ከማህበራዊ ሚዲያ ተረቱን ወይስ ትምህርቱን

ከማህበራዊ ሚዲያ ተረቱን ወይስ ትምህርቱን

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማህበራዊ ድረ-ገጽ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ብሎም የጥላቻና የነቀፋ መልዕክቶች ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ እየተፈታተኑ መምጣታቸው ይታወቃል። በሁሉም ዘርፍ በልጽገናል የሚሉትን አገራት ጨምሮ ገና በማደግ ላይ ያሉትም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ሰነባብተዋል። ችግሩ አሁንም ድረስ ሁነኛ መፍትሄ ሊገኝለት ባለመቻሉ ሁሉም አገራት ስጋታቸው ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል። ይህን ተከትሎም በዘርፉ የሚገኙ ተመራማሪዎች ችግሩን ለመፍታት ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ በቅርቡ ደግሞ በተለይ በማህበራዊ ድረ-ገጽ የሚለቀቁ የተዛቡና የጥላቻ መልዕክቶችን ለይቶ የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ማግኘታቸውን በመናገር ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያም የኢንፎርሜሽንን ወሳኝነትን በመገንዘብ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን እና  በተዛባ መልኩ ወደ ህብረተሰቡ እንዳይደርስ ኢንፎርሜሽኑ የሚከማችበትንና የሚተነተንበት እንዲሁም የሚሰራጭበትን የሳይበር ምህዳር ደህንነት በተመለከተ አጽንኦት ሰጥታ በመስራት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ በተለይም አሁን የተያያዘችው የልማት ጎዳና በተዛባና በተሳሳተ መረጃ ተበርዞ እንዳይደነቃቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ ናት።

በታዋቂ ሰዎችና በባለስልጣናት እንዲሁም በድርጅቶች ስም የውሸት አካውንት ከፍተው ብዙ ተከታዮችን በማፍራት  ያልተገባ መልዕክትና ለአመጽ የሚያነሳሱ ሐሳቦችን የሚያሰራጩ ሰዎችን በተመለከተ አገሪቱ ምን እያደረገች እንደምትገኝና ችግሩን እንዴት መፍታት ይቻላል በሚለው እንዲሁም ከማህበራዊ ድረ ገጾች ጋር በተያያዘ አዲስ ዘመን ጋዜጣ (የህዳር 07 ቀን 2010 ዓ.ም ዕትም) ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ሙሉ ቆይታውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ …

 

አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ምን ያህል የኢንተርኔት እና የማህበራዊ ድረ ገጽ  ተጠቃሚዎች አሉ?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ እስካሁን በአገራችን ኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው የሚባለው ካለው የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 15 በመቶ ያህሉ ነው። ይህን በቁጥር ስናስቀምጠው 16 ሚሊዮን ይሆናል። እንዲሁም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ህዝብ ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ነው፡፡ ይህ ቁጥር በ16 አመት ውስጥ ከ10 ሺህ ወደ 16 ሚሊዮን መምጣቱ ትልቅ መሻሻል ቢሆንም ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ሲተያይ ግን ገና ይቀረናል፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ከ48 ሚሊዮን አካባቢ ህዝብ ውስጥ 43 ሚሊዮኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህም የህዝቡ 90 ከመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ከእኛ ሀገር የቴክኖሎጂው አጠቃቀም ጋር ሲነጻጸር ቁጭት ሊፈጥር ይገባል፡፡

 

አዲስ ዘመን፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ ድረ ገጾች አማካይነት በሚሰራጩ የተዛቡ መልዕክቶች በአገሪቱ ችግሮች እየተከሰቱ ነው፤ ይህ እንዴት ይገለጻል?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ ማህበራዊ ድረ ገጽ ዓለማቀፋዊ ነው። በዚህም ምክንያት  የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲሁ ዓለም አቀፋዊ ናቸው። ስለዚህም በኢትዮጵያ የሚታየው የተለየ ችግር አይደለም። ለምሳሌ ፌስ ቡክ በብዛት ይነሳል እንጂ ቲዊተር፣ዩቲዩብ እና የመሳሰሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመልካም ነገር የመዋላቸውን ያህል ለመጥፎም በመዋል ላይ ይገኛሉ። ከፍተኛ ተከታይም አላቸው። ለአብነት ፌስ ቡክን ብንወሰድ ሁለት ቢሊዮን ያህል ተጠቃሚዎች አሉት። ከእነዚህ መካከል 270 ሚሊዮን የውሸት አካውንት ናቸው። በእነዚህም ትክክለኛ ያልሆኑ መልዕክቶች ሊተላለፉ ይችላሉ።

