አዲሱ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትሎቻቸው ከኤጀንሲው ሰራተኞች ጋር ትውውቅና ውይይት አድርገዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ  እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ሥራቸውን በይፋ ከጀመሩበት ከሚያዚያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የተቋሙን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም መላውን የኤጀንሲውን ማህበረሰብ አባል በመሰብሰብ የትውውቅ መድረክ እና በወቅታዊና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ከሚያዚያ 25 እስከ 26/2010 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከመላው የኤጀንሲው አባላት ጋር በተደረገ ውይይት የተቋሙን ራዕይና ተልዕኮ እውን በማድረግ ሂደት የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች እንዲሁም እንደ ተቋም ባሉ ጥንካሬዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡ አዲሱ አመራርም ከመላው ሠራተኛ ጋር በመቀናጀት የሚነሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ስትራቴጂክ በሆነ መልኩ እንደሚፈታ መልእክት አስተላልፏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢመደኤ እንደ ተቋም ባለፉት 11 አመታት ለሀገራዊ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በርካታ አስተዋጽኦዎችን ያበረከተ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን እያገለገሉ ያሉት ክቡር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በተቋሙ ታሪክ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸውና ተቋሙን በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃ የመሩ እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ዋና ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መልእክት ኢመደኤ ለሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተና ወደፊትም በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ያሰመሩበት ሲሆን ለዚሁ ስኬትም ተቋሙ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የመስራቱ ሂደቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻም መላው የኤጀንሲው ሰራተኞች እና አመራሮች ከመንግስት እና ህዝብ የተሰጣቸውን  ተልዕኮ በቁርጠኝነትና ትጋት እንደሚወጡ እጅ ለእጅ በመያያዝ ቃል ገብተዋል፡፡