸባርቅ ሲሆን ማህበራዊ ሚዲያዎች ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የህዝባዊ ጋዜጠኝነት (Citizen journalism) ለማስፋፋት፤ የኢንፎርሜሽን መጋራት ስርዓቱን ለማሳደግእና ለማስተባበር ጉልህ ሚና አላቸው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ የተራራቁ ሰዎችን ለማቀራረብ ከሚሰጡት ጥቅም ጀምሮ ምርትና አገልግሎትን እንዲሁም ብራንዶችን በቀላሉ ለማስተዋወቅ፣ በኪነ-ጥበቡ በኩልም በመደበኛ ሚዲያዎች ስራቸውን ወደ ማህበረሰቡ የማቅረብ ዕድል ላላገኙ ግለሰቦችና አካላት ጥሩ አጋጣሚ በመፍጠር፣ በአጠቃላይ ሲታይም ማህበራዊ ሚዲያ ለአዎንታዊ ተግባር ለሚጠቀም ዜጋ የልማት መሰረት ማድረግ እንደሚቻል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የሳይበር ፖሊሲና ሬጉሌሽን ጥናት ማዕከል ጥብቅ ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ይገልጻሉ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ገጽታ

ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚሰጧቸው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች ጎን ለጎን ለመጥፎና እኩይ ሃሳቦች ማስፈጸሚያ መሳሪያም በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ይህም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጠያቂነት የሌለበት ምህዳር በመፈጠሩ መጥፎ ዓላማ ያላቸው ሰዎች መድረኩን ያለ ሃላፊነት እየተጠቀሙት ከመሆኑም በላይ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላትም በሃሰተኛ ስምና ማንነት አፍራሽ መልዕክቶችን እንዲያሰራጩ በማስቻል በርካታ ጉዳቶችን እያስከተለ ይገኛል።

የአገራችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምም የዚሁ ገጽታ ነፀብራቅ ከመሆን አላለፈም፡፡አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት ማህበራዊ ሚዲያ በራሱ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን መሳሪያ ነው፤ መሳሪያን ደግሞ ተጠቃሚው ለአሉታዊ ድርጊት የሚያውለው ከሆነ ዜጎችን ብሎም አገርን ወደ መጥፎ ጎዳና ያስገባል፡፡ በተለይ ተጠያቂነት አልባ መረጃዎችን አጋኖ፣ አጣሞና ዋሽቶ በማቅረብ መገናኛዎቹ ለችግር ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች እያስከተሉ የሚገኙትን ችግርም በሶስት (በግለሰብ፣ በማህበረሰብ እና በአገር ደረጃ) ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ 

