አገራዊ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የብሔራዊ ህልውና ጉዳይ ነው

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ ከENN ቴሌቪዥን "ፊት ለፊት ፕሮግራም" ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢመደኤ ስለተሰማራበት የሥራ ምህዳር (ሳይበር) ምንነት እና ስለ ኤጀንሲው ተግባርና ሃላፊነቶች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም አገራዊ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የብሔራዊ ህልውና ጉዳይ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለንበት የኢንፎርሜሽንና ግሎባላይዜሽን ዘመን የትኛውም አገር ራሱን ከዓለም ነጥሎ መኖርም ሆነ ማደግ እንደማይችል የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአንድ በኩል የሳይበር ምህዳር መፈጠርን ተከትሎ የሚመጡትን መልካም አጋጣሚዎች በአግባቡ ለመጠቀም፤ በሌላም በኩል ከሳይበር ምህዳር ዓለም አቀፋዊነት እና ድንበር የለሽነት ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጉዳቶችን ለመከላከል ብሔራዊ የሳይበር ኃይል መገንባት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሳይበር ምህዳር የእውቀትና የመረጃ ምህዳር ሲሆን፤ ይህንን ምህዳር በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር ሀገራዊ የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግና ባለቤትነትን ማረጋገጥ፣ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ የሳይበር ኢንዳስትሪውን ማነቃቃት እንዲሁም በዋናነት በመረጃና እውቀት የሚያምንና የሚመራ ማህበረሰብ መገንባት ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ለምን ቁልፍ ብሔራዊ አጀንዳ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ ብሔራዊ የሳይበር ኃይል በመገንባት ሂደት ላይ የኢመደኤ ድርሻና ሃላፊነት ምን እንደሆነ ወ.ዘ.ተ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከENN ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ …

 

ENN ቴሌቪዥን

ከዚህ ቀደም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን "የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ" ብለን እንጠራ ነበር፤ ለመሆኑ በኤጀንሲው ዕይታ ኢንፎርሜሽን እና መረጃ የተጽእኖ እና ትርጉም ልዩነት አላቸው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ኢንፎርሜሽን እና መረጃ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ሁለቱ የሚገናኙበት ወይም የሚያያዙበት ነገር ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም፡፡ ኢንፎርሜሽን ሲባል በማንኛውም መልክ (በጽሁፍ፣ በፊደል፣ በድምጽ፣ በቪዲዮ፣ በምስል ወ.ዘ.ተ) የሚቀመጥ፣ የሚተነተን እና ለትንተና የሚጠቅም ግብአት ማለት ነው፡፡ ይሄ ኢንፎርሜሽን ዋጋ የሚኖረው ግን ከተፈጠረበት ቦታ ወደ ሚጠቀምበት አካል በአግባቡ ሲተላለፍ፣ ሲተነተን እና ለውሳኔ ግብአት ሆኖ ሲያገለግል ነው፡፡ በሌላ በኩል መረብ የሚባለው ኢንፎርሜሽን የሚተላለፍበት ወይም የሚሰራጭበት ማለት ነው፤ መረቡ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊሆን ይችላል፣ በአገር ደረጃ ወይም ደግሞ በተቋም ደረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢንፎርሜሽን የሚባለው በመረቡ የሚተላለፍ ወይም የሚሰራጭ እና ለቀጣይ ግብአት ወይም ለታሪክ የሚቀመጥ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢንፎርሜሽን ከላይ የተገለጹት ነገሮች ሁሉ መስተጋብ ውጤት ነው፡፡

ኢንፎርሜሽን ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣ ደግሞ ደህንነቱ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ኢንፎርሜሽን ደህንነቱ ተጠብቋል ሲባል፤ የኢንፎርሜሽኑ ሚስጥራዊነት፣ ምልዑነት እና ተደራሽነት (Confidentiality, Integrity and Availability- CIA) ተረጋግጧል ማለት ነው፡፡  ሚስጥራዊነት ሲባል ኢንፎርሜሽኑ ለተላለፈለት/ለተላከለት አካል ብቻ የማድረስ ሂደት ሲሆን፤ ምልዑነት ማለት ደግሞ የተላለፈው ኢንፎርሜሽን በማንኛውም መልኩ እንዳይቀየር፣ እንዳይደለዝ፣ እንዳይጠፋ ማድረግ ማለት ነው፤ ተደራሽነት ኢንፎርሜሽኑን ለሚመለከተው አካል የማድረስ ሂደት ሲሆን ይህም ኢንፎርሜሽኑ በትክክል እንዳይደርስ የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን የማስወገድና ለሚፈለገው አካል የማድረስ ነው፡፡