 

አዲስ ዘመን፦ የውሸት አካውንት ሲባልስ እንዴት ነው የሚገለጸው? በእነዚህ አማካኝነት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ በራስ ስም ሳይሆን በአገር፣ በድርጅት፣ በግለሰብ፣ በእጽዋት አሊያም በእንሰሳትም ሆነ በሌላ መጠሪያ አካውንት በመክፈት መጠቀም  ሀሰተኛ ያስብለዋል። አካውንቱ በግለሰብ ስም ከሆነ የተከፈተው ግለሰቡን ማጥቆር ሊሆን ይችላል። በአገር ደረጃም ከሆነ አገርን የማጥቆር ዘመቻ ይካሄድበታል። ከዚህም አልፎ ሽብር ከመንዛት እስከ ዘር ማንኳሰስም ሊደርስ ይችላል። እንዲሁም የውሸት መረጃዎችን መልቀቅም ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ተራ ማህበራዊ ግንኙነቶችን የሚያበላሹ ነገሮችን ይለቀቅባቸዋል። እንዲህ ሲባል ዘመቻቸው ፖለቲካው ላይ ብቻ አይደለም ለማለት ነው።

ሌላኛው ግን በታወቁ ተቋማትና በታዋቂ ሰዎች ስም አማካይነት የሚከፈተው አካውንት ማስመሰል (Impersonation) የሚባለው ነው። የታዋቂውን ሰው ማንነት በመውሰድ አካውንቱን የከፈተው ሰው ለሚፈልገው ዓላማ ይጠቀምበታል። ጉዳዩን አጥብበን ስናይ ግን ይህ የማንነት ስርቆት ነው የሚባለው።

ለምሳሌ በቅርቡ ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ላይ የተደረገው የማንነት ስርቆት ነው። የእርሱን ታዋቂነት በመጠቀም አካውንት ከፍተው ወደ 100ሺ ተከታዮችን ማፍራት ችለው ነበር። የአትሌት ሃይሌን ስም ተጠቅሞ የከፈተው አካል ለቢዝነስም ነው ሊጠቀም የሚችለው። ምክንያቱም ብዙ ተከታይ አለ ማለት በርካታ ማስታወቂያ በዛ በኩል ስለሚለቀቅ የሚያገኙትም ክፍያ ይኖራል። ከዛ አልፎ ደግሞ ለፖለቲካ ፍጆታም ይጠቀሙበታል።

በማስመሰል አካውንቱን የሚከፈቱ አካላት ይዘቶችን ቀያይረው ነው መልዕክቱን የሚያስተላልፉት፤ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ሰላም እያለ ሁከት እንዳለ በማድረግ በሌላ አገር የተከናወኑትን ግርግሮች ምስል በመጫን ወይም የድሮ ፋይሎች በማምጣት ሁከት እንዳለ በማስመሰል መልዕክት ማስተላለፍ ይችላሉ።  በአገራችን አምና የተከበረውን የኢሬቻ በዓልን ብንወስድ በወቅቱ ሲነገር የነበረው አየር ሃይል ሄሊኮፕተር ተጠቅሞ የበዓሉን ታዳሚ ደበደበ ነበር የተባለው። ይህ አይነቱ አባባል በአገሪቱ ሲነገር ለአገራዊ ደህንነት አደጋ ነው።

 

