ብሔራዊ የሳይበር ታለንት ልማት ፕሮግራም

ብሔራዊ የሳይበር ታለንት ልማት ፕሮግራም

ሳይበር በሦስት ነገሮች ማለትም በሰው ልጅ ንቃተ-ሕሊና ዕድገት፣ በቴክኖሎጅ ዕድገት እና በማሕበረሰባዊ መስተጋብር የተፈጠረ ክስተት ሲሆን፤ የመሰረተ-ልማት፣ የኢንፎርሜሽን፣ ኢንፎርሜሽኑን እና መሰረተ-ልማቱን የሚያስተዳድሩ ስርአቶች፣ ኢንፎርሜሽኑን ወደ እውቀት የሚቀይርና የሚጠቀም የሠው ኃይል እንዲሁም የህብረተሰብ ባህል መስተጋብር ውጤት እንደሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻለቃ ቢኒያም ተወልደ እና በኢመደኤ የሳይበር ሰራዊት ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሻለቃ ሰላምይሁን አደፍርስ ከሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ሳይበር እና የሳይበር ኃይል ምንነት እንዲሁም በብሔራዊ የሳይበር ታለንት ልማት ፕሮግራም ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አመራሮቹ ከሳይበርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ …

 

ሳይበርኛ - ሳይበር ምንድን ነው?

ሻለቃ ቢኒያም- ሳይበር ከሰው ልጅ ንቃተ-ሕሊና የመነጨ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማሕበራዊ መስተጋብር እና በኃይል ዳይናሚክስ መካከል የሚታይ ክስተት ነው፡፡ ስለ ሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና በምናወራበት ጊዜ የተለያዩ ደረጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ይህም የተለያዩ ስልጣኔዎችን በማጥናት፣ የተቋማት ዕድገትን በማመዛዘንና የሰው ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሁሉ ይጨምራል፡፡ በዚህ በኩል አራት እይታዎች አሉ፤ የመጀመሪያው ልማዳዊ ዕይታ (Habitual paradigm) ሲሆን ይህም የተለያዩ ተቃርኖዎችን መገንዘብ የማንችልበት፣ ሁሉም ጉዳይ በኃይል የሚነዳበትና በከፍተኛ ደረጃ ጥገኝነት የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ሁለተኛው ዕይታ ነገሮችን ከፋፍለን ማየት የምንችልበት (Singular paradigm) ሲሆን ይህም ተቃርኖዎችን ለያይተን የምንመለከትበትና አመክንዮአዊ የሆነ አስተሳሰብ የሚታይበት እንዲሁም ቅርጽ ባለው መንገድ ስራዎችን የምናከናውንበት ዕይታ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ነጻነት የማግኘትና ከጥገኝነት የመውጣት አስተሳሰብ የሚዳብርበት ዕይታ ሲሆን የተነጠለ ፓራዳይም (Singular Paradigm) ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡ ሦስተኛው ዕይታ ትስስራዊ ዕይታ (Connective paradigm) ሲሆን ይህም በክፍፍሎች መካከል ቁርኝትና ከማሕበረሰቡ ጋር ትስስር ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ አራተኛው ሁሉን አቀፍ ዕይታ (Holistic paradigm) የምንለው ዕይታ ሲሆን ይህም ነገሮች በከፍተኛ ደረጃ እርስ በእርሳቸው የሚተሳሰሩ ጉዳዮችን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ በፊት የታጠረ (Determinate) የተደረጉ ሥርዓቶች የነበሩ ሲሆን አሁን ግን የሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና እያደገ በመምጣቱ ከቴክኖሎጂ ጋር በየጊዜው እየተቀያየሩ የሚሄዱ አዳዲስ ክስተቶችን መገንዘብ የተቻለበትን ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ መስተጋብር ተዋረዳዊ ነው፤ አለቃ፣ መንግስት፣ ህዝብና የመሳሰሉትን በውስጡ ይዟል፡፡ በአራተኛው ዕይታ ግን የጎንዮሽ የእድገት ደረጃ ነው የሚኖረው፡፡ ሰው በእውቀቱ ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ትስስር ማለትም ሶስቱ የንቃተ-ህሊና የእድገት ደረጃዎች፣ የቴክኖሎጂ ምጡቅነትና የማህበረሰብ መስተጋብር የሚያስከትሉት ክስተት ሳይበር ልንለው እንችላለን፡፡