መረጃ ሲባል ግን ሌላ ትርጉም አለው፤ መረጃ ስለ ጠላት ወይም ስለ ንግድ ተወዳዳሪ አካል ግብአት መሰብሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- ስለ ቢዝነስ ተወዳዳሪ አካል ምን አይነት ስትራቴጂ፣ ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ ምን አይነት እቅድ፣ ፍላጎት ወ.ዘ.ተ እንዳለው ማጣራት መረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢንፎርሜሽን እና መረጃ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ ይህ ሲባል የሚገናኙበት ወይም የሚያያዙበት ነገር ሊኖርም ይችላል፡፡ መሰረታዊ በሆነ አመለካከት  ግን መረጃ ወይም ዳታን ብንወስድ (ለምሳሌ ስለ አንድ ግለሰብ ቁመት፣ መልክ፣ ክብደት) የሚገልጹ ዳታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እነዚህ ዳታዎች ለብቻቸው በወረቀት ላይ ተዘርዝረው ቢቀመጡ ትርጉም አይኖራቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ኢንፎርሜሽን መቀየር/መሸጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ከላይ የተሰበሰቡት ዳታዎች ትርጉም በሚሰጥ መልኩ የእከሌ/የእከሊት ማንነት (Profile) ተብለው ሲቀመጡ ትርጉም ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ትርጉም የሚሰጥ መረጃ ኢንፎርሜሽን ሲሆን፤ በቀጣይነት እውቀት ይሆናል፣ ወደ ሌላ አካል ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

ኢመደኤ በዋናነት የተሰማራበት ምህዳር የሳይበር ምህዳር እንደሆነ ይታወቃል፤ ለመሆኑ ሳይበር እና የሳይበር ምህዳር ምን ማለት ነው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በመጀመሪያ ደረጃ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ኢኮቴ)፤ ኢንተርኔት፤ ሳይበር የሚባሉ አጠራሮች አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ሳይበር ከተባለ ኢኮቴ፣  ኮምፒውተር እና  ሶፍትዌር ወይም ደግሞ ኢንተርኔት እንደሆነ ነው ግንዛቤ የሚያዘው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ መካከል ልዩነትም አንድነትም አለ፡፡ ልዩነቶቹን ስናይ፤ ለምሳሌ ኢኮቴ ሲባል በአብዛኛው በሃርድዌር እና ሶፍትዌር የሚገለጽ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሲባል በሃርድዌር ደረጃ ኮምፒውተር ወይም ሞባይል ሊሆን ይችላል፤  እንዲሁም እሱን የሚመራ ልክ እንደ ጭንቅላታችን የሚያስብና ፕሮሰስ የሚያደርግ ሶፍትዌር አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህን እና ከዚህ ጋር የተያያዙ ቴክኖሎጂዎችን  ነው በቀላሉ ኢኮቴ ብለን የምንጠራቸው፡፡ ወደ ኢንተርኔት ስንመጣ ዓለም አቀፍ የመስተጋብር ጀርባ አጥንት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ መስተጋብር ሲባል ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፤ ግንኙነት ይፈጠራል፣ ይዘት (content) ይኖራል፣ ምላሽ (Interaction) ይኖረዋል፣ ይዘቱ ፕሮሰስ የሚደረግበትና የሚቀመጥበት የራሱ ስርአት አለው፡፡ ስለዚህ ከቴክኖሎጂ አንጻር ዓለም አቀፋዊነት (Globalization) የሚባለው መሰረት የሚያደርገው በዋናት በሁለት ነገሮች ላይ ነው፤ አንደኛው ኢንተርኔት ሲሆን ሁለተኛው ትራንስፖርት ነው፡፡ ትራንስፖርት ሲባል የአየር፣ የባቡር ወ.ዘ.ተ ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ በመሆኑም ኢንተርኔት ለሁሉም ነገር የጀርባ አጥንት ነው ማለት ይቻላል፤ ለኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካ፣ ለውጭ ግንኙነት ወ.ዘ.ተ መሰረት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢንተርኔት ዓለም አቀፋዊ ትስስርን ነው የሚገልጸው፡፡