አዲስ ዘመን፦ በውሸት አካውንት ተከፍቶብኛል  ብለው ወደ እናንተ መጥተው ያመለከቱ አሉ?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ በዚህ አይነት አካሄድ የተጎዳ ነገር ግን ድምጹ ያልተሰማ ብዙ ሰው አለ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች ወደ እኛ መጥተው አመልክተዋል። በእኛ በኩል መረዳት የሚገባቸውን እንረዳለን። የህግ ጉዳይ ሲሆን ደግሞ በፖሊስ አማካይነት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታዘዝ አለበት።  ጉዳያቸውን ፖሊስ የሚመለከተው ሆኖ ሳለ ነገር ግን ጨንቋቸው ወደ እኛ በቀጥታም የሚመጡ አሉ። እኛም ስናማክራቸው ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ነበር።

በሻለቃ ሃይሌ  ስም በተከፈተው የውሸት አካውንት በጣም ያልተገቡ መልዕከቶች ሲተላለፉ ነበር። ይህ ደግሞ አገራዊ ደህንነትን የሚመለከት ነው። በሚኒስትሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ስም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ነበር። ስለዚህ የሁለቱም ሰዎች ለሚመለከተው  አካል ሪፖርት ተደርጓል። ሻለቃ ሃይሌ በግሉም ሪፖርት አድርጓል። ስለዚህም መፍትሄ ተሰጥቶታል። በመሆኑም በዚህ አይነት ሁኔታ በየደረጃው መፍትሄ ይሰጣል ማለት ነው። ነገር ግን መሰጠት ያለባቸው መፍትሄዎች በህግ ማዕቀፍ ማለትም በስርዓት መሆን አለበት። ስለዚህ ለወደፊቱ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው እየተሰራ ያለው።

በጥቅሉ ያለው አማራጭ ግን በልጦ በመገኘት ከዚህ ቴክኖሎጂ ሊገኝ የሚችለውን ትሩፋት ተቋዳሽ መሆን ነው። ስለዚህ የመጠቀም አቅምን መገንባት ይጠበቅብናል። ይህ አንዱ ነው እንጂ ማህበራዊ ሚዲያን መዝጋት አማራጭ ሊሆን አይችልም። ሁለተኛው ግን ችግሮች ሲያጋጥሙ ያንን ለመፍታት ህግ ማወቅ ተገቢ ነው፤ ህግ ሲባል የዓለም አቀፍ ተቋማትን ህግ ማወቅ አለብን። ፌስ ቡክ፣ ጎግል፣ ቲዊተር የራሳቸው ስርዓት አላቸውና ነው። እነርሱ የሚፈልጉት ጤነኛ የሆነ አካሄድ እንዲኖር ነው።

በአሁን ወቅት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ጅማሬዎች እየታዩ ነው። አገራትም ሆኑ ተቋማትም አደጋውን አስተውለዋል። በእርግጥ በሂደት ቢዝነሳቸውን መዝጋት አይፈልጉም። ስለዚህ ለመልካም ነገር መዋል አለበት ብለው ስርዓት እያበጁለት ይገኛሉ። ተቋማቱም ለመተባበርም ዝግጁ ሆነዋል። 

ሌላው ቀርቶ ለምሳሌ ፌስ ቡክ ከኢትዮያ ጋርም ለመተባበር ዝግጁነቱ አለው። ይህን የሚያደርገው ለኢትዮጵያ ብሎ አይደለም። ለራሱ ቢዝነስ ሲል እንጂ። ስለዚህ አንታወቅም ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት መታወቃቸውና  ወደ ህግ የመቅረባቸው ነገር አይቀሬ ነው።  ሌላው ግን በአገራችን የሳይበር ኢንዱስትሪው ማደግ አለበት። ይህንን ስናሳድግ ልክ እንደሌሎች ያደጉ አገራት የመደራደር አቅማችን ከፍተኛ ይሆናል። ደህንነትም የሚረጋገጠው ያኔ ነው። ህግና ንቃተ ህሊና ብቻ አይፈታውም። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በአገራችን ውስጥ እንዲመጡ መስራት የግድ ይለናል። ለዚህ ደግሞ እየሰራን ነው የምንገኘው።  

 

አዲስ ዘመን፦ ያልተረጋገጠና ተዓማኒነት የሌላቸውን መረጃዎች የሚለቁት እነማን እንደሆኑ ይታወቃሉ?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች ፍላጎታቸው የተለያየ ነው። ለምሳሌ በአገር አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ እንዲሁም የቢዝነስ ፍላጎትም ያላቸው  አካላት የውሸት አካውንት ሊከፍቱ ይችላሉ። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለቂም በቀል ወይንም ያልተገባ ዝና ለማግኘትም ሲባል ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካ ሌሎችንም ቀውሶች ይፈጥራል፤ እየፈጠርም ነው ያለው።

