በሞባይል የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት አይነተኛ ሚና አለው ተባለ

በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ማንሰራራት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ተባለ፡፡ ሰሞኑን GSMA በጥናት አረጋገጥኩት ባለው መሰረት ባለፉት ዓመታት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው እያደገ የመጣው የሞባይል አገልግሎት በአህጉሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ (GDP) ላይ የ150 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ6.7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል ብሏል፡፡ ይህ ዕድገት በፈረንጆቹ 2020 ወደ 210 ቢሊዮን እንደሚደርስ ያሳወቀው ሪፖርቱ ቴክኖሎጂው የጨለማ ተምሳሌት ተደርጎ ለሚታየው የአፍሪካ አህጉር ትልቅ የኢኮኖሚ ዋልታ እየሆነ መምጣቱን አውስቷል፡፡ አይቲ ኒውስ አፍሪካ (itnewsafrica.com) እንደዘገበው የሞባይል መረጃ ለመቀባበልና የንግድ ሥራን በማከናወን በኩል እየሰጠ ያለው ጥቅም በኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ዕሴት ማስገኘቱ ታምኖበታል፡፡ በአፍሪካ የቴሌኮም መሰረተ-ልማት አለመሟላትና የኃይል መቆራረጥን የመሳሰሉ ችግሮች በአገልግሎቱ ላይ ሳንካ ቢፈጥርም በዚህ ውስጥም ሆኖ ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጫወተው ሚና ግን የተሻለ ነው ተብሎለታል፡፡ ከዚህ የተነሳ በአህጉሪቱ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በኢንቨስትመንት ለሚሰማራ አካል አዋጭነቱ የጎላ መሆኑን ዘገባው ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

በአፍሪካ ከጠቅላላው የህዝብ ብዛት 46 ከመቶ ወይም 560 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ የሞባይል ተጠቃሚዎች መኖራቸውንና ይህም ገና ሊሰራበት እንደሚገባ ሪፖርቱ አውስቷል፡፡

http://www.itnewsafrica.com/2017/11/leveraging-innovative-solutions-for-bridging-the-digital-divide/