የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የሳይበር ደህንነት ጉባኤ ከሰኞ ሐምሌ 16/2010 ዓ/ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ህብረቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ ሐምሌ 14/2010 ዓ/ም፡ ጉባኤው በኮምፒዩተር እና ተያያዥ መሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያግዝ የቴክኖሎጂ ስርዓት መዘርጋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ አገሮች በተደራጀና ወጥነት ባለው ስልት የሳይበር ወንጀልን መከላከል በሚችሉበት መንገድ ላይም ውይይት ይደረጋል።

በአህጉሪቷ ሥራ ላይ እንዲውሉ የወጡ የሳይበር ስትራቴጂዎችና ህጎች ተፈጻሚ በሚሆኑበት ስልት ላይም አባል አገሮቹ ይነጋገራሉ ተብሏል።

የሳይበር ቴክኖሎጂ ለአህጉሪቷ እድገት የሚጫወተው ሚና እና የዘርፉ ፈተናዎች ከጉባኤተኞቹ የመወያያ አጀንዳዎች መካከል መሆናቸውንም የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።

የሳይበር ደህንነት ውጤታማነት ባለው መልኩ ለመተግበር ስትራቴጂካዊ እቅዶች ማዘጋጀት፣ መተግበር እና ተቋማዊ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ህብረቱ ጠቅሷል።

አፍሪካ በዚህ ረገድ የደረሰችበትን ደረጃ የተመለከተ ጥናት በጉባኤው ላይ እንደሚቀርብ ተመልክቷል።

በማላቦው የአፍሪካ ህብረት የሳይበር ደህንነት እና የግል መረጃ አጠባበቅ ስምምነት እንደዚሁም ቡዳፔስቱ የሳይበር ወንጀል መከላከል ስምምነት ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የማላቦ ስምምነት ከአራት ዓመት በፊት ቢጸድቅም እስካሁን ስምምነቱን የፈረሙት አስር የአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ፤ ስምምነቱን በፓርላማ አጽድቀው ተግባራዊ ያደረጉት ግን ሞሪሽየስና ሴኔጋል ብቻ ናቸው።

እ.አ.አ በ2001 በሀንጋሪ ይፋ የሆነውን የቡዳፔስት ስምምነትን በፊርማቸው የተቀበሉት ደግሞ ስምንት የአፍሪካ አገሮች ብቻ ናቸው።

ኢትዮጵያ እስካሁን ሁለቱንም ስምምነቶች አልፈረመችም።

ከሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የህብረቱ የሳይበር ጉባኤ ላይ አባል አገሮቹ፣ የሳይበር ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት (ኢዜአ)