ማህበራዊ ሚዲያ በግለሰብ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፡-ማህበራዊ ሚዲያዎች የሰዎችን (ግለሰቦችን) ሞራል የሚሰብሩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በርካታ ዜጎች ለሞራል ውድቀትና የማንነት ውዝግብ ውስጥ አስገብተውታል፡፡ በሚዲያዎቹ በሚቀሰቀሱ ፕሮፖጋንዳዎች የተለያዩ ዜጎች ላልተፈለገ ሁከትና ብጥብጥ አለፍ ሲልም ህይወታቸውን አስከማጣት እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል የግለሰቦችን ስም ማጥፋት፣ መሳደብ፣ ማዋረድ፣ እርቃንን የሚያሳይ ምስል መልቀቅና መሰል ጸያፍ ተግባራትን በግለሰቦች ላይ በማሰራጨት የስነ-ልቦና ችግር እንዲደረስባቸው በማድረግ በዜጎች ላይ እያሳደረ የሚገኘው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ጫና በማህበረሰብ ላይ፡- አገራት በተለይም  እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ጠብቆ በሰላምና በዕድገት ጎዳና ለመዝለቅ እንዲሁም እርስ በርስ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ሆኖም ማህበራዊ ሚዲያዎች በዚህ እሴት ላይ አደጋን መደቀናቸው አልቀረም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች በማሕበረሰብ ላይ የሚያደርሱትን ስጋት ጥቂቶችን ለማንሳት ያክል የዘረኝነት ስድቦች፣ የባህል ወረራ፣ ሃይማኖታዊ ትንኮሳዎችና የውሸት ፖለቲካ በመንዛት ዜጎች ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ስራቸውን እንዳያከናውኑ ማድረግ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ማሕበረሰቡ በሰላምና በፍቅር ተሳስቦ የሚኖርበትን ባሕል ከማጠናከር ይልቅ ጥላቻን እያስፋፋ ይገኛል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ጫና በአገርላይ፡- ማህበራዊ ሚዲያ በዓለም ላይ በርካታ አገራት እንደ አገር ለመቀጠል እየተንገዳገዱ ለመሆናቸው አንዱ ችግሩን ያጧጧፈ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዳኔል ጀ.ፍላነሪ "ማህበራዊ ሚዲያና በወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ" በሚለው ጥናታዊ ጽሑፉ እንዳመለከተው በዓለም ላይ 93 በመቶ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ወጣቶች ሁልጊዜም መልዕክት ቅብብሎሽ ላይ ንቁ (Active) ናቸው ይላል፡፡ ከዚህ አንጻር የማህበራዊ ሚዲያ ፈጣንነቱ (Imedaicy)፣ ስፋቱ (Volume) እና ተጽዕኖነቱ (Intensity) ከፍተኛ በመሆኑ ለሁከትና ለማሸማቀቅ ቅርብ ነው፡፡ ይህን ያክል ተጽዕኖ ያለው ማህበራዊ ሚዲያ ታዲያ ምንም አይነት ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነ የሚያስከትለውን ጉዳት መገመት አዳጋች አይሆንም፡፡ ዛሬ በዓለም ዙሪያ በአንዲት አገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የማህበራዊ ሚዲያው ጦርነት ሰለባ ሆነው በአገራቸው የመኖር እጣ ፋንታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ይላል ጥናቱ፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ እና የደንበኞቹ ስጋት

በተለያየ ጊዜ ዘጋርዲያን የተሰኘው የዜና አውታር ያወጣቸው ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት የደህንነት ሽፋን አሁንም ጥያቄ ውስጥ ነው ይላል፡፡ በፈረንጆቹ 2017 በጋዜጣው የዝግጅት ክፍል ፌስቡክና መሰል የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ለዓለም ማህበረሰብ ጠቃሚ ናቸው ወይ ተብሎ 3ሺ 700 ደንበኞች ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል፡፡ መልስ ከሰጡት መካከል ይጠቅማል ያሉት 10 ከመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ከጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ያሉት ደግሞ 68 ከመቶ ሲሆኑ ቀሪዎች 22 ከመቶ ከሁለቱም ሳያካትቱ አልፈውታል፡፡

በዚሁ ጥናት ላይ ማህበራዊ ሚዲያ ከሩቅ ያለን ሰው ለማገናኘት ጠቃሚነቱ ባያጠያይቅም በዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያመጣ መሆኑ፣ የፈጠራ ወሬዎችን በማስፋፋት የግጭት መነሻ መሆኑ፣ በልጆች ላይ እያስከተለ የሚገኘው የስነ-ልቦና ችግርና የመሳሰሉት ማህበራዊ መገናኛን ከፋይዳው ይልቅ ጎጅ ባሕሪውን እያጎሉ የሚገኙ ሁነቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ምንድን ነው የተባሉት ደንበኞች በግለጽ የተቀመጠ የሕግ ቁጥጥር ባለመውጣቱ  ነው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ በዚህ ሳያበቃ ፌስቡክ የደንበኞቹን የግል ደህንነት ይጠብቃል ወይ የሚል መጠይቅ አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም 83 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ደህንነት (ሚስጥራዊነት) እንደማይጠብቅ አሳይተዋል፡፡ እንደ አጠቃላይ 66 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች ማህበራዊ ሚዲያ ከጥቅሙ ይልቅ ዓለምን ለችግር እየዳረጋት ነው ሲሉ አሉታዊ ጎኑን አጉልተው አሳይተዋል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ እና የስጋት ምንጭ

ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው ለተለያዩ ተጋላጭነቶች መፈጠር ዋናው ምክንያት ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት በሙሉ የተጠያቂነት መዋቅራዊ መስመር (platform) ባለመዘርጋቱ ነው ይላሉ ምሁራን፡፡

ጃኮፕ አምዴ "The Impact of Social Media on Society" በተሰኘው ጥናቱ ማህበራዊ ሚዲያ በተለይም ፌስቡክ በሰዎች ላይ እያደረሰ የሚገኘው ተጽእኖ ለመለካት ከአቅም በላይ ነው ይላል፡፡ ሚዲያው በአሁኑ ጊዜ የወንጀል ምንጭ እየሆነ መምጣቱንም አጥኝው ሳያሰምርበት አላለፈም፡፡ በዚህም ወንጀለኞች ማህበራዊ ሚዲያን መረጃን ለማጭበርበር፣ ገንዘብ ለመመዝበር፣ ጥቃት ለመሰንዘር እና ጉዳት ለማድረስ ያውሉታል፡፡ በመሆኑም ይላል ምሁሩ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ መፍትሔ እንደማይሆንና አስፈላጊውን የሕግ ቁጥጥር ማድረግ ቀጠሮ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ሲል ያሳስባል፡፡

የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን ሰነድ 19 (3) ጨምሮ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 6 የወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንዲሁም የሰውን ክብርና መልካም ስም የሚያረክስ በሕግ እንደሚያስጠይቅ ይደነግጋል፡፡ አለፍ ሲልም የጦርነት ቅስቀሳዎች ማድረግና የሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ማውጣት በሕግ መገደባቸውን ያብራራል፡፡ ዓላማውም የግለሰቦችን ብሎም የሕዝብን ሰላም እንዲሁም በወጣቶች ላይ ሊደርስ የሚችል ተጽእኖ ለመጠበቅ እና ጤናማ የሆነ ህብረተሰብ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡

በሌላ በኩል በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ መረጃን በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ለአገር ባላንጣዎች፣ ለሽብር ቡድኖችና ህዝብን ከህዝብ በማተራመስ የፖለቲካ ፍጆታ ለማግኘት ለሚውተረተሩ አካላት አሳልፎ መስጠትም አልፎ አልፎ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ በመሆኑምይህንንና ሌሎች የተጠቀሱ ችግሮችን ለማቃለል የሕግ ማዕቀፎችን ማውጣትና ስጋቱን መቀነስ አይነተኛ ሚና አለው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ እና የሕግ ማዕቀፍ

በርካታ አገራት የማሕበራዊ ሚዲያዎችን ተጠያቂነት የሚያጎለብቱ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ስታንዳርድ አንቀጽ 19ን ጠቅሶ በአውሮፓ ሕብረት የዜጎች ጉዳይ መብትና እኩልነት (REC) ዲፓርትመንት በፈንጆቹ 2018 ያዘጋጀው ‹‹በሶሻል ሚዲያዎች ላይ የሚሰነዘረውን ጥላቻ መዋጋት›› የሚለው ሪፖርት አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው ስታንዳርዱ በሌሎች ሚዲያዎች የሚያስከብረውን የሰዎች መብት በተመሳሳይ በማህበራዊ ሚዲያዎችም እንዲያሰፍን ("same rights that people have offline must also be protected online") ሲል  ይጠይቃል፡፡ ችግሩ በመላው ዓለም እየጎላ መምጣቱ ደግሞ ጥያቄውን የመላው የሰው ልጆች ጉዳይ ያደርገዋል፡፡

