12ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ

12ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "በሕገ መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ዓርብ ሕዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ተከበረ፡፡

በዕለቱ "የፌዴራል ሥርዓት ምንነትና አስፈላጊነት፣ እያመጣ የሚገኘው ድሎችና እየገጠመው ያለው ፈተናዎች" በሚል መነሻ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዶ በርካታና ሰፊ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ የአገራችን የፌዴራል ሥርዓት ሕብረ-ብሔራዊነትን በማስተናገድ ደማቅ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝ ስርአት እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ ሕብረ-ብሔራዊነት ሕዝቦች በአንድ አገር ውስጥ ቋንቋቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ታሪካቸውንና መሰል ዕሴቶቻቸውን አክብረው አንድነትን የሚመሰርቱበት ስርአት እንደሆነም በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡ በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ከመገንባት አንጻር ጥረት ቢደረግም አንዳንድ ፈተናዎች እንደገጠሙትም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና በቅርቡ እያቆጠቆጠ የሚገኘው አክራሪ ብሔርተኝነት እንዲሁም ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርአቱን ከማስረጽ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው ይጠቀሳሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ (ዶ/ር) በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያውያን ማለት በብዙ ገመድ ታሪክ የተሳሰርን ህዝቦች መሆናችንንና ይህን ለማፍረስ የሚጥር ካለም ግብዝነት ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል አልፎ አልፎ የሚታዩ አለመረጋጋቶችን ከምንጩ ለማድረቅ መፍትሔው ለመማርና ለመስራት ዝግጁ መሆን አለብን ይህም ከጥገኝነትና ከጠባቂነት እንድንወጣ ይረዳል ብለዋል፡፡