የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ለሰራተኞቹ ልጆች ያዘጋጀውን የህጻናት ማቆያ አስመረቀ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ለሰራተኞቹ ልጆች ያዘጋጀውን  የሕፃናት ማቆያ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በይፋ አስመርቋል፡፡ ከ6 ወር- 3 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ  ላሉ ልጆች አገልግሎት የሚሰጠው የህጻናት ማቆያው           ሀሙስ፡ነሀሴ 10/ 2010 ሲመረቅ በበዓሉ ላይ የተገኙት ክብርት / ያለም ጸጋይ፣ የኢፌዴሪ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር እንደተናገሩት በስራ ከባቢ የህጻናት ማቆያዎች እንዲዘጋጁ መደረጉ ሴቶች በስራቸው ስኬታማ እንዲሆኑና የተዋዳዳሪነት መንፈስ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

 

ክብርት ሚኒስትሯ አክለው እንደገለፁት በአዋጅ በተቀመጠው መሰረት የህፃናት ማቆያዎችን በሥራ ቦታ በማዘጋጀት ረገድ በአንዳንድ ተቋማት አበረታች ውጤት እየታየ ቢሆንም ዛሬ በኢመደኤ የተመለከትኩት ግን ለአገራችን እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡  

 

አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደገለፁት  በአዋጅ በተቀመጠው እና የኢፌዴሪ መንግስት በሰጠው ትኩረት መሰረት ተቋማት በስራ ከባቢያቸው የህፃናት ማቆያ ማዘጋጀት የሚጠበቅባቸው ከመሆኑ አኳያ ኤጀንሲው ይህን ማዕከል ለማዘጋጀት ችሏል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬተሩ አክለው እንደተናገሩት ማዕከሉ የተዘጋጀው ለሰራተኞቻችንና ለእናቶች ካለን ክብር አንጻር ሲሆን ከዚህ ጅምር ተነስተን በቀጣይም ማዕከሉን ይበልጥ ለማጠናከር አቅጣጫ ጠቋሚ ነው ብለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል የኢመደኤ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽጌረዳ ወርቁ እንደገለጹት ማዕከሉን ዕውን ለማድረግ ውጣ ውረዶች የነበሩ ቢሆንም መጨረሻ ላይ ተፈጻሚ በመሆኑ ኤጀንሲውን አመስግነው የማዕከሉ መከፈት ለ14 ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠሩ ጥምር ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

 

ከ700 መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ማቆያው ከ100 በላይ ሕፃናትን የማስተናገድ አቅም አለው ተብሏል::  https://youtu.be/YhWvZpO80yo