ሳይበር ሲባል ግን ከኢኮቴም ሆነ ከኢንተርኔት ላቀ ያለ ትርጉም አለው፡፡ ሳይበር መሰረተ-ልማት አለው፤ መሰረተ-ልማት ሲባል ኢንተርኔት ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ከኢንተርኔት ውጪ ያሉ ከባቢያዊ (Private) ኔትዎርኮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ የባንኮች፣ የመከላከያ፣ የውጭ ጉዳይ ወ.ዘ.ተ ኔትዎርኮች ከኢንተርኔት ውጪ ያሉ ከባቢያዊ ኔትዎርኮች ናቸው፡፡ ከዚያ አልፎ ደግሞ የኢንዳስትሪያል ቁጥጥር ስርአቶችም አሉ፤ ፋብሪካ የሚያንቀሳቅስ ቴክኖሎጂም ሊሆን ይችላል፤ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማትም ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ መሰረተ-ልማት ስንል በሳይበር ውስጥ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል ህጎች፣ ስታንዳርዶች፣ ፖሊሲዎች ወ.ዘ.ተ አሉ፡፡ ከዚህም አልፎ የተለያየ አይነት ኢንፎርሜሽን አለ፡፡ የሰው መስተጋብ አለ፡፡ ባህል አለ (ሳይበሩ ወደ ህብረተሰቡ ይደርሳል ህብረተሰቡ ሳይበሩን ይጠቀማል)፡፡ ስለዚህ በአጭሩ ሳይበር የመሰረተ-ልማት፣ የኢንፎርሜሽን፣ ኢንፎርሜሽኑን እና መሰረተ-ልማቱን የሚያስተዳድሩ ስርአቶች፣ ኢንፎርሜሽኑን ወደ እውቀት የሚቀይርና የሚጠቀም የሠው ኃይል እንዲሁም የህብረተሰብ ባህል መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ ይህ መስተጋብር ግን ከኢንተርኔት በላይ የሆነ ነው፤ ኢንተርኔት ዓለም አቀፋዊ ሲሆን ሳይበር ውስጥ ያለው መስተጋብር ግን በአንድ ሀገር ውስጥ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

የሳይበር ምህዳር ዓለም አቀፋዊ ገጽታው በምን መልኩ ነው የሚገለጸው? ለመሆኑ የሳይበር ምህዳር ተፈጥሯል ስንል ምን ማለታችን ነው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በመሰረታዊነት ምህዳር ስንል ክልል ማለታችን ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ ሀገራት የራሳቸው የሆነ የአየር ወይም ስፔስ ክልል፣ የባህር ክልል፣ የመሬት ክልል አላቸው፡፡ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትም የሚገለጸው በእነዚህ ክልሎች ላይ ያላቸውን ጥቅምና ፍላጎት በማስከበርና ባለማስከበር ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን ሉዓላዊነት የምንለው ህዝብ ነው፤ ሉዓላዊ የሆነ ህዝብ (በራሱ የመረጠው የሚተዳደርበት ህግ፣ አስተዳዳሪ ያለው ህዝብ) ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቀድሞ የነበሩ ክልሎች አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይቀጥላሉ፡፡ አሁን ላይ ግን የሳይበር ክልል ወይም ምህዳር የሚባል ነገር ተፈጥሯል፡፡ ሳይበር ክልል የሚባለው ከላይ የተገለጹት ክልሎች (አየር፣ መሬት እና ባህር) መስተጋብር እና አስቻይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል መሬት ላይ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የባቡር ወ.ዘ.ተ መሰረተ-ልማቶች ይዘረጋሉ፡፡ እነዚህ መሰረተ-ልማቶች በመሰረታዊነት ሳይበር ላይ ነው የሚመሰረቱት፤ ማለትም እነዚህን መሰረተ-ልማቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ መቆጣጠር፣ ማስተዳደር፣ መጠቀም ወ.ዘ.ተ የሚቻለው በሳይበር አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ሳይበር ስንል እውቀትን መሰረት ያደረገ ሃይል ማለታችን ነው፡፡ በመሆኑም ሳይበር እያልን ያለነው በአንድ በኩል ለአየር፣ ለውሃ እና ለመሬት ክልሎች አስቻይ ሲሆን፤ በሌላ በኩልም ሳይበር በራሱ ሃይል ነው፡፡ በሳይበር ምህዳር ውስጥ ጊዜ፣ ቦታ ርቀት የሚባሉ ጉዳዮች ምንም አይነት ተጽእኖ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ግለሰብ ከየትኛውም የአለም ክፍል ጋር የባህል፣ የንግድ፣ የትምህርት ወ.ዘ.ተ ግንኙነት መፍጠር ይችላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ናቸው የሳይበር ምህዳርን ዓለም አቀፋዊ ወይም ዓለምን ወደ አንድ መንደር ያመጣ የሚያሰኙት፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

