Skip to Content
  • Drop an Email contact@insa.gov.et
  • Get in Touch +251-113-71-71-14
ደህንነቱ የተጠበቀ ሳይበር ለሰላም ፣ ለልማትና ዲሞክራሲ
Back

ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት አቅም መገንባት … የጋራ የቤት ሥራ

ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ተልዕኮዎች መካከል፤ ብሔራዊ የሃይቴክ እና ሴኪዩሪቲ ኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲረጋገጥ የዳታና ኮምፒቲንግ አቅምን ማልማት አንዱ ነው፡፡ ኤጀንሲው በሀገራዊ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ፤ በተለይም ደግሞ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር ላይ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በማልማትና ደህንነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ ሀገራዊ የሳይበር ኢንዱስትሪ እንዲነቃቃና እንዲያድግ በዘርፉ ከተሰማሩ ሀገር በቀል የግል ተቋማት ጋር በጋራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የኢመደኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በኤጀንሲው ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉ የቴክኖሎጂ ልማት ፕሮግራሞችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ (የሐምሌ 15/2017 እንግሊዝኛ ዕትም) ጋር ሰፊ ቆይታ አድርገዋል፡፡ ይህንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች በሀገሪቱ አቅም ማምረት የማይቻልና አዋጭ ባለመሆኑ በተመረጡ የቴክኖሎጂ ከባቢዎች ላይ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ማረጋገጥ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን ከማረጋገጥ አንጻር ኢመደኤ ብቻውን የሚወጣው ሃላፊነት እንዳልሆነና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ የመንግስትና የግል ተቋማት ሃላፊነት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ረገድ ኤጀንሲው በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የመንግስትና የግል ተቋማት ደህንነታቸው (ከግንዛቤና ንቃተ-ህሊና፣ ከፖሊሲና ከስርአት፣ ከመሰረተ-ልማት፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ አንጻር) እንዲረጋገጥ የማድረግ ስራ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በመቀነስና ባለቤትነትን በማረጋገጥ በኩል ኮር የሆኑ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞችን የማበልጸግና የማልማት ስራ ነው፡፡

የተቋማትን የኢንፎርሜሽን ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር እንደ ሀገር በአንጻራዊ መልኩ በፊት ከነበርንበት ደረጃ መሻሻሎች እንዳሉ የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ ማለት ግን የተሟላ የደህንነት ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ፣ የቴክኖሎጂ አቅም፣ የፖሊሲና የአሰራር ስርአት፣ እንዲሁም መሰረተ-ልማት ፈጥረናል ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የመከላከያና ደህንነት ተቋማትን፣ የፋይናንስ ተቋማትን እና ቁልፍ መሰረተ-ልማቶችን ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ደህንነታቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ሲሆን በሂደት ሁሉንም የመንግስትና የግል ተቋማት መድረስ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በተለይም የደህንነት ጉዳይ የሁሉም የመንግስትም ይሁን የግል ተቋማት ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ መፈጠሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን፤ ይህ ግንዛቤ ከተፈጠረና ፋይዳውን በትክክል መረዳት ከተቻለ ተቋማት በደህንነት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሚሆኑ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡   

ኮር የሆኑ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞችን በማልማትና በማበልጸግ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ተቋማት (እንደ Microsoft, Oracle, SAP) ያበለጸጓቸውን ጨዋታ ቀያሪ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞች፤ ማለትም ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች፣ የተለያዩ አፕሊኬሽን ፕላትፎርሞች (Enterprise Resource Planning /ERP System/, Core Banking System, National Payment System etc.) በሀገራዊ አቅም የማበልጸግ አቅጣጫ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ ም/ዋና ዳይሬከተሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በሁሉም ኮር ቴክኖሎጂዎች ላይ አበረታች የሚባሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ኮር የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞች መካከል አንዱ ሀገር አቀፍ የክፍያ ስርአት (National Payment Platform) ሲሆን፤ ከዚህ አንጻር ኤጀንሲው "ደራሽ" የተሰኘ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርም በማበልጸግ ከ2010 የበጀት አመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ፕላትፎርሙ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀላል የሆነ የፋይናንስ ልውውጥ በመፍጠር ህብረተሰቡ ሳይንገላታ ባለበት ቦታ ሆኖ የተለያዩ ክፍያዎችን (የአገልግሎት ክፍያዎች፣ የባንክ ክፍያዎችን፣ ከቀረጥና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ ክፍያዎች ወ.ዘ.ተ) ለመፈጸም የሚያስችል ፕላትፎርም ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የነበሩ የክፍያ ስርአቶችን አቀናጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል ፕላትፎርም እንደሆነ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በሳይበር ኢንዳስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞችን የሚያለሙ ሀገር በቀል የግል ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እንደሆነ የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲው እነዚህን የግል ተቋማት የማበረታታት፣ የመደገፍና አብሮ የመስራት አቅጣጫ በማስቀመጥ ግልጽ የሆነ ስርአት ዘርግቶ እየሰራ እንደሆነም  ገልጸዋል፡፡ በተለይም ኤጀንሲው ቁልፍ በሆኑና በሀገራዊ አቅም መፈጠር ያለባቸው አቅሞች እንዲፈጠሩ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ ሲሆን፤ ከኤጀንሲው ኮር ተልእኮ ውጪ የሆኑ ስራዎችን ግን በውጭ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያለውን ጥገኝነትን በሚቀንስ መልኩ ሀገር በቀል የግል ተቋማት ሊሰሩበት የሚችል ሁኔታ በመፍጠርና እነሱን በማብቃት የመስራት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በሌላም በኩል ሀገራዊ አቅም ባልተፈጠረባቸው የቴክኖሎጂ ፕላትፎርሞች ላይ ጥገኝነትን በዘላቂነት በሚፈታ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያረጋግጥ መልኩ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በትብብርና በቅንጅት የመስራት አቅጣጫም ተቀምጦ እየተሰራ እንደሆነ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡    

ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በመቀነስ ረገድ በኤጀንሲው በኩል ተጨባጭ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንንም በአራት ተመጋጋቢ የእድገት ደረጃዎች ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም፡- ቴክኖሎጂውን ማወቅ፤ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተጠቃሚነት እንዲኖር ማድረግ፤ በቴክኖሎጂው ላይ እሴት በመጨመር መስራት፤ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት አቅምን የመገንባት ስራ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በኩል በርካታ ፈተናዎች እንዳሉት የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በዘርፉ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ የግል ተቋማት ይህንን ከመታገል አንጻር እሴት በመጨመር መርህ ላይ በማተኮር ለዘላቂ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡  

  

     

   


   ሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም

ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

ራዕይ

  • በ2017 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብቃት ያለው እና በሀገሪቱ ህዳሴ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ብሄራዊ የሳይበር ሴኪዩሪቲ ተቋም እውን ማድረግ፡፡   

ተልዕኮ

  • የአገሪቱን ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፡፡

እሴቶች

  • ተዓማኒነት
  • ሁሌም መማርና ማደግ
  • ልዩነት መፍጠር 
  • ተጠያቂነት

Web Content Display Web Content Display

 
 
INSA

ያግኙን ያግኙን

ስልክ: +251-11-371-71-14
ፖ.ሣ.ቁ: 124498
ኢሜል: contact@insa.gov.et
ፋክስ: +251-11-320 40 37
አድራሻ: አዲስ አበባ,ኢትዮጵያ