የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ

ሰኔ 15/2010 ዓ/ም፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መስሪያ ቤት ጉብኝት በማድረግ በቀጣይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ እና በተቋማቱ የሚሰሩ ስራዎች እና ውጤቶች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡  

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የተደረገው ውይይት ገንቢ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በኮሚኒኬሽን ሳተላይት ዙሪያ በጋራ የሚሰሩበትን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡና የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ወደፊት ሊሰሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት በጋራ ፕሮጀክቶች የሚቀረፁበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡ ኢመደኤ በማንኛውም ግዜ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ እና በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


በውይይቱም አጠቃላይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ገለፃ እና ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት እየተሰሩ ስላሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ተቋሙ ከኢመደኤ ጋር በተለይ በሳተላይት ፕሮጀክቶች፣ በሳይበር ደህንነት እና በአይ.ሲ.ቲ ደህንነት እንዲሁም የስፔስ ጉዳይ ደንቦች ላይ በጋራ መስራት የሚችሉባቸው ጉዳዮች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡


በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተደረገው ውይይት ጥሩ እንደነበርና በተቋሙ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ለማወቅ ያስቻለ መሆኑን የኢመደኤ ከፍተኛ አመራሮች የገለፁ ሲሆን በቀጣይም በሳይበር ደህንነት፣ በስፔስ ደህንነት እና በኮሚኒኬሽን ደህንነት ላይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የተለያዩ ስራዎችን መስራት የሚያስችል ሳተላይት እንዲኖረን ለማድረግ በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል፡፡


በመጨረሻም ሁለቱ ተቋማት ያደረጉት ውይይት የተቋማቶቹን ስራ ተገንዝቦ በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚፈጥር መሆኑንና በቀጣይም በጋራ በመሆን ጠንካራ የሆነ የኮሚኒኬሽን ሳተላይት መገንባት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ተናግረዋል፡፡