በሌላም በኩል ሳይበር እንደ አብዮት ይታያል፡፡ በፖለቲካውም ካየነው በፊት የነበረውና የአሁኑ ይለያል፤ ስለሆነም ከዚህ ላይ ወሳኝ የኃይል ሚዛኑ እውቀት ነው፡፡ ሳይበር ትናንሽ ለሆኑ ቡድኖችም፣ ግለሰቦችም ከፍተኛ ኃይል የሚሰጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከማህበረሰብ አኳያ ስናየው በፊት በተዋረድ የነበረ ጉዳይ አሁን ግን በጎንዮሽ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመሆኑም ትስስሩን መገደብ አይቻልም፤ በአንድ ቦታ የተገደበም አይደለም፤ በኢኮኖሚ ዓለም ሲታይ ደግሞ የበፊቶቹ በአካላዊ ሃብት ነበር የሚተማመኑት አሁን ግን በዕውቀት ሆኗል፡፡ ከዚህ አንጻር ትላልቆቹ የኢንዱስትሪ ተቋማት በትንንሾቹ ሊደረመሱ ይችላሉ፡፡ ሌላው በባሕል ተገዥነትና ወረራ ላይ የሚያበረክተው ሚናም ከፍተኛ ነው፡፡ በሳይበሩ ዓለም ወታደራዊ መከላከያው ዕውቀት ያስፈልገዋል፡፡ በአጠቃላይ ባህሪውን ካየነው ሳይበር ትስስር ያለው፣ ተለዋዋጭ፣ አዳዲስ ጉዳዮችን የሚያሳይና ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው፡፡ በመሆኑም ሳይበርን ለመረዳት ትስስራዊ ዕይታ ወሳኝ ነው፡፡ ሳይበር በሦስቱ ነገሮች ማለትም በሰው ልጅ ንቃተ-ሕሊና ዕድገት፣ በቴክኖሎጅ ዕድገት እና በማሕበረሰባዊ መስተጋብር የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡

 

 

ሳይበርኛ- ስለ ሳይበር ይህን ያህል ማብራሪያ ከሰጡን ለመሆኑ የሳይበር ኃይል ምንድን ነው?

ሻለቃ ቢኒያም - ከላይ ሳይበርን በገለጽነው መሰረት የሳይበር ምህዳር መፈጠርን ተከትሎ በመጣው አብዮት መሰረት ለዚያ የሚመጥን ፖሊሲ ከሌለን አገር የሚባል አይኖርም፤ የባሕል ወረራውም መከሰቱ አይቀርም፤ የፖለቲካ ስርዓቱም አደጋ ላይ ይወድቃል፤ የህብረተሰቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴም ቢሆን ጥሩ ነገር አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ይህን የሚመጥን ዕይታ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ሳይበርን የሚመጥን ፖሊሲ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሳይበርን እንደ ኃይል ነው የምናየው፤ ሳይበር ልክ እንደ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲና ወታደራዊ ኃይል አገራዊ የኃይል መሳሪያ ነው ብለን ልንጠራውም እንችላለን፡፡ ሳይበር ማስተሳሰር የሚችል ኃይል አለው፤ በዚህ ዙሪያ የባለቤትነት ቦታን ለመያዝና ነጻ የመውጣት ዕድሉን ለማግኘት  እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንደ አገር መቀጠል አይቻም፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር የሳይበር ኢንዱስትሪ የማልማት ስትራቴጅ ተቀርጾ እየተሰራ ሲሆን፤ በሰው ኃይል ልማት ረገድም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ኮር የሚባሉ ቴክኖሎጅዎችም እየተሰሩ የሚገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌላው በከፍተኛ ደረጃ ጨዋታ በሚቀይሩና ኢንዱስትሪውን ሊያቀጣጥሉ በሚችሉ ኮር ፕላትፎርሞች በምንላቸው ላይ ለአፕሊኬሽኖች መነሻ የሚሆኑ ፕላትፎርሞች ከመገንባት አንጻርም ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ጨዋታ ቀያሪ የሆኑ ከአገራዊ ፍልስፍና ጋር የተሳሰሩ መሰረተ-ልማቶችን መገንባትም ያስፈልጋል፡፡