 

አዲስ ዘመን፦ እንዲህ አይነቱን ችግር ለመከላከል መደረግ የነበረበት አሊያም ያለበት ምንድን ነው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ እንዲህ አይነቱ ችግር ሊመጣ የቻለው ፌስ ቡክ ከመጀመሪያም ሲፈጠር የተጨነቀው ስለይዘቱ ባለመሆኑ ነው። ዓላማው የነበረው የመገናኛ አውታሩን በመዘርጋት ቢዝነስ መስራት ነው። ይህ በመሆኑ የይዘት ቁጥጥር  ስርዓት አልነበረውም። ዓላማው የነበረውን ቢዝነስ ሲያካሄድ ያልተገቡና የተሳሳቱ መረጃዎችም መውጣት ጀመሩ። ነገር ግን ገና ከመጀሪያው ዲዛይን ሲደረግ ተገቢ ያልሆኑ መልዕክቶችን ማስወገድ  ወይም መቆጣጠር የሚችልበትን ስርዓት ቢዘረጋ ችግሮቹ ይቀንሱ ነበር።

ማህበራዊ ድረ ገጾችን መቆጣጠር የሚቻልበት ስርዓት ባለመዘርጋቱ በአሁኑ ወቅት ለአሸባሪዎች፣ ለወንጀለኞች፣ ለአጭበርባሪዎችና እነዚህን መሰል ተግባር ለሚሰሩ አካላት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። እንዲህ ሲባል ግን ለተሻለ ተግባርም ጥቅም ላይ መዋሉ መዘንጋት የለበትም።

 

አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ ማህበራዊ ድረ ገጾች የሚጠቀሱትን ስጋቶች መቆጣጠር ካልቻሉ አሁን ምንድን ነው መደረግ ያለበት?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ ማህበራዊ ድረ ገጾች የግል ቢዚነስ ተቋም እንደመሆናቸው መንግስት አያስተዳድራቸውም። ራሳቻውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትንና የሚቆጣጠሩበትን ስርዓት መፍጠር አለባቸው ተብሎ ነው የሚታሰበው። ለአብነት ፌስ ቡክ ችግሩን ለማቃለል እርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል። በተለይ የጥላቻ ንግግር የሚሏቸው፣ ሽብርን የሚያነሳሱ መልዕክቶችና መጥፎ ይዘቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ስርዓት ለመዘርጋት እየሞከረ ነው።

 

አዲስ ዘመን፦ ፌስ ቡክ ለመዘርጋት እየሞከረ ያለውን ስርዓት አገራት እንዴት ነው መጠቀም ያለባቸው ?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ ፌስ ቡክ የሪፖርት አደራረግ ስርዓትን ዘርግቷል። የውሸት አካውንት በሚፈጠርበት ጊዜ ግለሰቦች ሪፖርት የሚያደርጉበት ስርዓት አለ። የሚሞላ ቅጽ ልንለው እንችላለን። ይሁንና አሁን በተዘረጋው ስርዓት ሁሉም አገራትና ሁሉም ሰው እኩል ይጠቀሙበታል ማለት አይቻልም። በዋናነት አሁን በተዘረጋው ስርዓት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት ያደጉ አገሮች ናቸው። በተለይ በዋናነት ለአሜሪካና ለምዕራብያኑ አገሮች አሁን የተዘረጋው ስርዓት ምቹ ሊሆን ይችላል። 

ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ ሪፖርት በሚደረግበት ጊዜ የውሸት አካውንት ለመሆኑ ለማረጋገጥ ከሚጠየቁት አንዱ የግለሰቡ መታወቂያ  ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መታወቂያ  ሪፖርት ቢደረግበት ተቀባይነት አለው ወይ የሚለውን ስናስተውል ይህ በራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ወጥ የሆነ የመታወቂያ አሰራር ስርዓት የለም። ምናልባት ፓስፖርት በመጠቀም ሪፖርት ማድረግ ይቻል ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የሚታዋቁ ሰዎች ከሆኑ በቀላሉ ለማረጋገጥም አይከብድም። ይህ አካሄድ ግን ለጥቂቶች ካልሆነ በስተቀር ለብዙሃኑ የሚሰራ አይደለም። አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ያደጉ አገሮች ግን ዜጎቻቸው ወጥ የሆነ መታወቂያ አላቸው። ስለዚህም ይህን ሪፖርት የማድረጊያ ስርዓትን በመጠቀም የውሸት አካውንቶችን ማዘጋት ይችላል። በዚህም የተሳሳቱ መልዕክቶችን በማስተካከል ተጽዕኖ መፍጠር ይቻላል።

በዚህ መልኩ አገራትም ያላቸው ቦታ የተለያየ ነው ማለት ይቀላል፤ ምዕራባውያን የተሻለ የማስፈፀም አቅም አላቸው። ምክንያቱም ሪፖርት አድርገው እንዲዘጋ የማድረግ አቅማቸው ሃያል ነው። ለምሳሌ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች ሪፖርት አርገው የተሰጣቸው ምላሽ ለአንዳንዱ አገራት ዜሮ በመቶ ነው። ለምሳሌ  ለደቡብ ሱዳን ፌስ ቡክ ምንም ምላሽ አልሰጣትም። ኬንያም እንዲሁ ጠይቃ የተሰጣት ምላሽ እዚህ ግባ የማይባል ነው። ለአደጉ አገሮች ሲሆን ግን ለአንዳንዶቹ 70 በመቶ ለሌሎቹ ደግሞ 80 በመቶ ያህል ምላሽ ይሰጣቸዋል፤ እስከ 90 በመቶ ድረስም ምላሽ ያገኛሉ። ይህ በፌስ ቡክ በጎ ምላሽ ላይ የተመሰረተ እርምጃ የመውሰድ ሂደት ነው።

 

አዲስ ዘመን፦ ታዳጊ የሚባሉ አገራት በተለይም አፍሪካውያን አመልክተውም ተገቢ ምላሽ አያገኙምና መፍትሄው ምንድን ነው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ የአፍሪካ አገራት ከማንም በላይ ቀውሱ እየተፈጠረባቸው ያሉ እንደመሆናቸው ትብብር ያስፈልጋቸዋል። ሲተባበሩ የጋራ ድምጽ ይኖራቸዋል፤ ያኔ ደግሞ ይሰማሉ። በእኛ በኩል የተጀመረ ስራ አለ። ነገር ግን በቂ አይደለም። የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ማሳተፍ አለበት። እንዲያም ሆኖ ግን የችግሩን ጥልቀት በመረዳታችን ስራ ጀምረናል። ሁሉም ጉዳዮች ግን እኛን ብቻ የሚመለከቱ ባለመሆናቸው ባለድርሻ አካላቱን ማንቀሳቀስ ያስፈልገናል።

ሌላው መፍትሄ ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅምም ያስፈልጋል። ከመስራቾቹ ጋር የመደራደር አቅም ይኑረን እላለሁ።  እንደ ቻይና እንዝጋው ማለት አያስፈልግም። እንዲያውም ግልጽ እናድርገው ባይ ነኝ። ግን ከቻይና መማር ያለብን ነገር እንዳለ ሊዘነጋ አይገባም። ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ባለሀብቶች ሊሆኑ ይችላሉ ሌሎቸንም የፈጠራ ባለቤት በማሳደግ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሚና ሊጫወት የሚችል ቴክኖሎጂ መስፋፋት አለበት። በራሳችን ቋንቋና በራሳችን ባህል ገበያው ማደግ አለበት።

 

አዲስ ዘመን፦ ይህንን ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ሃላፊነት ያለባቸው ተቋማት እነማን ናቸው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ ጉዳዩን ለመከላከል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚተላለፈው መልዕክት ይዘት እነርሱም ብዙ ናቸው። ለምሳሌ አንዳንዱ የወንጀል ጉዳይ  በመሆኑ የሚመለከተው ፖሊስን ነው። ሳይበርን በሚመለከት የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ወጥቷል። ደንብና መመሪያን ተከትሎ የሚተገበር ነው የሚሆነው።

