በኢንፎርሜሽን ደህንነት ዙሪያ ከቁልፍ የመንግስት ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ

በቁልፍ የመንግስት ተቋማት የሚስተዋሉ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ክፍተቶችን ለማስወገድ በሚያስችሉ መፍትሄዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ተካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተካፈሉ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት የኢንፎርሜሽን ደህንነታቸው ምን እንደሚመስል የዳሰሳ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በሌላም በኩል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የተዘጋጀውን "የወሳኝ አቅም ሳይበር ደህንት ስታንዳርድ" መሰረት በማድረግ በተካሄደው ውይይት ላይ፤ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት የያዙትን ራዕይና ተልዕኮ እንዲያሳኩ የኢንፎርሜሽን ደህንነታቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

የቁልፍ የመንግስት ተቋማትን የኢንፎርሜሽን ደህንነት ለማረጋገጥና ተጋላጭነታቸውን በዘላቂነት ለመቀነስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጋራ ፎረም ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ላይ  ተደርሷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተካፈሉ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት በበኩላቸው የየተቋሞቻቸውን የኢንፎርሜሽን ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሀገራዊ የሳይበር ሃይል አካል ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢመደኤም በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት ለተቋማቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