በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች ለሳይበር ጥቃት መጋለጣቸው ተነገረ

 

በኮምፒውተር ማዕከላዊ ፕሮሰሲንግ ዩኒት (CPU) ላይ በተፈጠረ የደህንነት ክፍተት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች ለሳይበር ጥቃት መጋለጣቸውን የዘርፉ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተለይም ግዙፉ የቺፕ (chip/microchip) አምራች በሆነው ኢንቴል (Intel) ምርቶች ላይ በተፈጠረ የደህንነት ክፍተት ሳቢያ በርካታ ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፖችና ስማርት ስልኮች ለሳይበር ጥቃት መጋለጣቸው ተነግሯል፡፡ ከኢንቴል በተጨማሪ የኤ.አር.ኤም (ARM) እና ኤ.ኤም.ዲ (AMD) ምርቶችም ለሳይበር ጥቃት መጋለጣቸው ተነግሯል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም ዓይነት የመረጃ ጥቃት ጥቆማ አለመምጣቱም የተገለጸ ሲሆን፤ የአሜሪካው የሀገር ውስጥ ደህንነት ዲፓርትመንት (Department of Homeland Security) ባስተላለፈው መልዕክት ለተፈጠረው የደህንነት ክፍተት ችግር ዋነኛው መፍትሄ የኮምፒውተሮችን ማዕከላዊ ፕሮሰሲንግ ዩኒት (CPU) መቀየር እንደሆነ አሳውቋል፡፡

በችፑ ላይ የተፈጠረው ክፍተት የመረጃ ጠላፊዎች በኮምፒውተር ሚሞሪ ውስጥ የተከማቹ እና የተመዘገቡ መረጃዎችን እንዲያነቡ ከማስቻሉ በተጨማሪ የይለፍ ቃል እና ሌሎች መረጃዎችን ለመበርበር ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ችግሩን ተትሎም ቀዳሚ የኦፕሬቲንግ ሲስተም አምራች የሆኑት ማይክሮሶፍት፣ አፕል እና ሊነክስ ለክፍተቱ መሙያ/መጠገኛ (Patch) የሚያቀርቡበትን ቀናትን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም ማይክሮሶፍት ለዊንዶው 10 ምርቶቹ ከፈረንጆቹ ጥር 4/2018 ጀምሮ ያቀረበ ሲሆን  በሂደትም ለዊንዶው 7 እና 8 ምርቶችም እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡  

በአለም አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ የኮምፒውተሮች ተጠቃሚ ማለትም የዴስክቶፕም ሆነ የላፕቶፕ ተጠቃሚዎች 1.5 ቢሊዮን ሲሆን ከዚህ መካከል 90 ከመቶ የሚሆኑት የኢንቴል ቺፕ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡

http://www.bbc.com/news/technology-42562303