ሌላው ደግሞ ከአገር ደህንነት አኳያ ሲታይ ደግሞ ኢንፎርሜሽን ጦርነት በሚሆንበት ጊዜ የሚሰሩ አካላት አሉ፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች ባለድርሻዎች ያሉ ሲሆን፤ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሎኮምን መጥቀስ ይቻላል። ተቋሙ የራሱ ስርዓት አለውና በእርሱም የሚፈቱ ጉዳዮች ይኖራሉ። በዋናነት ግን ግለሰቡና ተጠቃሚው የሚፈቷቸው ደግሞ አሉ።

 

አዲስ ዘመን፦ ግለሰቡ መፍታት የሚችለው እንዴት ነው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ በመጀመሪያ ደረጃ ግለሰብ አካውንት በሚከፍትበት ጊዜ በራሱ የተረጋገጠ መሆን አለበት። መስራቾቹ የሚያረጋግጡበት መንገድ አላቸውና በዚህ መንገድ የተረጋገጠ አካውንት ሊኖረው ይገባል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አካውንት የሌለውም በስም ማጥፋቱ ጉዳይ ተጠቂ መሆኑ ነው። እንዲያውም የሚመረጠው ተጠቃሚ መሆን ነው። ይህም የሚጠቅመው የመደመጥ አቅም ስለሚኖር ያንን በመጠቀም ለችግሩ አንድ መፈትሄ ማበጀት ያስችላልና ነው። የተረጋገጠ አካውንት ሲኖር ደግሞ ግለሰቡ ሲያመለክት በቀላሉ ማመሳከር ይችላሉ።

ሁለተኛው ደግሞ ችግሩ በሚከሰትበት ጊዜ ፈጥኖ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት የማድረግ ጉዳይም መኖር አለበት። ለሚመለከተው በተለይ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ፤ ወይም ደግሞ ለራሱ ለማህበራዊ ድረ ገጽ ተቋማቱ ሪፖርት ማድረግ ይችላል። በተለይ በአገራችንም ደረጃ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሩ ያጋጠማቸው ሰዎች ታዋቂ ከሆኑ የውሸት መሆን አለመሆኑን ለመለየት በጣም ይቀላልና ምቹ ነው፤ ነገር ግን ይህ እምብዛም የለም። የሚተላለፈው መልዕክት አገራዊ ደህንነትን የተመለከተ ከሆነ ደግሞ ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሪፖርት ማድረግ ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ ለኤጀንሲው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ላለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ሃይል (ኢትዮ ሰርት) ሪፖርት ማድረግ ይቻላል። በዚህ መልኩ ከተቋማት ጋር በመተሳሰር ነው።

ሶስተኛው ደግሞ በስማቸው የውሸት አካውንት የተከፈተባቸው ሰዎች የእነርሱ አካውንት የቱ እንደሆነ ለተከታዮቻቸው በየጊዜው መረጃ መስጠትና በስማቸው የተከፈተው ደግሞ እንደማይወክላቸው ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ሌላ ግን ብሄርን ከብሄር፣ ዘርን ከዘር የሚያጣላ እና ሽብር የሚነዛ አይነት መልዕክቶችን ለመከላከል ንቃተ ህሊናን ማሳደግ ይገባል። ቴክኖሎጂው አዲስ እንደመሆኑ አንድ ህጻን ልጅ ከተወለደ በኋላ ቆሞ ለመራመድ ሂደትን እንደሚጠይቅ ሁሉ እየተገነዘቡ ለመሄድ ልምምድ ቀዳሚው ነገር ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ መውደቅና መነሳት እንደሚኖር መረዳቱ መልካም ይሆናል። መውደቅ መነሳቱን ካለፈነው በኋላ ለመልካም ነገር የመጠቀም አቅማችን እያደገ ይሄዳል። በመዝጋት የሚመጣ መፍትሄ የለም። በእርግጥ አሁን እየታያ ያለው ክስተት አዲስ ነው። ይህን ክስተት ደግሞ መሸሽ የለብንም። እንዲሁ በምንጠቀምበት ጊዜ መውደቅ መነሳት እንዳለብንም መዘንጋት የለብንም። እንዲያም ሆኖ ፈጣን የሆነ የመማር አቅምን ማዳበር ይጠበቅብናል።

 

አዲስ ዘመን፦ መንግስት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ምንድን ነው ማድረግ ያለበት? 