 

ሳይበርኛ- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሰው ኃይል ልማትን በተመለከተ ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ?

ሻለቃ ሰላምይሁን- ከሰው ኃይል ልማት አንጻር ሲታይ እስካሁን ከፍተኛ ጥናት ተደርጎበት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 401/2009 መሰረት የሳይበር ሰራዊት ልማት ኢንስቲትዩት ተቋቁሟል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሳይበር ሰራዊት ለመገንባት በትስስሩ ውስጥ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ከዚህ በፊት ከነበረው የሰው ኃይል ጋር ተመሳሳይ የሆነ አካል መፈጠሩ አስፈላጊነት አይኖረውም፡፡ ከዚህ አንጻር ስራውን ለማሳደግ ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፍ ከሆኑ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ለዚህ ፕሮግራም የሚመጥኑ ሰዎች ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በፍጥነት የሚማርና እንደበፊቱ ሳይሆን በቶሎ ሁኔታዎችን የሚረዳ የሰው ኃይል መፈጠር አለበት፡፡

ከዚህ አንጻር ኢንስቲትዩቱ ሲቋቋም ዋና ዋና ተብለው የተሰጡት ስራዎች አሉ፤ አገራዊ ፍላጎት ተብለው የተነሱም እንደዚሁ፡፡ ስለዚህ ኢንስቲትዩቱ የዚችን አገር ህልውና የሚጠብቅ ሰው የሚያፈራ ነው፤ በዚህ የሚፈጠረው ሰው ከልማዳዊ ሁኔታው ተነስቶ በፍጥነት የሚማር መሆን አለበት፡፡ እንደተባለው ሳይበር ትልቅ ኃይል እንደመሆኑ መጠን ይህን የሚያውቅ የሰው ኃይል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ሳይበር ታለንት ሲባል ሁሉም ሰው ተሰጥኦ አለው ከሚል ዕሳቤ የሚነሳና ለሳይበር የሚመጥን ሰዎች አሉ ካልን ይህን ፈልጎ ለማግኘት የተቀረፀ ፕሮግራም ነው፡፡

 

ሳይበርኛ- የሳይበር ታለንት ፕሮግራሞች የሳይበር ኃይልን ከመፍጠር አንጻር የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው?