የሳይበር ምህዳር ዓለም አቀፋዊነትን ተከትሎ ሳይበር የሉዓላዊነት ስጋት ተደርጎ ይታያል፤ ይሄንን እንዴት ያዩታል?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በሳይበር ምህዳር ውስጥ ሉዓላዊነት ቀድሞ በሚታወቅበት ትርጓሜ ሊታይ አይችልም፡፡ በቀድሞ ጊዜ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚገለጸው በመሰረታዊነት አራት መመዘኛዎችን ሲያሟላ እንደሆነ የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም አንደኛው እ.ኤ.አ 1948 የተፈረመው የዌስትፋሊያ ስምምነት ሲሆን ይህም የአውሮፓ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ደረጃ መሰረት የጣለ እና የሀገራት ጂኦግራፊያዊ ድንበር አይደፈሬነትና ከማንኛውም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት ነጻነት መከበር ነው፤ ሁለተኛው ከሌሎች ሀገሮች ጋር በሚኖረው ትስስር እና ግንኙነት በእኩል ደረጃ የመወዳደር እና ድምጽን የማሰማት ሉዓላዊ ስልጣን እንዲሁም በማንኛውም የውጭ ሃይል ያለመደፈር መብት ነው፤ በሦስተኛ ደረጃ ሀገራት ባላቸው የግዛት ዳር ድንበር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትንም ሆነ ግዑዝ አካላትን የሚገዛ ህግ የማውጣት፣ የመተግበር፣ ጣልቃ የመግባት እና የመምራት የውስጥ ሉዓላዊነት ሲሆን፤ በአራተኛ ደረጃ ሀገራት ዳር ድንበራቸውን ከማንኛውም የውጭ ወራሪ ሃይል የማስጠበቅ፣ ይህንን ለማድረግም ሃይል የመጠቀም፣ ወታደራዊ ሃይል የማንቀሳቀስ እንዲሁም ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመመከት ዓለም አቀፋዊ ሉዓላዊነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሳይበር ምህዳር መፈጠርን ተከትሎ ቀድሞ በነበሩ የሉዓላዊነት መመዘኛዎች ላይ ሙሉ በሙሉ የተቀየረ ነገር ባይኖርም የተወሰኑ ጉዳዮች ሊቀየሩ ችለዋል፡፡ በሳይበር ምህዳር ውስጥ ድንበር ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፤ ይህ አንዱ የተቀየረ ጉዳይ ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

