ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል

10ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም "ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል" በሚል መሪ ቃል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ተከበረ፡፡ በዓሉ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች በተገኙበት በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከብሯል፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከዚህ በፊት የሰንደቅ አላማችንን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሲባል የተለያዩ ጦርነቶች እንደተካሄዱ ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የሃገራችን ነፃነት የሚገለፅበት ትልቁ መሳሪያ እውቀት ነው ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው እንደገለፁት የሃገራችን ነፃነት የሚረጋገጠው ድህነትን አሸንፈን ወደ ብልፅግና ጎራ ስንቀላቀል ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ በዋናነት እውቀት ሲኖረንና እውቀታችንን ተጠቅመን ሃብት ማፍራት ስንችል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኢመደኤ እንደተቋም እውቀት በመፍጠርና በማቀጣጠል ሂደት ላይ የላቀ ድርሻ ያለው ተቋም ሲሆን ሁሉም የኤጀንሲው አባላትም ተልዕኳችንን በላቀ ደረጃ በመወጣት የሰንደቅ አላማችንን ክብር በስራ ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