ሻለቃ ቢኒያም- የሳይበር ታለንት የሚያስፈልገው አንደኛ ከህልውና አንጻር እና እንደ ሀገር ለመቀጠል ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ከዚያም የተፈጠረውን የእድገት እይታ በመጠቀም አገራችንን ወደ ተሻለ መንገድ መውሰድ ስላለብን ነው የሳይበር ሀይል እንደ ወሳኝ ጉዳይ የሚታየው፡፡ ከዚህ አንጻር በሚቀጥሉት 8 ዓመታት አገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሳይበር ሀይል ትገነባለች ብለን ራዕይ አስቀምጠናል፡፡ ይህ ማለት የቴክኖሎጂ እውቀት ማግኘት፣ የንቃተ-ሕሊና ለውጥ ማምጣት፤ በባህልና በሰው ኃይላችንም ከፍተኛ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት ሳይበር የሚፈልገው ስብዕና እና አስተሳሰብ ያለው የሰው ኃይል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በሳይበሩ ዓለም መተሳሰር በጣም ትልቅ ቦታ አለው፤ ከዚህ በተጨማሪም በፍጥነት የመማርና ነገሮችን የመረዳት ሁኔታ ትልቅ አንድምታ አለው፡፡  እንደተባለው አንዳንዱ ልማዳዊ ዕይታ ላይ ሲሆን ጥቂቶቹ ደግሞ በተከፋፈለ ሂደት ወይም አስተሳሰብ ላይ ስለሚገኙ ይህን ወደ ትስስር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ እንደ ሀገር ጥሩ እሴቶችም አሉን፤ በራስ አቅም የሆነ ነገር የመገንባት ጥበብም ያለን እና ነጻነታችንን ጠብቀን የቆየን  ህዝቦች መሆናችን አይዘነጋም፡፡ በመሆኑም እነዚህን እሴቶች ተጠቅመን ወደ ትስስር መዝለል አለብን፡፡  ሳይበር በጥገኝነት የሚገኝ አይደለም፤ በዕውቀት የሚሰራ ነው፤ ሆኖም ግን ጥገኝነቱ አሁንም አለቀቀንም፡፡ ከዚህ አንጻር በሰው ኃይላችን ላይ የሚያዘልል  ወይም የሚያስፈነጥር ነጥብ (Tipping point) ማምጣት አለብን ማለት ነው፡፡ ይህን ካመጣን የተቀመጠውን ራዕይ ማሳካት እንችላን፡፡ ይህን ካላሳካን ግን የአገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ታለንት ልማት በዚህ ላይ ዝላይ የሚፈጥርልን ተግባር ነው፤ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀድመን የታለንት ልማት ፕሮግራም አካሄደናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታለንት ልማትን ከፍ ለማድረግ ከውጭ አገር ልምድ ለመውሰድ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዝንባሌያቸው ከሳይበር ልማት ጋር ጥሩ የሚባሉ ሰዎችን እስከ 9 ወር በሚደርስ ጊዜ ውስጥ በውጭ አገር ለማሰልጠን ዕቅድ ተይዟል፡፡ እነዚህ አካላትም በቀጣይ ለሚያስፈልገው ተግባር ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ስልጠናው የፈጠራ አቅማቸውንና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን የሚያሳድግላቸው ይሆናል፡፡ ስልጠናው የሚሰጠው እስከ 30 ለሚደርሱ ሰዎች ሲሆን እነዚህ ሰዎች አቀጣጣይ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስልጠናው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ትምህርት ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡ ሰልጣኞችን በተመለከተ የራሳቸው እድገት እንዲኖራቸውና ትላልቅ መሪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የፈጠራ ሰዎችና መሰል ሰዎች እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡  

 

 

ሳይበርኛ- የሳይበር ታለንት ፐሮግራም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? እነማን ናቸው ተሳታፊዎቹ?

ሻለቃ ሰላምይሁን- የታለንት ፕሮግራም ምዝገባን በተመለከተ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰራጭቷል፤ ሰዎችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ፤ ህብረተሰቡም እድሉን መጠቀም አለበት፡፡ ምን አይነት ሰዎች ናቸው ለሚለው ከኮምፒውተርና ተያያዥ ሙያዎች ዙሪያ የተመረቁ፣ በኢንጅነሪንግ መስክ የሚገኙ፣ የተመረቁ ብቻም ሳይሆን በስራ ላይ ያሉም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱ የሚሰራው በጣም ልዩና ወሳኝ ለሆኑ የሰው ኃይል ነው፡፡ ለጠቅላላ ፍላጎት ግን ብዙ የሰው ሃይል ስለሚያስፈልግ ይህን ለማሟላት ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ፕሮግራም ቀርጸን እየተንቀሳቀስን ስለሆነ በዚህ የምናሟላው ይሆናል፡፡

 

ሳይበርኛ - በሳይበር ታለንት ልማት የሚሳተፉ ሰዎች ለወደፊት እጣ ፋንታቸው ምንድን ነው የሚሆነው?