በሳይበር ዓለም ውስጥ የሀገራት ሉዓላዊነት ከየትኛውም ቦታ፤ በማንኛውም ሀገር፣ ቡድን ወይም ግለሰብ ሊጣስ ይችላል፤ ይህ ሲባል በሳይበር መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው ወይስ ሌላ መገለጫ አለው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በመሰረተ-ልማት ደረጃ ስናየው ሀገራችን የራሷ የሆኑ ሳይበርን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ወይም የተዘረጉ መሰረተ-ልማቶች፤ የመብራት፣ የውሃ፣ የባቡር፣ የቴሌ፣ የባንክ ወ.ዘ.ተ አሏት፡፡ ስለዚህ መሰረተ-ልማትን ብቻ ነጥለን ስናየው የራሳችን የምንለው ግዛት አለን፤ ምንም እንኳን ይህ መሰረተ-ልማት ገና በጅምር ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም፡፡ እነዚህ ሳይበርን መሰረት አድርገው የተዘረጉ ስርአቶች ስራዎቻችንን የምናቀላጥፍባቸው፣ ከዓለም ጋር የምንገናኝባቸው ናቸው፤ እነዚህን ስርአቶች ግን ከየትኛውም የአለም ጫፍ ማጥቃት ይቻላል፡፡ ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ከሌላ ሀገራት የሚሰነዘርን ጥቃት ድንበርን በማጠር (በመሬት፣ በአየር፣ በውሃ ላይ ያለውን ድንበር በማጠር) መከላከል ይቻል ነበር፤ በሳይበር ዓለም ውስጥ ግን ይህ የቀድሞ አካሄድ ፈርሷል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ያለው የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌ፣ የግለሰቦች ኢ-ሜይል አካውንት ወ.ዘ.ተ ከየትኛውም የአለም ጫፍ ሊጠቃ ይችላል፤ ሀገራት የራሳቸውን የመከላከል አቅም እስካላሳደጉ ድረስ በሳይበር ዓለም ውስጥ ሁሉም ነገር ክፍት ነው፡፡ በመሆኑም ቀድሞ የነበረው የሉዓላዊነት ትርጓሜ በሳይበር ዓለም ውስጥ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው፡፡ ሉዓላዊነት ሲባል በዋናነት የሚነሳው የህዝቦች መብት ነው፤ ህዝቦች የተለያዩ አገልግሎቶችን፤ የመብራት፣ የውሃ፣ ኢንፎርሜሽን፣ የባንክ አገልግሎት ወ.ዘ.ተ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች ግን ሳይበር ውስጥ በመግባታው በማንኛውም ጊዜ ከየትኛውም የዓለም ጫፍ በሚሰነዘር ጥቃት ሊቋረጡ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በሳይበር ዓለም ውስጥ ቀድሞ የነበረው የሉዓላዊነት ትርጓሜ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡

 

 

ENN ቴሌቪዥን

ሳይበር ወደሚባለው ዓለም ወይም ምህዳር ውስጥ የግድ መግባት አለብን? አለመግባት አይቻልም?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

አሁን ባለንበት ዓለም ውስጥ ወደ ሳይበር አለመግባት አይቻልም፤ እንደ አማራጭም ሊወሰድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሳይበር ዋና ዓላማው እድገት ነው፤ ሳይበር ማለት በራሱ እውቀት እና የእውቀት ልውውጥ ነው፤ ከእውቀት ውጪ ደግሞ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፡፡ አንድ ሀገር ለብቻው አጥር አጥሮ መኖር የሚችልበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ የለም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፤ አንደኛው የሳይበር ምንነትን በደንብ አውቆ ሙሉ በሙሉ እራስን ወደ ሳይበር አስገብቶ እንደሌሎቹ በሳይበር ተጠቃሚ የሆኑ የዓለማችን ክፍሎች ማደግ ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ስለ ሳይበር ምንነት ሳታውቅ ወደ ሳይበር ዓለም መቀላቀል ነው፡፡  ስለሆነም የተሻለ አማራጭ የሚሆነው የመጀመሪያው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለ ሳይበር ምንነት በደንብ አውቆ ራስን አዘጋጅቶ መግባት ሲቻል የመከላከልና የመቆጣጠር አቅምም ይኖራል፤ ይህ ካልሆነ ግን ሁለተኛው አማራጭ የግድ ይሆናል፤ ምክንያቱም ከዓለም ተነጥሎ መኖር አይቻልም፡፡ በሁለተኛው አማራጭ ስለ ሳይበር ምንነት በደንብ ሳታውቅና ሳትዘጋጅ መግባት የሌሎች መጠቀሚያና ባሪያ እንደሚያደርግህ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ፌስቡክን ብናይ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ አለመረጋጋት መሳሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፤ የውሸት ዜናዎች በየሰከንዱ እየተፈበረኩ ዜጎች ከዜጎች ጋር፤ ብሔር ከብሔር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት ወ.ዘ.ተ ጋር የሚጋጩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሳይበር ዓለም ሳያውቁና ሳይዘጋጁ መግባት የወንጀል፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የትርምስ ማዕከል እንዲሁም የሌሎች መጠቀሚያ እና ባሪያ መሆን ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