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ የመጀመሪያው ህግ ማውጣት ነበር፤ የወጣ ህግ አለ። ይሁን እንጂ ኢንተርኔት በዋናነት በአሜሪካ ስለተፈጠረ በእነርሱ ቁጥጥር ስር ያለ ስርዓት ነው። እዚያም ቢሆን   ጎግል፣ ቲዊተር፣ ፌስ ቡክ እና ብዙዎቹ ኩባንያዎች በግለሰቦች የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህም እነዚህ አካላት እራሳቸውን በራሳቸው ነው እንጂ የሚቆጣጠሩት መንግስት አይደለም።

እንዲያውም በዓለም ደረጃ ኢንተርኔት ከአሜሪካ ቁጥጥር ስር መውጣት አለበት የሚል የተለያዩ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ናቸው። በዛው ልክም ብዙ መፍትሄዎች እየተቀመጡ ይገኛሉ። በጥቅሉ ግን ከቁጥጥራችን ውጪ ነው ብለን መቀበል አለብን፤ ይህ የመጣው ለእኛ ብቻ እንዳልሆነ ከግምት ውስጥ በማስገባት ማለት ነው። ምክንያቱም ለእኛ ብቻ አይደለም ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነው፤ ለሁሉም ዓለም ነው። እንዲያውም ለአሜሪካን መንግስት ራሱ ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኗል። ከሌላው አንጻር ሲታይ ግን ለአሜሪካ መንግስትም ሆነ ህዝብ የተሻለ ግንዛቤ ስላላቸው በቀላሉ ጉዳት ላያደርስባቸው ይችላል።

ስለዚህ ማድረግ ያለብን የምንከተለው ህግ አለ። ለምሳሌ የኢንተርኔት ማስፋፋትና መቆጣጠር የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሃላፊነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከሳይበር ደህንነት አንጻር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሃላፊነት አለበት።  ከወንጀል መከላከል አንፃር ደግሞ ፖሊስ አለ። ብዙን ጊዜ የተቋማትን ሚና ካለመለየትም የሚመጣ ውዥንብር አለ። በዚህ አይነት መልኩ ሚናን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግስት የሚመለከታቸውን አካላት አቋቁሞ እያንሳቀሰ ነው። እነዚህ ተቋማት ሚናቸውን በሚፈፅሙበት ጊዜ የማስፈጸም አቅም ያስፈልጋቸዋል።

ለምሳሌ ህጉ ከወጣ በኋላ ህጉን ለማስፈፀም ፖሊስ መሰል ወንጀሎችን የመመርመር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተባብሮ መስራትም ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂው ከፍ ያለ እንደመሆኑ ይህንኑ ለመመርመር የሚያስችለውን እውቀት ማጎልበት ያስፈልገዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲም ቢሆን እንዲሁ ነው፤ አቅሙን ማጎልበት ይጠበቅበታል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት አቅም ስለሚያስፈልጋቸው ያንን  መገንባት አለባቸው።

 

አዲስ ዘመን፦ አሁን እየታዩ ላሉ ችግሮችስ እርምጃ የሚወሰደው እንዴት ነው? 

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ አሁን ላሉ እንቅስቃሴዎች የሚወሰዱ እርምጃዎች አሉ። የችግሩ ሰለባ የሆነ ሰው በምሬት የሚናገረው በአስቸኳይ መዘጋት አለበት የሚለውን ነው። ወዲያውኑ የሚታየው መፍትሄ ይህ በመሆኑ መንግስት ያቋርጠው ማለትን ይመርጣል። ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ተዘግቶ ነበር። በተወሰነ መልኩ በመዘጋቱ እፎይታ ታይቶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ መፍትሄ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። በእርግጥ በልዩ ሁኔታ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደተደረገው ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም። ምክንያት ቢባል የሰዎችን ሃሳብ የመግለጽና የመናገር መብት የሚጋፋ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን መዘጋት የለበትም የሚባለው ኢኮኖሚያዊም ምክንያት ስላለው ጭምር በመሆኑ ነው።