ሻለቃ ሰላምይሁን- እነዚህ ሰዎች ወደ ታለንት ልማት ፕሮግራሙ ሲገቡ የተሰጠውን ትኩረት ያክል ሲወጡም ከዚያ ጋር የሚመጥን አገራዊ ትራንስፎርሜሽንን የሚያረጋግጡ፤ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴዎች ውስጥም በሂደት እየተሳተፉ የሚሄዱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ትልልቅ በሳይበሩ ዓለም የጀማሪ (Start-ups) ካምፓኒዎች የሚመሰርቱና በዚሁ አቅማቸውን የሚጠቀሙና ትልቅ የሚሆኑበት መንገድ ይኖራል፡፡ የሳይበር ኢንዳስትሪውን በማቀጣጠል ሂደትም ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ አንድ ሰው ብዙ አይነት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሆኖ የእሱ መገኘት በዚያ ቦታ ላይ  የማቀጣጠል ሂደቱም በስፋት የሚሰራ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህ ሌላ አንድ ሰው በሳይበር ውስጥ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ በደንብ ሊያሳዩ የሚችሉ ሰዎች ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ እንደ ግለሰብም የስኬት መሰረታቸው ጽኑ የሆነ ሙሉ በራስ መተማመንና ስብዕና ያላቸው ሰዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህን ለማሳካትም የምንጨነቅበት ነው የሚሆነው፤ ከዚያ በላይ ደግሞ በቴክኖሎጂው ረገድ ትልልቅ ውጤቶችን ሊያስመዘግቡ የሚችሉበት አቅም የሚገነቡ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሰዎች ከላይ የተነሱ አንኳር የስራ እንቅስቃሴዎችን አካተው የያዙ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡  

 

ሻለቃ ቢኒያም- እነዚህ ሰዎች ካዘጋጀነው የውጭ አገር የስልጠና ፕሮግራም በመጠቀም ጭምር ትላልቅ የሆኑ ደርማሳዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚያፈልቁ ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም ሳይበሩ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ አለው፤ ስለዚህ ከዚህ ለውጥ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ የሚፈጥሩና ቴክኖሎጂዎችን የሚያበለጽጉ አካላት ከእነዚህ ሰዎች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንዳንዶቻቸው ደግሞ ዕይታቸው ወደ ቢዝነስና ስራ ፈጠራ ሆኖ ትላልቅ ኩባንያዎችን የሚፈጥሩ ይሆናል፡፡ በሳይበሩ ዓለም ትላልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ኩባንያዎችንም የሚመሰርቱ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶቻቸው ደግሞ በአገር ደሕንነት ማለትም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አንጻርም ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ዋልታና መከታ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶቹም የወደፊቱ የአገር ህልውና ከሳይበር ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ትላልቅ አመራርና ፖለቲከኛ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ የሚፈጠረው አቅም በራስ መተማመናቸው፣ የፈጠራ ብቃታቸው፣ በፍጥነት የመማራቸው ወ.ዘ.ተ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚቀየር ሀሴት የተሞላበት ህይወትም ይኖራሉ፡፡ ትላልቅ ተጽዕኖዎችም የሚፈጥሩ፤ ሌሎች ሰዎችንም በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተምሩ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ከሰራን በአገር ደረጃ ሉዓላዊነት ይጠበቃል፤ ኢንዱስትሪውንም ማልማት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች እየተባዙና እየተቀጣጠሉ በሚሄዱበት ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በአጠቃላይ የሳይበር ኢንዱስትሪውን የማሳደግ፣ ኢኮኖሚውን የማበልጸግና ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ አዝማሚያ ይኖራል፡፡ እነዚህ ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃም የሳይበር እይታውን የሚቀይሩ አስተሳሰቦችን ሊያመጡ የሚችሉ፣ አለም አቀፋዊ አስተዋጽኦም የሚያደርጉ ተግባር የሚሰሩ ሰዎች ይሆናሉ፡፡

ሳይበርኛ- ስለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን

ሻለቃ ቢኒያም እና ሻለቃ ሰላምይሁን- እኛም እናመሰግናለን፡፡