የሳይበር ጥቃትን የተመለከተ ጉዳይ የበለጸጉት ሀገራት ጉዳይ አድርጎ የማየት ሁኔታ አለ፤ በእርግጥ የሳይበር ጉዳይ የበለጸጉት ሀገራት ጉዳይ ብቻ ነው? ታዳጊ ሀገራትስ የሳይበር ዓለም መጠቀሚያ እና ባሪያ ላለመሆን መዘጋጀት አይገባቸውም?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ሀገራት በሳይበር ላይ ያላቸው ሉዓላዊነት የሚለካው በሳይበር ላይ ባላቸው ቦታ ነው፤ ማለትም ሳይበርን (የሳይበር ቴክኖሎጂ፣ መሰረተ-ልማት ወ.ዘ.ተ) በመፍጠርና በመጠቀም ደረጃ ያላቸው ቦታ ምን ያህል ነው የሚለው ነው የሚወስነው፡፡ ከዚህ አንጻር  ሳይበርን በመፍጠርም ሆነ  በመቆጣጠር  አሜሪካ በቀዳሚነት የምትቀመጥ ሀገር ናት፡፡ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች፤ አውሮፓ እና ቻይና በተወሰነ መልኩ በሳይበር ዓለም ውስጥ ያላቸውን ቦታ በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አፍሪካን ስንመለከት በሳይበር ውስጥ ያላት ቦታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢንተርኔትን እንኳን ብንወስድ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ የተፈጠረው አሜሪካ ሲሆን የሚቆጣጠረውም አይካን (The Internet Corporation for Assigned Names and Numbers-ICCAN) የተሰኘው የአሜሪካ ካምፓኒ ነው፡፡ ሌሎች ካምፓኒዎች ከዚህ ድርጅት ውክልና በመውሰድ ለሌሎች ሀገራት፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ዶሜይን ስም ይሸጣሉ (በሌላ አነጋገር ከፍተኛ የሆነ ቢዝነስ በሳይበር ዓለም ውስጥ ያከናውናሉ)፡፡ ኢትዮጵያም እንደ አንድ ሉዓላዊት ሀገር ዶት ኢቲ (.et) የተሰኘ ዶሜይን ስም ወይም ግዛት አላት፤ ከዚህ በተጨማሪ ዶት ኢድዩ (.edu) የተባለ ዶሜይን ስም አላት፡፡ በሌላ በኩል ኬንያን እንኳን ብንወስድ ከ100 በላይ ዶምይን ስም አላት፤ ይህ ሀገራት በሳይበር ዓለም ያላቸውን ቦታ የሚያሳይ አንድ ማነጻጸሪያ ነው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ሳይበር በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እንዲሁም በማህበራዊው መስክ ትልቅ አቅምና ተጽእኖ ፈጣሪ እየሆነ ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ ብንወስድ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሳይበርን መሰረት አድርጎ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ ይህንን በቀላል ምሳሌ ለመግለጽ፡- ቀደም ባለው ጊዜ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚገናኙት በኤምባሲ በኩል ነበር፤ አሁን ይህ ሁኔታ ተሻሽሎ እያንዳንዱ ዜጋ (ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጀንዳ በመቅረጽና መልእክት በማስተላፍ) የሀገሩ አምባሳደር በመሆን የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰራበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡  ከኢኮኖሚ አንጻር የሳይበር ኢንዳስትሪ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ የሚገኝ ነው፤ ኢንዳስትሪው በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር መዋዕለ-ንዋይ የሚያንቀሳቅሰው ነው፤ ዓለም አቀፍ ገበያዎች ሳይበር ላይ ነው የተመሰረቱት፤ ስለዚህ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትም ሆኗል፡፡ በማህበራዊ መስክም ከፍተኛ የሆነ የባህል መስተጋብር በሳይበር ውስጥ ይፈጠራል፤ ሀገሮች ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብሩበት አውድ ሳይበር ነው፡፡ በአጠቃላይ የሳይበር ዓለም ውስጥ ያልገባ ሀገር የለም ማለት ይቻላል፤ ልዩነቱ ያለው ሀገራት በሳይበር ምህዳር ላይ ያላቸው የመፍጠር፣ የመጠቀምና የመቆጣጠር አቅም ደረጃ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በዋናነት መወሰድ ያለበት ትልቅ ጉዳይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች በፍጥነት ለማደግ ሳይበር (የሳይበር አቅምን ማሳደግ) አቋራጭ ወይም ማስፈንጠሪያ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ነው፡፡ ይህ ሲባል እውቀትን መሰረት ያደረገ ማህበረሰብ የመገንባት ጥያቄ ነው፤ በእውቀት የሚያምን፣ የሚመራ ማህበረሰብ መፍጠር በፍጥነት ለማደግ ትልቅ መስፈንጠሪያ አቅም ነው፡፡ በመሆኑም ሳይበር የበለጸጉት ሀገራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ በዋናነትም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች የህልውና እና በፍጥነት ለማደግ አቅም የሚፈጥር አቅም ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

