Skip to Content
  • Drop an Email contact@insa.gov.et
  • Get in Touch +251-113-71-71-14
ደህንነቱ የተጠበቀ ሳይበር ለሰላም ፣ ለልማትና ዲሞክራሲ
Back

የሳይበር ምህዳር ልቅነት እና የሀገራት ሉዓላዊነት

መግቢያ

በአለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዋና ተዋናዮች ሀገራት፣ ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ናቸው። ይሁን እንጂ  በዘልማዳዊው የአለማችን የፖለቲካ መዋቅር የፖለቲካ ሃይል ክምችት በዋናነት በሀገራት ላይ ተወስኖ ይገኛል። ይህም የጦር ሃይልን የማደራጀት እና የመጠቀም፣ ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሃይል አማራጭን የሚጠቀሙት መንግስታት (Nation States) ብቻ ሁነው እናገኛቸዋለን። ይሁን እንጂ የኢንተርኔት ወይም ሳይበር  ልቅ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የሀገራት ሉዓላዊነት ዝቅ እያለ በተቃራኒው ሃይል የሚጠቀሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል።  በተለይም ደግሞ የሳይበር ምህዳር ለፖለቲካ አላማ ማራመጃነት እና ለፖለቲካ ተዋናዮች ዋና ምሽግ እየሆነ መምጣቱ ቀደም ሲል በሀገራት ላይ ተወስኖ የነበረው ልማዳዊ ሉዓላዊነት (Traditional Soverignity) እየተሸረሸረ እንዲመጣ አድርጎታል።  

 

በተለይም ዘርፉ ያልተማከለ (decentralized) እና የግል ሴክተሩ በዋናነት የሚያንቀሳቅሰው በመሆኑ በሀገራት ሉዓላዊነት እና የሳይበር አስተዳደርን በሚመለከት ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።   ይህንን ተከትሎም ሀገራት የሳይበር ምህዳራቸውን የመቆጣጠር ስልጣናቸው ምን ድረስ ነው? ሀገራት የግል የሳይበር ተዋናዮችን የመቆጣጠር አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሳይበር ምህዳርን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል? ሀገራት በሳይበር ህዋ ላይ የራሳቸው ሉዓላዊነት ስልጣን ካላቸው ወንጀለኞችን እንዴት መቆጣጠር ይችላሉ? የሳይበር ምህዳርን ለማስተዳደር የሀገራት የተጽዕኖ አቅም ምን ድረስ ነው? ወ.ዘ.ተ  የሚሉ ጥያቄዎች የተሟላ ምላሽ ያላገኙ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።

በሀገራችን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለ የዘርፉ መስፋፋት በሃገሪቱ ሊኖር የሚችለውን የሳይበር ሉዓላዊነት ደረጃ መጠየቅ ወቅታዊ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ አንጻርም የሳይበር ምህዳር በሀገራችን ምን ያህል ከስጋት ነጻ መሆኑን እንዲሁም የሳይበር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እየተደረጉ ያሉ የሳይበር አስተዳደር፣ የህግ ማዕቀፎች እና የቁጥጥር አቅሞች ምን ድረስ እንደሆነ መዳሰስ ይኖርበታል።

 

የሳይበር ምህዳር ምንድን ነው?

የሳይበር ምህዳር ሶስት መሰረታዊ ማለትም አካላዊ (physical)፣ አመክንዮአዊ (logical) እና ማህበራዊ (social) ጉዳዮችን አጣምሮ የያዘ ከባቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። አካላዊ ስንል የሚጨበጡ እና የሚዳሰሱ የኮምፒውተር  እና መልከዓ ምድራዊ ጉዳዮችን ያቀፈ ሲሆን አመንክዮአዊ የምንለው ደግሞ የኔትወርክ መሰረተ-ልማቶችን እና ትስስሮችን ያካትታል። ማህበራዊ ስንል ደግሞ የሰብአዊ ተጽዕኖዎችን እና ስርዓቱን የሚያሽከረክሩት የሰው አዕምሮአዊ እና ግንኙነቶችን ያካትታል። በአጭር አገላለጽም የሳይበር ምህዳር ስንል የሚዳሰሱ ቁሶችን እና የማይዳሰሱ ምናባዊ (virtual) እሳቤዎችን አጣምሮ የያዘ ኮምፒውተርን፣ የኮምፒውተር መረብን፣ የተጠራቀመ ዳታን እና የኮምፒውተር ኔትወርክን አቅፎ የያዘ ክልል በማለት መግለጽ ይቻላል። በአጠቃላይ ሳይበር የመሰረተ-ልማት፣ የኢንፎርሜሽን፣ ኢንፎርሜሽኑን እና መሰረተ-ልማቱን የሚያስተዳድሩ ስርአቶች፣ ኢንፎርሜሽኑን ወደ እውቀት የሚቀይርና የሚጠቀም የሠው ኃይል እንዲሁም የህብረተሰብ ባህል መስተጋብር ውጤት ነው፡፡