በአገራችንም ችግሩ ተመሳሳይ ገጽታ እየተላበሰ ቢመጣም እስካሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያዎችን መሰረት ያደረገ ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ይሁንና ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ህግ በበይነ-መረብ አማካኝነት ሊሰራጩ የሚችሉ እና ህገመንግስቱ ላይ በተቀመጡት ገደቦች ዙሪያ ያነጣጠረ "የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ" ወጥቷል፡፡ በኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ አንቀጽ 12፣  13 እና 14 እንደተጠቀሰው በወንጀልነት የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነርሱም ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ፀያፍ ድርጊቶች፣ ለሕዝብ ደህንነት አደገኛ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ማንኛውንም መልካም ያልሆነ እንቅስቃሴ በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ማሰራጨት በወንጀል የሚያስጠይቁ ድርጊቶች መሆናቸው ተደንግጓል፡፡

ከዚህ አኳያ ማህበራዊ ሚዲያዎች እያስከተሉ ከሚገኙት ዘርፈ-ብዙ ተጽዕኖ አንጻር የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ጉዳዩን መቆጣጠር (Regulate) በማስፈለጉ የተጀማመሩ ስራዎች መኖራቸውን አቶ ተስፋሁን አንስተዋል፡፡ እንደርሳቸው ገለጻ የሕግ ማዕቀፍ ሲባል ሙሉ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ሳይሆን የዜጎችን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ፣ አደጋውን ማስገንዘብና መሰል ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ በአገር ብሎም በወገን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያገለግል ነው፡፡ ስለዚህ ቁጥጥር በውስጡ በርካታ ሁነቶችን አካቶ የሚይዝ ሲሆን ይህም ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረጉ ወሳኝ ተግባራትን ለመፈጸም የሚያገለግል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል የህግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል ሲባል ነጻነትን መጋፋት አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ሳያነሱ አላለፉም፡፡ በመሰረቱ ነጻነት ሲባል ገደብ የለሽ ነው ማለት ግን አይቻልም፤ ነጻነትን ማረጋገጥ ሲባልም የሌላውን ነጻነት ማሳጣትም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጥላቻ ንግግሮች፣ የሀሰት ወሬዎች፣ አክራሪነት እና የመሳሰሉት ሀሳብን ከመግለጽ ነጻነት ውስጥ አይካተቱምና ነው፡፡

በተመሳሳይ ፌስቡክ ኩባንያ እንደትልቅ የሚዲያ አውታርነት የማይፈቅዳቸው ጽሁፎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነሱም ቀጥተኛ ዛቻ፣ ራስን በራስ ማጥፋትን ማበረታታት እና የመሳሰሉት በፌስቡክ የሚዲያ አውታር ላይ የተከለከሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፌስቡክ 2 ቢሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፍ አውታር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አፈጻጸሙን ማስተግበር አስቸጋሪ ስለሚያደርገው በዚህ ዙሪያ በጋራ የመስራትና ጉዳዩን የማስተካከል እንቅስቃሴ አንዱ የሕግ ማዕቀፉ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ አቶ ተስፋሁን፡፡

በሌላ በኩል የማሕበራዊ ሚዲያ የህግ ማዕቀፍ ሲባል ተራ ጉዳዮች ላይ የሚጠመድ ሳይሆን አገራዊና ሕዝባዊ ችግሮችን በማስወገድ ላይ ያመዘነ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎችም ሁኔታውን በአንክሮ የሚመለከቱትና ቦታ ሰጥተው የሚያዩት ተግባር ይሆናል፡፡

