ኢመደኤ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሰራው የERP ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2010 ዓ/ም፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሰራው Enterprise Resource Planning System (ERP) ፕሮጀክት በይፋ ተመርቋል፡፡

የኢመደኤ ም/ዋና ዳይሬክተር ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋማት አጠቃላይ ሥራዎቻቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ ቴክኖሎጂ በመደገፍና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ፍላጎቶች እንዳለ ገልጸው ከዚህ አኳያ ኢመደኤ በተሰጠው ተልዕኮ ላይ መሰረት በማድረግ ከቁልፍ ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ገልጸው፤ እንደነዚህ አይነት የፕሮጀክት ሥራዎች ሊሳኩ የሚችሉት በቅንጅትና ተቀራርቦ በመስራት እንደሆነም አስምረውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃ/ማርያም በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ድርጅታቸው በየቀኑ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እንደሚፈጽም ገልጸው፤ ይህንን ከፍተኛ ሃገራዊ ሃብት ታሳቢ በማድረግ ከጅቡቲ ወደብ እስከ ታችኛው ተጠቃሚ ድረስ ያለውን የድርጅቱን አሰራር በቴክኖሎጂ በመታገዝ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመምራትና ለመስራት በነበረው ፍላጎት ይህ ፕሮጀክት ሊሰራ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም የፕሮጀክት ሥራው 90 በመቶ የሚሆነውን የድርጅቱን ፍላጎት መመለስ እንደቻለም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

የERP ፕሮጀክት ዓላማ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የድርጅቱን አጠቃላይ አሰራሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማነቱን ማሳደግ ነው፡፡  በአጠቃላይ በዚህ ፕሮጀክት ሥራ አስር ያህል የተቀናጁ ሲስተሞች የተገነቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፤ Strategic Petroleum Reserve Administration System (SPRAS)፣ Property and Procurement Management System (PAPMS)፣ Integrated Budget and Financial Management System (IBFMS)  የሚጠቀሱ ናቸው፡፡