የዛፍ ችግኝ በመትከል ለአካባቢ ጥበቃ የበኩላችንን እንወጣለን

አዲስ አበባ ሐምሌ 14/2010 ዓ/ም፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አመራርና ሠራተኞች ሐምሌ 14/2010 ዓ/ም "የዛፍ ችግኝ በመትከል ለአካባቢ ጥበቃ የበኩላችንን እንወጣለን" በሚል መሪ ቃል የዛፍ ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ አከናውነዋል፡፡

የኢመደኤ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፤ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢመደኤ  በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ከመፈጸም ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይም ይሁን በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በንቃት እንደሚሳተፍ ገልጸዋል፡፡ ኢመደኤ በየአመቱ የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር እንደሚያካሂድ የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም አሁን ያለውን ሃገራዊ መነቃቃት እንዲሁም የክቡሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን መልዕክት መሰረት በማድረግ ኢመደኤ እንደ ተቋም ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ እንዲሁም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሰራና እየሰራም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተልኳችንን በመወጣት ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና ከምንግዜውም በላይ በሙያችን የሚጠበቅብንን ከመፈጸም ባሻገር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታም ይሁን ሌሎች ማህበራዊ ሃላፊነቶቻችንንም በአግባቡ እንወጣለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