ኢመደኤ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ ውይይት አደረጉ

ዕሮብ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም፡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዑባህ መሃመድ የተመራ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት መርህን መሰረት ባደረገ መልኩ በመደጋገፍ ተደምሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይት ነው ያደረጉት፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ልዑካን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ውይይቱን የከፈቱ ሲሆን፤ ሁለቱ ተቋማት ሀገራዊ ራዕይን መሰረት ባደረገ መልኩ በመደመር ሊሰሯቸው የሚገቡ በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ "ስንደመር የተሻለ ውጤት እናመጣለን፤ ይህ ደግሞ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው" ሲሉም በቀጣይነት ሁለቱ ተቋማት በመተባበርና በመደጋገፍ ለመስራት የሚያስችላቸው መንገድ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ወ/ሮ ዑባህ መሃመድ በበኩላቸው ሁለቱም ተቋማት የሚሰሩት ሥራ ዓላማን መሰረት አድርጎ ሀገራዊ ግብን ለማሳካት መሆን እንዳለበት የተናገሩ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ቢያንስ እያንዳንዳችን ምን እየሰራን እንደሆነ ተናበን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመቀጠልም በኢመደኤ ተልዕኮ ዙሪያ የተዘጋጀውን ገለጻ የኢመደኤ ም/ዋና ዳይሬክተር ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡ ኢንፎርሜሽን ቁልፍ ሃብት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደህንነቱን በማረጋገጥ ለሀገሪቱ የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ መርሃ-ግብሮች ማስፈጸሚያ እንዲሆን ማስቻል በማስፈለጉ ኢመደኤ በአዋጅ እንደተቋቋመ ገልጸዋል፡፡ የኢመደኤ ስትራቴጂክ መሰረቶች ምን እንደሆኑ፣ የተቋሙ የለውጥ መሳሪያዎች፣ ቁልፍ የመወዳደሪያ አቅሞች ምን እንደሆኑ ወ.ዘ.ተ በገለጻው ቀርቧል፡፡ በቀጣይነትም ሁለቱ ተቋማት በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉ ሁኔታዎች/ሀገራዊ ፍላጎቶች የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ የሳተላይት ባለቤትነትን በማረጋገጥ ዙሪያ፤ በብሔራዊ የማንነት መለያ (National ID) ዙሪያ፤ በቁልፍ የህዝብ መሰረተ-ልማቶች (Public Key Infrastructures- PKI) ዝርጋታና ደህንነት ዙሪያ፤ በብሔራዊ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርም-ደራሽ ዙሪያ … ወ.ዘ.ተ በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚቻል ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በገለጻቸው አቅርበዋል፡፡

የቀረበውን ገለጻ ተከትሎ በሁለቱ ተቋማት መካከል በትብብርና በመደመር ስሜት ለመስራት የማያስችሉ እንቅፋቶች ምን እንደነበሩ እንዲሁም በቀጣይነት በምን መልኩ ችግሮቹን መፍታት እንደሚቻል የተለያዩ አስተያየቶችና ማብራሪያዎች ቀርበዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በሁለቱ ተቋማት መካከል ከመተባበር ይልቅ ተነጣጥሎ የመስራት እና ተደምሮ ለአንድ ሀገር እንደሚሰራ ግንዛቤ አለመዳበሩ እንደ ቁልፍ ችግር የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንን ከመፍታት አንጻር በሁለቱም ተቋማት አዲስ የተመደቡ ከፍተኛ አመራሮች በፍጥነት ተነጋግረው ያለውን ችግር ለመፍታትና ተቀራርቦ ለመስራት ያሳዩት ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ ጅምር እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱ ተቋማት የጀመሩትን ውይይትና ግንኙነት ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትንም ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም ሁለቱም ተቋማት በአዋጅ የተሰጣቸውን ተግባርና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ መተባባርና መደጋገፍ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