በአውሮፓ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ጠበቅ ያለ ህግ ወጥቷል

አንገብጋቢ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን የሚቆጣጠሩ የቴክሎጂ ድርጅቶች ማንኛውንም የሳይበር ጥሰት ለሚመለከተው ክፍል ሪፖርት እንዲያደርጉ አዲሱ ህግ ያስገድዳል፡፡ ህጉ ለባንኮች፤ ለሃይልና ውሃ ልማት አገልግሎቶች የሳይበር ደህንነታቸው የሚረጋገጥበትን  ሚኒመም ስታንዳርድም አስቀምጧል፡፡

ይህ በአውሮፓ ምድር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የወጣ ህግ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ የህጉ መውጣት በተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንደ አየር ማረፊያና የሃይል ስቴሽኖች ላይ ከሚደርስ የሰርጎ ገብ ጥቃት ለመታደግ ነው ተብሏል፡፡ ህጉ የኦንላይን የገበያ መገበያያ የሆኑትን እንደ ኢ ቤይ አማዞንና የሰርች ኢንጅን የሆነውን ጎግልን ጨምሮ የሚመለከት ዝርዝር ነገር ያካትታል ተብሏል፡፡

 በኔትወርክና ኢንፎርሜሽን ደህንነት ዙሪያ ይህን መመሪያ ለማውጣት የተገደድነው የሳይበር ጥቃት ስጋት እየጨመረ በመሄዱ ነው ሲሉም ህግ አውጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ 

የአውሮፓ የኔትወርክና ኢንፎርሜሽን ደህንነት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረትም የሳይበር ጥቃት በአመት ከ260 እስከ 360 ቢሊዮን ዩሮ ክስረት እንደሚያደርስ ነው፡፡ በአዲሱ ህግ መሰረት አባል ሃገራት የመረጃ ጥሰቶችን በመለዋወጥና በማልማት  ዙሪያ ተባብረውና ተሳስረው በመስራት  የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ህጉ ጠቁሟል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