 

የሳይበር ከባቢ ወይም ምህዳር ያልተማከለ፣ ባልታወቁ አካላት ሊመራ የሚችል፣ ዘርፈ ብዙ እና በየጊዜው እየተለዋወጠ የሚሄድ እንደመሆኑ መጠን በሀገራት ደህንነት፣ ዳር ድንበር፣ የሰብአዊ መብት፣ ግለኝነት እና ሉዓላዊነት በሚሉ የአንድ ሀገር ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው። ይህም የቴክኖሎጂ መለዋወጥን ተከትሎ ነባር የነበረውን የሀገራት ሉዓላዊነት እንዲሸረሸር እና የሳይበር ሉዓላዊነት እስከምን ድረስ የሚል ሃሳብ እንድናነሳ ያስገድደናል።

 

በዚህ ረገድ የሳይበር ምህዳር ዓለም አቀፋዊ የጋራ መገልገያ ነው የሚሉ አካላት የሀገራት ሉዓላዊነት በምህዳሩ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ዝቅተኛ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ እንደ እነሱ ገለጻ  የሳይበር ምህዳር እንደ ውቅያኖስ፣ አየርና ህዋ ከሰው ልጅ ርስት ውጪ የሆነና አካላዊ ምህዳርና ድንበር የሌለው ነው፡፡

ምንም እንኳን የሳይበር ምህዳር ዓለም አቀፋዊ የጋራ መገልገያ ይሁን እንጂ ዓለም አቀፋዊ አይደለም፡፡ ምህዳሩ ድንበር የለሽ ይሁን እንጂ የሚጠቀማቸው መሰረተ-ልማቶች በድንበር የተገደቡ ናቸው፡፡ ይህንንም በመጠቀም ሀገራት ምህዳሩን ለመቆጣጠርና ምናባዊ የሆነ ድንበር ለመገንባት ጥረት እንሚያደርጉ የማይጠረጠር ነው፡፡ በሌላ በኩልም ምህዳሩ የግል ንብረትም ያልሆነ፣ ሉዓላዊ ግዛት የሌለው እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የጋራ መገልገያ ያልሆነ ምናባዊ የህብረት ንብረት አድርጎ የሚመለከቱም አሉ፡፡

 

የሳይበር ምህዳር እና ሉዓላዊነት ትስስር

ሉዓላዊነት አንድ ሀገር በዳር ድንበሩ ላይ ሙሉ ራሱን የመጠበቅ እና የማስከበር ስልጣንን የሚያመላክት ጽንሰ-ሃሳብ ነው። በዚህም በአለም አቀፍ ግንኙነት ከሚጠቀሱት ሶስቱ ተዋናዮች ማለትም ሀገራት፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች መካከል ሙሉ የፖለቲካ ሃይል የመተግበር ስልጣን በሀገራት ላይ የተወሰነ ነው። በዚህም ሀገራት ባላቸው የግዛት ዳር ድንበር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትንም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ግዑዝ አካላትን የሚገዛ ህግ የማውጣት፣ የመተግበር፣ ጣልቃ የመግባት እና የመምራት የውስጥ ሉዓላዊነት እንዳላቸው የሞንትቪዲዮ ኮንቬንሽን (Montevideo Convention) ያስረዳል። በተመሳሳይ ዳር ድንበሩን ከማንኛውም የውጭ ሃይል የማስጠበቅ፣ ይህንን ለማድረግም ሃይል የመጠቀም፣ ወታደራዊ ሃይል የማንቀሳቀስ  እንዲሁም ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመመከት አለም አቀፋዊ ሉዓላዊነት (international sovereignty) አላቸው። በተጨማሪም ከሌሎች ሀገሮች ጋር በሚኖረው ትስስር እና ግንኙነት በእኩል ደረጃ የመወዳደር እና ድምጽን የማሰማት ሉዓላዊ ስልጣን እንዲሁም በማንኛውም የውጭ ሃይል ያለመደፈር መብት አለው። ይሁን እንጂ የሳይበር ምህዳር መፈጠርን ተከትሎ ሳይበር ምህዳር በባህሪው ያልተማከለ በግለሰቦች የሚተዳደር በመሆኑ የሳይበር ምህዳር አስተዳደር እና የሀገራት ሉዓላዊነት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል። በመሆኑም የሳይበር ምህዳር ያልተማከለ አስተዳደር እና የሀገራት ሉዓላዊነት አመጣጥኖ ማስቀጠል የዘርፉ ጥያቄ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