ኢንተርኔቱን አሊያም ማህበራዊ ድረ ገጽን ማቋረጥ ማለት ቢዝነስንና እድገትን እንደ መገደብ ይቆጠራል። በተጨማሪም ማህበራዊ መስተጋብርንም እንደመገደብ ይቆጠራል። እውቀትን የሚገበያዩበት አንዱ መንገድም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ስለዚህ እውቀትን ገድቦ፥ ማህበራዊ መስተጋብርን ጠርንፎ፥ ኢኮኖሚውንም አቀዛቅዞ የሚመጣ እድገት አይኖርም። ስልጣኔም  ሊኖር አይችልም። ስለዚህ መገደብ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ሲባል ግን በጭራሽ መታሰብ የለበትም ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ከአገር ደህንነት ጋር ተያይዞ ከሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት እንደተደረገው ለተወሰነ ጊዜ በልዩ ሁኔታ ሊቋረጥ ይችላል።

ሌላው መሆን ያለበት ነገር ቁጥጥር ማድረግ ነው። ለመቆጣጠር ደግሞ በዘርፉ ሚና ያላቸው ሃይሎች የቁጥጥር ስርዓትን መዘርጋት አለባቸው። እንዴት ነው ቁጥጥር የሚደረገው ሲባል ቀደም ሲል የተጠቀሱት ባለድርሻዎች ተቀናጅተው የሚቆጣጠሩበት ስርዓት ሊኖራቸው ይገባል። ህግ መውጣት ብቻ ሳይሆን የቁጥጥር ስርዓቱም ሊኖር ይገባል።

 

አዲስ ዘመን፦ ቁጥጥር ሲባል በምን አይነት መንገድ ነው የሚካሄደው?

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ ቁጥጥር ሲባል አስቀድሜ እንደገለጽኩት መገደብ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ጠቃሚ ያልሆኑትን ማንንም የማያንጹትን የጥላቻ ንግግሮችን ከፌስ ቡክም፥ ከቲዊተርም ሆነ ከሌሎችም ጋር ተነጋግሮ ማስወገድ ነው። የውሸት አካውንትንም በዚህ መልኩ ማድረግ ነው። ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃም አይፈለግም። ስለዚህም የዓለም አቀፍን ህግ በመከተል ያንን ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ታድያ በቴክኒኩም በኩል አቅም መገንባት ግድ ይላል።

ከዚህ አንጻር እንግዲህ ተፈጠሩ የተባሉት የተወሰኑ የውሸት አካውንቶች ለአገራዊ ደህንነት አደጋ በመሆናቸው ምክንያት በፌስ ቡክ ገጽ ላይ በአሁኑ ወቅት የሉም፤ የዓለም አቀፍ አሰራርን በመከተል ተወግደዋል ማለት ነው።እንዲህ ሲባል ግን ግለሰቦችም ወደ ፌስ ቡክ ሪፖርት አድርገው ማስቆም ይችላሉ። በአሁኑ ሰዓት ግን በኢንሳ እና በሚመለከተው አካል እንዲወገዱ ተደርጓል። ወደ ዋናው መስራች አካል በተደረገው ሪፖርት መሰረት ማለት ነው። ይህ የሆነው የውሸት አካውንቶች አገራዊ ደህንነትን የሚነኩ በመሆናቸው ነው።

በጣም በርካታ የውሸት አካውንቶች ተፈጥረው በማተረማመስ ላይ እንዳሉ ግን ልብ ይሏል። ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ግለሰቦች ለማዘጋት ሲጠይቁ መጀመሪያ የሚጠየቁት መታወቂያ ነው። ያንን ለማድረግ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ወጥ የሆነ መታወቂያ የለም። ቁጥጥር ማድረግ አለብን ያልኩት ለዚህም አይነት ጉዳይ ምላሽ መስጠት አለበት የሚቆጣጠረው አካል።

 

አዲስ ዘመን፦ ስለሰጡን ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን !

ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን (ዶ/ር)፦ እኔም አመሰግናለሁ !