የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ፎረም ተካሄደ

አምስት ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ እስከ 8 የሚደርሱ ተቋማትን በውስጡ የያዘው የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ፎረም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስተናጋጅነት ለ7ኛ ጊዜ ተካሄደ፡፡ ፎረሙ ከጥቅምት 20 እስከ 21/2010 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በመጀመሪያው ዕለት "የጂኦስፓሻል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ትግበራ በኢትዮጵያ"  የሚል የፕሮጀክት ጥናት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ ያቀረቡት የባሕርዳር ዩኒቨርስቲ የስነ-ምድር መረጃና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ማናጀር ዶክተር አስናቀ መኩሪያ እንደገለጹት ስራው አመርቂ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ ይውላል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ኢመደኤ በመደበው 3 ሚሊዮን ብር እየተሰራ የሚገኝ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አስናቀ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ በተመረጡ 388 ተቋማት ላይ የፕሮጀክቱ ጥናት ያነጣጠረባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመዝጋት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ያሉት አቅራቢው ኢመደኤ በጅኦስፓሻል መስክ በትስስር ለመስራት ባደረገው ጥረት በአገራችን ተበታትነው የሚኖሩ ባለሙያዎችን ያሰባሰበ ፎረም በመመስረት የምርምር ተግባራትን ለማከናወን የረጅምና የአጭር ጊዜ አቅጣጫዎች ተቀምጠው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በኢመደኤ የጂኦስፓሻል ትስስር ቡድን መሪ አቶ በሪሁ አለማየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት የፎረሙ ዓላማ የሳይበር ልማትን ከሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በትስስር ለመስራትና በመስኩ የሚታየውን ከፍተት ለመዝጋት ነው ብለዋል፡፡  ከዚህ በተጨማሪም የፎረሙ መቋቋም የሳይበር ታለንት ልማትን ለማሳደግ፣ የምርምርና የአዳዲስ ግኝቶች ስራ ከነበሩበት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ብሎም ችግር ፈች ጉዳዮች ላይ በትኩረት ለመስራት ነው ብለዋል፡፡ ትስስሩ አገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ያስረዱት አቶ በሪሁ በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈልቁ ሀሳቦችን ወስዶ አዳዲስ ጉዳዮችን መፍጠርና ወደ ተግባር በመቀየር አገራችን የተያያዘችውን የልማት ጉዞ ለመደገፍ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡  በውይይቱ ላይ ልዩ ልዩ የተጀማመሩ ፐሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃና የፎረሙ ቀጣይ የአስተዳደር መመሪያዎችን ጨምሮ በርካታ ርዕሰ-ጉዳዮች በአጀንዳነት የተያዙ መሆኑን በፎረሙ ላይ ተገልጿል፡፡

የጂኦስፓሻል ኢንዳስትሪ ፎረሙ በ2008 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ኢመደኤን ጨምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ባሕርዳር የኒቨርሲቲ፣ ጅማ የኒቨርሲቲ፣ መቐለ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም እንጦጦ የምርምር ተቋም በአባልነት አካቷል፡፡