ኡበር የተፈጸመበትን የሳይበር ጥቃት በመደበቁ የ148 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል

 

አዲስ አበባ መስከረም 18/2011፡- የዘመናዊ ተሸከርካሪዎች አምራች ኩባንያው ኡበር በ2016 የተፈጸመበትን የሳይበር ጥቃት ደብቆ ማቆየቱን ተከትሎ የ148 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

ኩባንያው በፈረንጆቹ 2016 በተፈጸመበት የሳይበር ጥቃት የ57 ሚሊዮን ደንበኞች የግል መረጃ እና የመንጃ ፍቃድ ቁጥሮች ቢጠለፍም ክስተቱን ሳያሳውቅ በመቅረቱ ነው ለቅጣት የተዳረገው፡፡

በወቅቱ ኩባንያው ስለ ሳይበር ጥቃቱ ለደንበኞቹ ከማሳወቅ ይልቅ ለመረጃ በርባሪዎቹ 100,000 ዶላር በመክፈል የመዘበሩትን መረጃ እንዲሰርዙ ማድረጉን ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም ባለፈው ህዳር 2017 የተወሰኑ መረጃዎችን ይፋ ቢያደርግም አሁን ላይ ስለ አጠቃላይ ጥቃቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ኡበር ከችግሩ ጋር በተያያዘም ሁለት የደህንነት ኦፊሰሮችን ከስራ ማባረሩን የገለጹት የኡበር ሃላፊ የሆኑት ዳራ ኮርስሮውሻሂይ ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት ተግባራትን እንደማይታገሱ ጠቁመዋል፡፡

በ2016 በተፈጸመው የሳይበር ጥቃትም 600,000 መንጃ ፍቃድ ቁጥሮችን ጨምሮ የ57 ሚሊዮን ደንበኞች የኡበር አካውንት ተመዝብሮ ነበር፡፡

https://www.bbc.com/news/technology-45666280