የሳይበር አስተዳደር ጉዳይ በምን ደረጃ ላይ ያለ ነው? አስተዳደሩን በሚመለከት ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ ወይ?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በሳይበር ዓለም ውስጥ ቁልፍ ሃብት (Critical Resource) የሚባሉት ቁጥርና ስም (Alfa-numeric) ናቸው፡፡ ስለ ሳይበር በምናወራበትም ጊዜ በዋናነት የምናወራው ስለ ኤይ ፒ አድሬስ (Internet Protocol-IP) ነው፡፡ አይ ፒ ማለት ከላይ እንደተገለጸው ቁጥር እና ስም ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፤ ለምሳሌ የአንድ ግለሰብ ኢ-ሜይል አድራሻ (somebody@gmail.com) ሲባል ለዛ ግለሰብ የሚሰጠው ፊደል እና ቁጥር (Alfa-numeric) ነው፤ ይህንን ግን ኮምፒውተር ሊረዳው አይችልም፤ ስለዚህ ይሄንን ተጠቅሞ አንድ ግለሰብ ሌላ ሀገር ላይ ለሚገኝ ወዳጁ መልእክት ሲልክ መልእክቱ እንዴት ብሎ ነው ለተቀባዩ የሚደርሰው የሚለው ነው ቁልፉ ጥያቄ፡፡ የፕሮቶኮሎች እና ስታንዳርዶች ጉዳይም የሚነሳው እዚህ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ከአንደኛው ግለሰብ ወደ ሌላኛው ግለሰብ የተላከውን መልእክት የሚቀይሩ በርካታ ስታንዳርዶች አሉ፤ ፕሮቶኮል ማለትም ይሄ ነው፡፡ ከሰው ወደ ማሽን፣ ከማሽን ወደ ማሽን ከዚያም ከማሽን ወደ ሰው የሚቀይሩ የግንኙነት ፕሮቶኮሎች ወይም ፎርማቶች አሉ፡፡ አይካን ብለን ቅድመ ያነሳነው የአሜሪካ ካምፓኒም እነዚህን ዶሜይን ስሞች (Domain Names) ነው የሚሰጠው፡፡ ለምሳሌ ዶት ኢቲ (.et) ሲባል ቀላል ነገር ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ይህን ዶሜይን ስም ለመስጠት በርካታ መሰረተ-ልማቶች ይዘረጋሉ፤ በርካታ ዳታ ማእከላት ይቋቋማሉ ወ.ዘ.ተ፤ እነዚህ በሙሉ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በርካታ ዶሜይን ስሞች (.gov, .edu, .com, ወ.ዘ.ተ) የሚባሉት የሚፈጠሩበት ዋና ወይም መሰረት የሆነ ቦታ አለ፤ ማለትም ዳታ ሴንተሮች፣ ሰርቨሮች፣ ሪፖዚተሪዎች ወ.ዘ.ተ የሚቀመጡበት፣ ፕሮሰስ የሚደረጉበት በአጠቃላይ የሳይበር ምህዳር ዋናው ምንጩና ስርአቱ የሚተዳደርበትን የሚቆጣጠሩት ማዕከላት ዋና ዋናዎቹ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው የሳይበሩ ዓለም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር እንዳለ ነው፡፡ ከአሜሪካ በመቀጠል አውሮፓውያን የተወሰነ ድርሻ አላቸው፡፡ አዚህ ላይ ነው የሳይበር አስተዳደር ጉዳይ የሚነሳው፤ የሳይበር አስተዳደር ፍትሃዊ አይደለም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ ፈጠራ አንጻር አሜሪካ አብዛኛውን ቴክኖሎጂ ስለፈጠረች እውቅናውንም መብቱንም መውሰድ እንዳለባት ግልጽ ነው፡፡ ምህዳሩን በማስተዳደር በኩል ግን ሌሎች ሀገራት (አውሮፓውያን፣ ቻይና ወ.ዘ.ተ) የይገባናል ጥያቄ በማንሳት ላይ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ምህዳሩን ለማስተዳደርም በርካታ አማራጮች፤ የብዝሃ አካላት አስተዳደር መንገድ፣ በአንድ ተቋም ስር እንዲተዳደር የማድረግ መንገድ ወ.ዘ.ተ አማራጮች በተለያየ ጊዜ ይቀርባሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ የሳይበር አስተዳደር ጉዳይ እልባት ያላገኘ የክርክር ነጥብ ሆኖ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሜሪካ የሳይበር ዓለምን በብቸኝነት በመቆጣጠር እንደምትጠቀምበት ግልጽ እየሆነ (በተለይም ስኖውደን የተባለው ግለሰብ ይህንን የተመለከተ በርካታ ሚስጥሮችን ካወጣ በኋላ) ሌሎች የዓለም ክፍሎች፤ አውሮፓ፣ ቻይና ወ.ዘ.ተ የራሳችን የኢንተርኔት የጀርባ አጥንት ይኑረን የሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የየራሱን ግዛት መፍጠር በቂ አይደለም፤ ከአለም ጋር መገናኘት አለባቸው፤ ስለዚህ ስርአት ያስፈልጋቸዋል፤ በመሆኑም ወደ ኢንተርኔት መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ከዚህ በመለስ ግን ሀገራት የየራሳቸውን የሳይበር አቅም በመገንባት ረገድ የሚከለክላቸው ነገር የለም፤ የቴክኖሎጂ አቅም እስካላቸው ድረስ፡፡  በሌላ በኩል ሁሉም ሀገራት የየራሳቸውን የሳይበር ክልል የመፍጠር እንቅስቃሴ በአንድ በኩል በአደጋ መልኩ የሚታይ ነው፤ ይህም ማለት የሳይበር ዓለም በአሜሪካ ቁጥጥር ስር በመሆኑ ምክንያት  የተፈጠረውን አለመተማመን ተከትሎ ሀገራት ወደ ተናጠል አካሄድ መሄዳቸው ዓለም አቀፋዊነት (Globalization) የሚባለውን ጉዳይ አደጋ ውስጥ የሚከተው ጉዳይ ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