 

የሳይበር ሉዓላዊነት

የሀገራት ሉዓላዊነት መሰረት ከጣለው የዌስትፋሊያ ውል ማለትም 1648 ጀምሮ የሀገራት ጂኦግራፊያዊ ድንበር አይደፈሬነት እና ከማንኛውም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት ነጻነት ተከብሮ እና የአለም ስርዓትን ሲገዛ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ የሳይበር ምህዳር ሉዓላዊነት ጉዳይ አወዛጋቢ ጽንስ ሃሳቦችን ይዞ ይገኛል። የቀደመው ሉዓላዊነት የሚያተኩረው የድንበር አይደፈሬነት ላይ ቢሆንም የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የኢንተርኔት አብዮት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት መከሰት በሳይበር ምህዳር ኔትወርክ ላይ በሚደረግ የሀገራት እንቅስቃሴ የስልጣን ገደብ የወቅቱ የሳይበር ሉዓላዊነት ጥያቄ ማጠንጠኛ ሁኗል።   

የሳይበር ሉዓላዊነት ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ የመጣውም የሻንጋይ ትብብር ድርጅት (Shanghai Cooperation Organisation) አባል ሀገራት ማለትም ቻይና፣ ሩሲያ፣ ታጃኪስታን እና ኡዝቤኪስታን በ2011 ባዘጋጁት "የኢንፎርሜሽን ደህንነት አለም አቀፍ ኮድ" በሚል ረቂቅ ህግ በማቅረብ የሳይበር ሉዓላዊነትን ህጋዊ መሰረት ለማስያዝ ጥረቶች ተደርገዋል። ሀገራቱ ባዘጋጁት ኮድ ሀገራት በሌሎች ሀገራት የሳይበር ህዋ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ገደብ የሚያትት ሲሆን በመግቢያው ላይ፡ 

"…ከኢንተርኔት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የሀገራት ሉዓላዊ መብቶች ናቸው። ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ አለም አቀፍ ጉዳዮችን በሚመለከትም መብቶች እና ግዴታዎች አሏቸው።"  ሲሉ አመላክተዋል።

የሳይበር ሉዓላዊነት ጥያቄም የተለጠጠ የሳይበር ጥቃትን ከመመከት አኳያ የሚታይ ነው። በዚህም የሳይበር ጥቃት የኮምፒውተር መረብን በመጠቀም ዳታ መበዝበር እና ሀብት እና ዳታ ከመስረቅ ባለፈ ሃይል በመጠቀም ትልቅ ኪሳራዎችን ሊያደርስ የሚችል ለአብነትም የሳይበር ጥቃትን በመጠቀም የኒውክሌር ማብላያዎችን ማቅለጥ፣ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ በመጠቀም የአውሮፕላን ግጭት መፍጠር፣ ወዘተ የሳይበር ሉዓላዊነት ጥያቄን ወሳኝ እና አንገብጋቢ ያደርገዋል።  

