ኢመደኤ የተሰጠውን ሃገራዊ ግዴታ ለመወጣት የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ እየሰራ ነው

ዕሮብ ሰኔ 13/2010 ዓ.ም፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዲሱ አመራር ኤጀንሲው የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እየተወሰዱ ባሉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ከኤጀንሲው ሰራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ወቅት እንደገለጹት ኤጀንሲው ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር ተደምሮ በመስራት ረገድ ቀደም ሲል የነበሩ ውስንነቶችን በመፍታት አብሮ መስራት መጀመሩንና በዚህ ረገድ በውጭም ሆነ በውስጥ የነበረውን የኮሙኒኬሽን ክፍተት ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡  

ተቋሙን አስመልክቶ በተቋሙ ውስጥ እና በውጭ የነበሩና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን፣ በፕሮጀክት አሰተዳደር በኩል የነበሩ ክፍተቶችን እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ከአባላት እና ከባለድርሻ አካላት የተገኘውን ግብረ-መልስ መሰረት በማድረግ ማሻሻዎች መደረጋቸውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡

ኢመደኤ በአዋጅ የተሰጠው ግልጽ ተልዕኮ እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን በተመለከተ ከሌሎች ተቋማት ጋር በሚገባ ተግባብቶ በምን መልኩም በመደመር ስሜት እንደሚሰራ በተግባቦት ላይ የተመሰረተ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ችግር የኮሙዩኒኬሽን ችግር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በውስጥ በኩል አባላት የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ፤ በውጭ በኩልም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚያነሷቸው ቅሬታዎች እንዳሉ፤ ሲደመርም ሕዝቡ በተቋሙ ላይ ያለው አተያይ እኔን የሚጠብቅ ተቋም ነው በሚል ስሜት ሳይሆን የመጠራጠር ሁኔታዎች እንዳሉ የገለጹ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የችግሮቹን ምንጮች በመለየት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሌላም በኩል በፕሮጀክት አስተዳደር ስርአት ላይ ችግር እንዳለ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው በሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ በጊዜው አጠናቆ በማስረከብ በኩል ችግሮች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹ ሲሆን፤ ይህንን ከመፍታት አንጻር ኤጀንሲውን የማይመለከቱ ፕሮጀክቶችን ባለቤት በመፍጠር ለሚመለከተው ማሸጋገር፤ በሌላም በኩል የኤጀንሲው የሆኑ ፕሮጀክቶችን ደግሞ በሚገባ በመያዝ በተቀመጠላቸው ጊዜና ወጪ ለመፈጸም የሚስችል አደረጃጀት የተፈጠረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የማስተካከያ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

     

በአጠቃላይ አዲሱ የኤጀንሲው አመራር ሥራውን በይፋ በጀመረ ማግስት ከሠራተኞች ጋር ያደረገውን ግልጽ ውይይት ተከትሎ አጠቃላይ በተቋም ውስጥም ይሁን ከተቋሙ ውጪ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት፣ መፍትሄ ለመስጠትና የተቋሙን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር የሚያስችል የመፍትሄ እርምጃ እንደተወሰደና በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