በሩስያ አማካኝነት ወደ ህዋ የተላከችው የአንጎላ የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ግንኙነት መቋረጡ እየተነገረ ነው

 

በሩሲያው የህዋ ምርምር ተቋም ሮስኮስሞስ (Roscosmos) አማካኝነት ወደ ህዋ የተላከችውና አንጎሳት አንድ (Angosat-1) የሚል መጠሪያ የተሰጣት የመጀመሪያዋ የአንጎላ ሳተላይት ግንኙነት መቋረጡ ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ህዳር ወር ሩስያ ለአየር ጸባይ ትንበያ በሚል የላከቻት ሳተላይት ግንኙነት ከተቋረጠባት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በሩሲያ የተሰራ የሳተላይት ስህተት መሆኑ እየተነገ ነው፡፡ በፈረንጆቹ ታህሳስ 27/2017 የሩሲያው የህዋ ምርምር ተቋም ሮስኮስሞስ የአንጎሳት አንድን ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ማምጠቁን እና የምድር ምህዋር ላይ መድረሷን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

የአንጎሳት አንድ ፕሮጀክት በአንጎላ እና በሩሲያ መካከል እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2009 የፕሮጀክት ስምምነት የተደረሰበት ሲሆን በስምምነቱ መሰረትም ከሳተላይት መስራት እስከ ማምጠቅ እንዲሁም በሃገሪቱ ዋና ከተማ ሉዋንዳ መሰረተ-ልማቶችን ግንባታን ያካተተ ነበር፡፡ አንጎላም ለፕሮጀክቱ እስከ 280 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከሩሲያው የብሄራዊ ባንክ ባገኘችው ብድር ስራው መከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

ሳተላይቱ በሃገሪቱ ያለውን የሳተላይት ተግባቦቶችን፣ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዲሁም የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን አገልግሎትን ከፍ ለማድረግ የ15 ዓመት ተልዕኮ ይዛ ወደ ህዋ የተላከች ሳተላይት ናት፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይዘውት በወጡት መረጃ መሰረት የሳተላይቷ ግንኙነት መቋረጡን እየጠቀሱ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት የዘርፉ ጠበብቶች ከፍተኛ የሚባሉ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የችግሩ ምክንያት ምን እንደሆነም እስካሁን አለመታወቁም ተጠቅሷል፡፡

https://news.cgtn.com/news/77516a4e34637a6333566d54/share_p.html