በሳይበር ምህዳር ላይ መኖር ስላለበት ሉዓላዊነት አንድ አይነት አቋም የማይታይ ሲሆን ሁሉም ሀገራት የሳይበር ምህዳር አለም አቀፋዊ የጋራ መገልገያ ይሁን አይሁን፣ ከሉዓላዊነት ጋር በማይጣረስ መልኩ ሊተዳደር በሚችልበት ሁኔታ እና በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ይዘው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻርም የሳይበር ሉዓላዊነት እና የኢንተርኔት ነጻነት በሚመለከት ሁለት የጽንሰ-ሃሳብ ጎራዎች ይገኛሉ። እነዚህም ነጻ  የሳይበር ምህዳር (Cyber-Libertarianism) እና የሳይበር ኮሌክቲቪዝም (Cyber-Collectivism) ጽንሰ-ሃሳቦች ናቸው፡፡

ነጻ የሳይበር ምህዳር (Cyber-Libertarianism) ጽንሰ-ሃሳብ ግለሰቦች በማንኛውም አቅጣጫ በግለሰብ፣ በድርጅት፣ በቡድን እንዲሁም በሚፈልጉት አቅጣጫ ፍላጎታቸውን "በኦንላይን" ለመግለጽ ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን አለባቸው የሚል ፍልስፍና ነው። ይህ ጽንሰ-ሃሳብ መንግስታት በኢንተርኔት ላይ የሚያደርጉትን ዕቀባ ሙሉ በሙሉ ማንሳት አለባቸው የሚል ሲሆን ነጻ የኢንተርኔት ፍሰት መኖር አለበት የሚል ነው። ይህ የሳይበር ኒዮሊበራል ጽንሰ-ሃሳብ እውነተኛ የኢንተርኔት ነጻነት ከማንኛውም የሀገራት ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ነው የሚል እምነት ያለው ሲሆን ከኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ነጻነት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ያስረዳል። በዚህም ማህበራዊ ነጻነት ግለሰቦች በሳይበር ምህዳር የፈለጉትን አመለካከት የማራመድ፣ የመሞገት፣ ሃሳባቸውን የማንጸባረቅ ነጻ መብት እንዳላቸው የሚደነግግ ሲሆን  ከኢኮኖሚ አንጻርም ማንኛውም ግለሰብ የሳይበር ምህዳርን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ጉዳዮች የመለዋወጥ፣ የመተግበር፣ የመጠቀም እና የማስፋፋት ነጻ ምርጫ እንዳላቸው ያስቀምጣል።

በሌላ በኩል ሳይበር ኮሌክቲቪዝም (Cyber-Collectivism) ጽንሰ-ሃሳብ የሳይበር ሊበርታሪያኒዝም ተቃራኒ ሲሆን የኢንተርኔት አጠቃቀም በመንግስታት ቁጥጥር ስር መዋል እንዳለበት ያምናል። በዚህም የኢንተርኔት ተጽዕኖ በሀገራት ደህንነት፣ ባህል እና በማህበረሰብ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር የሀገራትን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚፈታተን በመሆኑ መንግስታት መቆጣጠር እና በፈለጉት አቅጣጫ መምራት አለባቸው የሚል ነው።  

በሌላ በኩል በሳይበር ምህዳር አስተዳደር ውስጥ ማን መሳተፍ አለበት፣ ሳይበር ምህዳር እንዴት መተዳደር አለበት፣ ቁጥጥሩ እስከየት ድረስ መሄድ አለበት የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሶስት የሳይበር ምህዳር አስተዳደር ስልቶችን/መንገዶችን ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህም ያልተማከለ አስተዳደር (Distributed Governance)፣ የብዙሀን (የጋራ) አስተዳደር (Multilateral governance)፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት (Multi-stakeholderism) አስተዳደር ስልቶች የሚሉት ናቸው። 

ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት በጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ያለውን የአስተዳደር ስርአት በመጀመሪያው ወይም ባልተማከለ አስተዳደር ስር መመደብ ይቻላል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው አስተዳደር የተወሰነ፣ ያልተደራጀና መረጃ ነጻና በቁጥጥር ስር መሆን የለበትም በሚሉ የኦን ላይን ማህበረሰብ የተገደበ ነበር፡፡ ይህ ዘዴ ኦን ላይን ማህበረሰቦች ትንሽ፣ አንድ አይነትና ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉበትን ዘመን ነበር። እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከ1 ሚሊዮን በታች የነበሩ ሲሆን የሳይበሩ ምህዳር በማንኛውም ሀገር ድንበር ስር እስካልተገኘ ድረስ በመንግስታት ቁጥጥር መዋል የሌለበትና የራሱ የሆነ ማህበራዊ ስምምነት ሊኖረው እንደሚገባ የሚከራከሩበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰአት የሳይበር ምህዳር እጅጉን የዘመነበትና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት ከመሆኑም ባሻገር ዘርፉ እየተወሳሰበ መጥቷል። ይህንን ተከትሎም የሳይበር ምህዳር የቁጥጥሩን ፍላጎት እየጨመረ እንዲመጣ እና ያልተማከለ አስተዳደር ስርአት አሁንም በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ አገልግሎት ላይ እየዋለ ቢገኝም ለዚህ ዘመን በሳይበር ምህዳር ላይ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ጥያቄ አስነስቷል፡፡

የሀገር ሉዓላዊነት ከፍተኛ አትኩሮት የሚሰጠው በሁለተኛው ወይም በብዙሃኑ የአስተዳደር ስርአት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ዘዴ ሀገርን ማዕከል ያደረገ ሲሆን የሳይበርን ምህዳር ለደህንነት አስጊ የሆኑ ነገሮችን የሚያመጣ ብጥብጥ የበዛበት ስርአት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ለዚህም ሀገራት ለሳይበር ምህዳር አስፈላጊ የሆኑ ፖሊሲዎችን ማውጣት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ዘዴው በተባበሩት መንግስታት ስር የሳይበርን ምህዳር ማስተዳደር የሚችል አንድ አካል መፈጠር አለበት ሲል ይከራከራል፡፡ ምንም እንኳን መሰል የጋራ አለም አቀፋዊ የሳይበር ምህዳር አስተዳዳሪ አካል መቋቋም አንዳለበት ዘዴው ቢጠቁምም ሀገራት የራሳቸውን ብሄራዊ ፖሊሲዎች መቅረጽ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ይህ ስልት /ሞዴል/ በሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ኢራንና ሳውድ አረቢያ ይደገፋል፡፡

በጎግል፣ ፌስቡክና ቲውተር የወጡ ግላዊ ፖሊሲዎች ለዲጂታል ሉዓላዊነትና ለብሄራዊ ደህንነት በመንግስታት በኩል እንደ ስጋት መታየት ጀምረዋል፡፡ በዚህም የዲጂታል ንብረታቸውንና ወሳኝ የሚባሉ መሰረተ-ልማቶቻቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ የሚወስዱት እንቅስቃሴ በሳይበር ምዳር ውስጥ ክፍፍልና ወደ ጥቃቅን ተፎካካሪ /ተቃራኒ/ መንግስታት ሊወስደው እንደሚችል የሚያሳዩ ክርክሮች ይነሳሉ፡፡ ሀገራት አሁን ካለው ኢንተርኔት እራሳቸውን በማውጣት የራሳቸውን ቀጠናዊ ወይም ብሄራዊ የተገደበና ግላዊ የሆነ የግንኙነት መረብ (Intranet) መዘርጋት ይችላሉ፡፡ ሀገራት ብሄራዊ የሆነ የሳይበር ምህዳርን የመፍጠር፣ ውቅያኖስ አቋራጭ የሆኑ መስመሮችን የመገንባት እና የኢንተርኔት መረጃዎችን በድንበራቸው ውስጥ ባሉ ሰርቨሮች ላይ የማከማችትን አማራጮች እየፈተሹ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም ከአለም አቀፋዊ ግንኙነቶች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች ያስቀድማሉ/ይመርጣሉ፡፡

የብዙሃን አስተዳደር ዘዴ /ሞዴል/ አራማጆች የኢንተርኔት አስተዳደር "በዌስትፋሊያ" የተደነገገውን የሀገራት ሉዓላዊነት ማክበርና የአለም አቀፉን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ህብረትን መምሰል አለበት ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የዲጅታል ሉዓላዊነትና የመረጃ ደህንነት የብዙሃን አስተዳደርን በሚያራምዱ ሀገራት ዘንድ በዋንኛነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ሌላው ለብዙሃን አስተዳደር እንደምሳሌ የሚታየው የሻንጋይ ትብብር ድርጅት (Shangahai Cooperation Organization/SCO/) ነው፡፡ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ኢራንና ሌሎች የመካከለኛው ኢስያ ሀገራት የኢንተርኔት ደህንነት ፖሊሲዎቻቸውን በዚህ ድርጅት በኩል በማቀናጀት በኢንተርኔት የሚካሄዱ የፖለቲካ አመጾች/ረብሻዎች መመከት የሚያስችል የሳይበር እንቅስቃሴ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

