የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢመደኤ ጉብኝት አደረጉ

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጂ.አይ.ኤስ ዘርፍ የድህረ-ምረቃ እና ፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎች እንዲሁም ሠራተኞች ሐሙስ ግንቦት 2/2010 ዓ.ም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የብሔራዊ ጂኦስፓሻል መረጃ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከጎበኟቸው የኤጀንሲው የሥራ ክፍሎች መካከል ጂኦስፓሻል ኢንጂነሪንግ፣ ብሔራዊ የስፓሻል ዳታ መሠረተ-ልማት፣ ሰርቬይንግ እና ካርታ ሥራ ተቋም፣ ካርቶግራፊ ማዕከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በኢመደኤ የብሔራዊ ጂኦስፓሻል መረጃ ዘርፍ ጊዜያዊ አስተባባሪ ሌ/ኮሎኔል በላቸው ፀሃይ በኢመደኤ ስለሚከናወኑ የጂኦስፓሻል መረጃ ስራዎች እና ሀገራዊ ፋይዳቸውን በተመለከተ ለተማሪዎቹ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፤ ኢመደኤ የሀገሪቱን የስፓሻል ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግና ደህንነቱንም በመጠበቅ ብሔራዊ ጥቅሞችን የማረጋገጥ ስራ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በጎበኟቸው ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውንና ኢመደኤ በሀገሪቱ የጂኦስፓሻል ዘርፍ ላይ እያበረከተ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ተማሪዎቹ፤ በቀጣይ በጂኦስፓሻል ዘርፍ ከኤጀንሲው ጋር ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል; ኢመደኤ በሚያዘጋጀው የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ - ዩኒቨርሲቲ ፎረም ላይ ለመሳተፍና አባል ለመሆንም ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