የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር በሰኔ 16/2010 ሕዝባዊ ሠልፍ በተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ የተጎዱ ዜጎችን ጎብኝተዋል

ሰኔ 23/2010 ዓ/ም፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ "ለውጥን እንደግፍ፤ ዲሞክራሲን እናበርታ" በሚል መሪ ቃል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ እና መንግስታቸው እየወሰደ ለሚገኘው የለውጥ እርምጃ ድጋፍና ምስጋና ለመስጠት በተካሄደው ሕዝባዊ ሠልፍ ላይ በደረሰው የቦንብ ጥቃት የተጎዱ ዜጎችን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመገኘት ጎብኝተዋል፡፡ የኢመደኤ አመራርና ሠራተኞች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ደም መለገሳቸውን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲውና የኤጀንሲው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በቀጣይነት እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ 
ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ያላቸው የመንፈስ ጥንካሬ ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እያታየ ያለው የለውጥ ጉዞ ብርታት እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም መላው ማህበረሰብ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና መንግስታቸው እየወሰደ የሚገኘውን የለውጥ ጉዞ እንዲደግፍና ማናቸውንም የልማት እንቅፋቶች በቁርጠኝነት እንዲታገል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በአደጋው ወቅት ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችም መጽናናቱን ተመኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜናም ኢመደኤ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር የሚሰራቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እነዚህን ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ https://youtu.be/1ZtQ4obyA-U