“የሳይበር አቅም ለተሻለች ኢትዮጵያ” በሚል የተጀመረው ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባጳጉሜ 2/2010 ዓ/ም

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት የተካሄደው የመጀመሪያው የውስጥ የሳይበር ኮንፍረንስ ዛሬ ተጠናቀቀ ፡፡

በሁለተኛ ቀን ውሎው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ እንዳሉት፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከፖሊቲካ ቅኝ-ግዛት ራሳችንን መጠበቅ ብንችልም ከቴክኖሎጂ ቅኝ-ግዛት መውጣት አለመቻላችንን ገልፀዋል፡፡ ሃገራችን ባለፉት ጥቂት አመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሃገራት በቀዳሚዎቹ ተርታ ብትሆንም ይህ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የቴክኖሎጂ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን በላይ አንስተዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በተጨማሪ እነዚህን መሰረተ-ልማቶች መጠበቅ እና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት / ሰለሞን ከህዋ ሳይንስ ጋር በተያያዘም ዘርፉ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የሃገራችንን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማጎልበት አንፃር  እንዲሁም የሳይበር ምህዳር ደህንነትን ከማስጠበቅ አኳያ አንድ ተቋም ብቻውን መከወን የሚችለው ተግባር ባለመሆኑ በመደመር መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም የሚመለከታቸው የምርምር ተቋማት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢመደኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ የኢኮኖሚ እድገት ያለ ቴክኖሎጂ የማይታሰብበት ደረጃ ላይ መደረሱን አንስተዋል፡፡ 
በሃገራችን ለሚደረገው የድህነት ቅነሳ እንቅስቃሴም ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ሃገሪቱ ለያዘችው የእድገት ውጥንም ተወዳዳሪ የሆነ የሳይበር ደህንነት ተቋም ከመሆን ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ በተቋም ደረጃ ብቻ የተደረገው የሳይበር ኮንፈረንስ ወደፊት በሃገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ሊሆን እንደሚገባ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ 

ባቀረቡት የምርምር ውጤት ተመርጠው ከ1-3 የወጡ እና ለሌች ተሳታፊዎች  በኮንፈረንሱ መዝጊያ ላይ ከኤጀንሲው ም/ዋ ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው ወርቁ ዕጅ የማበረታቻ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱን በንግግር የዘጉት ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው ወርቁ ለዝግጅቱ ስኬት አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን እና አዘጋጆቹን አመስግነው እንደዚህ ዓይነት ኮንፈረንስ ከተቋማችን ተልዕኮ ጋር የተዛመደ በመሆኑ በቋሚነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