የማሕበራዊ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ያደረጉ አገራት

ሮይተርስን የመሰሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ደጋግመው እንደዘገቡት አንዳንድ የዓለም አገራት ማህበራዊ ሚዲያን ከመቆጣጠር አንጻር ቀድመው ሄደውበታል፡፡ በዚህ ላይ አውሮፓዊቷ አገር ጀርመን እና የኢሲያዋ አፍጋኒስታን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ አላስፈላጊ መልዕክቶችን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ ከማውጣት ጀምሮ ተግባራዊ እስከ ማድረግ ብዙ ተራምደዋል፡፡ችግሩ የሁሉም አገሮች እንደሆነ መገመት ባያዳግትም ማህበራዊ ሚዲያው እንደየአገራቱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ግን ይለያያል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አገራት ጉዳይ ቢሆንም የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ግን እንደ ሁኔታቸው እንደሚለያይ አቶ ተስፋሁን ይገልጻሉ። ለአሜሪካ የምርጫ ማስታወቂያዎች በምርጫ ውጤት ላይ ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው ማድረጉ፣ ለቻይና የርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖን መገደብና የአገር ውስጥ የኢንተርኔት ኩባንያዎችን ከመዋጥ መከላከል፣ ለአውሮፓ አገራት የዜጎች መረጃ በኩባንያዎቹና አብረዋቸው በሚሰሩ ኩባንያዎች መበዝበዝ፣ በአንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታይ የሚበዛባቸው አገራት ደግሞ የሃይማኖት መንቋሸሽን መግታት ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ለማንኛውም አገራት የጋራ ችግር ናቸው የተባሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች ስጋት ደግሞ የሀሰት ወሬ (Fake News)፣ የጥላቻ ንግግር (Hate Speech)፣ አክራሪነት (Extremism) እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡የጀርመን መንግስት በዋናነት ከላይ የተነሱትን የጋራ ችግሮች በዜጎቹ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል የሕግ ማዕቀፉን በማውጣት ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን የአፍጋኒስታን መንግስት በአንጻሩ በኃይማኖት ዙሪያ የሚሰነዘሩ አሉታዊ ገጽታ ያላቸውን መልዕክቶችን ለመመከት ማዕቀፉን ስራ ላይ አውሏል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ብሔር ብሐሔረሰቦች ሀገር፣ የበርካታ ኃይማኖቶች መገኛ እና መሰል ሁነቶችን በማስተናገድ ላይ ለምትገኝ አገር የማህበራዊ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍ ከምንግዜውም በላይ አስፈላጊና ወቅታዊ ጉዳይ ያደርገዋል፡፡

ለመሆኑ የሕግ ማዕቀፉ ማንን ይጠቅማል?

ሕግና ኅብረተሰብ ጠንካራ ቁርኝት አላቸው፡፡ ኅብረተሰብ በሌለበት ሕግን ማሰብ፣ ሕግ በሌለበት በሥርዓት የሚኖር ኅብረተሰብን ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜም የሕግ ማዕቀፎች ኅብረተሰቡ ያልደረሰበትን ለውጥ ለማስገኘት የማይተካ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚወጡ እሴቶችንና ባህሎችን ወደ ሕግ ደረጃ በማሳደግም የኅብረተሰቡን ሕልውና ማስቀጠል ይቻላል፡፡ እነዚህ የተሳሰሩ ግንኙነቶች ኅብረተሰቡ ከሕግ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያሰፉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ሕጉ ከኅብረተሰቡ ዕድገት ወደኋላ ከቀረ ከወረቀት ያለፈ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ሲባልም መመሪያዎችን የማውጣት፣ የማስፈጸም፣ ፈቃድ የመስጠት እና አስተዳደራዊ እርምጃ የመውስድ  ስልጣንን ያጠቀላል ሲሉ አቶ ተስፋሁን ይገልጻሉ።

አገር አቀፍ የማሕበራዊ ሚዲያ የህግ ማዕቀፍ ከማውጣት አኳያ እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ አስመልክተው ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በተወሰኑ አካላት ብቻ እንደማይፈጸም እና በቀጥታ ማዕቀፉ የሚመለከታቸው ተቋማት ሌሎችን አስተባብረው የሚሰሩት ነው ይላሉ:: በእርግጥ በእኛ አገር ደረጃ የማሕበራዊ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣት ጠንከር ያለ ጥናት እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ ሳያሰምሩበት አላለፉም፡፡

እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ግንዛቤ መፍጠርን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን ቀዳሚ ተደርገው እንዳስፈላጊነቱ የሚሰሩ የሕግ ማዕቀፎችን ማውጣት ተገቢ መሆኑን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የማህበረሰብን ብሎም የአገርን ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት የማስቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ የወንጀለኞችን አደገኛ መልዕክቶች ለመከላከል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና ከማህበረሰቡ፣ ከኩባንያዎች፣ ከመንግስትና መሰል አካላት ጋር ተጋግዞ መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ አቶ ተስፋሁን ይገልጻሉ፡፡

ከማሕበራዊ ሚዲያ ደንበኞች ምን ይጠበቃል?