ከላይኛው ዘዴ እጅጉን በተለየ መልኩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስተዳደር (Multi-stakeholderism) ሀገራትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የቢዝነሱንና የሲቪል ማህበረሰቡን የሚወክሉ አካላትን ያካትታል፡፡ ይህ ዘዴ መንግስት ብቻውን የሳይበርን ምህዳር ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊቆጣጠረው እንደማይችል ያስረዳል፡፡ ስለዚህ እንደ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የመፈለጊያ ኢንጂን ካምፓኒዎች (እንደ ጎግልና ማይክሮሶፍት ያሉ)፣ የቴክኒካል ነክ ጉዳዮች ህብረቶች /አካላት/ ኢንተርኔትን በማስተዳደር ረገድ መሳተፍ አለባቸው፡፡ የዚህ ሞዴል አራማጆች እንደሚሉት  የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ልማዶችን (Norms) ሊቀበሉ የሚችሉ የቀረጻው አካል ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህም በሳይበር ምህዳር ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶችን፣ ካምፓኒዎችና ተቋማትን ተቀባይትና ስልጣን ያሳድጋል፡፡ ይህ ዘዴ በአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና እንደ ጎግል ባሉ ተቋማት ተቀባይነት አለው።

ድንበር የለሽነት፣ ተጣጣፊነት፣ ተለዋዋጭነት እና አሳታፊነት የሳይበር ምህዳር መገለጫዎች ናቸው። የሳይበር ሉዓላዊነትም አጠቃላይ የኢኮኖሚው እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከኢንተርኔት እና ቴክኖሎጂ ጋር ካላቸው ጥገኝነት ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ አንጻርም የሳይበር ሉዓላዊነት መደፈር ወይም ማስተዳደር በሀገራት ካለ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ጋር ተያያዥነት አለው። የሳይበር ጥቃትን ለመዳኘት አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ህጎች ተግባር ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ከአለም አቀፍ ህግ አንጻር ሀገራት ማንኛውንም በሳይበር ምህዳር የሚያደርጉትን ተግባር ሲያከናውኑ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት በማይጻረር መልኩ መሆን እንዳለበት ያትታል።  በተለይም ደግሞ የሳይበር ምህዳር ትስስር ድንበር ተሻጋሪ እና በአንድ ሀገር ላይ የደረሰ ጥቃት በሌሎች ላይም ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በአንድ ሀገር ላይ ዒላማ ያደረገ ኦፕሬሽን ሌሎችን ሊጎዳ ስለሚችል በአለም አቀፍ ህግ መተዳደር ግድ እንደሆነ ያስረዳናል። ሀገራት የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከልም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 51 በሚያዝዘው መሰረት የኮምፒውተር ኔትወርክን በመጠቀም የሚደርስን ጥቃት ራስን የመከላከል መርህን ተንተርሰው መመከት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።


   ሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም

ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

ራዕይ

  • በ2017 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብቃት ያለው እና በሀገሪቱ ህዳሴ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ብሄራዊ የሳይበር ሴኪዩሪቲ ተቋም እውን ማድረግ፡፡   

ተልዕኮ

  • የአገሪቱን ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፡፡

እሴቶች

  • ተዓማኒነት
  • ሁሌም መማርና ማደግ
  • ልዩነት መፍጠር 
  • ተጠያቂነት

Web Content Display Web Content Display

 
 
INSA

ያግኙን ያግኙን

ስልክ: +251-11-371-71-14
ፖ.ሣ.ቁ: 124498
ኢሜል: contact@insa.gov.et
ፋክስ: +251-11-320 40 37
አድራሻ: አዲስ አበባ,ኢትዮጵያ