የማህበራዊ ሚዲያ ደንበኞች ጥቅምና ጉዳት ተገንዝቦ ስጋቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የራሱ የግለሰቡና የማህበረሰቡ ብሎም የአገር ጉዳይ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጠቃሚዎች ወደ ራሳቸው የዕይታ መረብ (Time Line) መልዕክቶች ሲገቡ ዕውነትነታቸውን ማረጋገጥና ጓደኞቻቸው ጸያፍ መልዕክቶችን ሲለጥፉ እንዲያስተካክሉ መምከር ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ለችግሩም ሆነ ለበጎው ባለቤቱ እሱ ራሱ ስለሆነ መንግስት ለሚያከናውናቸው ሕጋዊ ተግባራት ከጎኑ ሊሰለፍ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ምክረ-ሃሳቦች ማህበራዊ ሚዲያን አወንታዊና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል በጥቂቱ ተዘርዝረው የቀረቡ ሲሆን፤ ማንኛውም ተጠቃሚ ተግባራዊ ቢያደርጋቸው የሚያገኘው ጠቀሜታ እጅጉን የጎላ ነው፡፡

 • የግል ሚስጥርን ብሎም መረጃን በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ፤
 • በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንጋራቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ መመርመር፤
 • ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የምናሳልፈውን ሰአት መቆጣጠርና በራስ ተጽእኖ ስር ማድረግ፤
 • የታዳጊ ልጆችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና የጓደኞቻቸውን ዝርዝር ማጤንና መከታተል፤
 • ወላጆች የቤተሰብ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደንቦችን ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ፤
 • ለታዳጊ ልጆች በማህበራዊ ሚዲያ ጠንቅና ጠቀሜታ ዙሪያ ማስተማር፤
 • ከማያውቁትና አጠራጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ለማውራት ፍቃደኛ አለመሆን፤

በአጠቃላይ ማህበራዊ ሚዲያ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን እና ማህበራዊ ህይወታችንን እንዳይሸረሽረውና ባህላችንን እንዳያናጋው ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡ በሌላም በኩል ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ለመጠቀምና የጎንዮሽ ጉዳቶቹን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግን መሰረት ያደረገ ቁጥጥር ማስፈን እንደሚያስፈልገው እሙን ሲሆን፤ ለዚህም መንግስት የራሱን ጥናትና ምርምር በማድረግ ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ችግሩን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ማህበረሰቡ (ተጠቃሚው) በዚህ ላይ የራሱን ድጋፍ በማሳየት ለተግባራዊነቱ መትጋት አለበት፡፡

 

 

 


   ሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም

ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

ራዕይ

 • በ2017 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብቃት ያለው እና በሀገሪቱ ህዳሴ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ብሄራዊ የሳይበር ሴኪዩሪቲ ተቋም እውን ማድረግ፡፡   

ተልዕኮ

 • የአገሪቱን ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፡፡

እሴቶች

 • ተዓማኒነት
 • ሁሌም መማርና ማደግ
 • ልዩነት መፍጠር 
 • ተጠያቂነት

Web Content Display Web Content Display

 
 
INSA

ያግኙን ያግኙን

ስልክ: +251-11-371-71-14
ፖ.ሣ.ቁ: 124498
ኢሜል: contact@insa.gov.et
ፋክስ: +251-11-320 40 37
አድራሻ: አዲስ አበባ,ኢትዮጵያ