በሀገራችን ያለውን የመረጃ አጠቃቀም በተመለከተ በተለይም ደግሞ በጂኦስፓሻል መረጃና ቴክኖሎጂ በኩል ኤጀንሲው እየሰራ ያለው ስራ ምን ይመስላል?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ኢመደኤ በዋናነት የሚሰራው የኢንፎርሜሽን እና መረብ ደህንነት ላይ ነው፡፡ ኢንፎርሜሽን ሲባል በተለያየ አይነት መልኩ የሚሰበሰብ (በሠው ወይም በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚሰበሰብ ኢንፎርሜሽን) ሲሆን፤ ኢንፎርሜሽኑ ከተሰበሰበ በኋላ መተንተን ይኖርበታል፤ አብዛኛውን ጊዜ ለትንተና ኮምፒውተር እና ሶፍትዌሮች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከዚያም ኢንፎርሜሽኑ መከማቸት ይኖርበታል፤ ኢንፎርሜሽን ለማከማቸት የተለያዩ ሰርቨሮች፣ የመረጃ ቋቶች ወ.ዘ.ተያስፈልጋሉ፡፡ በመጨረሻም ኢንፎርሜሽኑ ይሰራጫል፤ ለማሰራጨትም የኮሙዩኒኬሽን ስርአት ያስፈልጋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ተጋላጭነት የምንለውም በእነዚህ ሂደቶች ላይ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ የኢንፎርሜሽን ደህንነትን ማረጋገጥ ሲባል ኢንፎርሜሽኑ በሚሰበሰብበት፣ በሚተነተንበት፣ በሚከማችበት እንዲሁም በሚሰራጭበት ወቅት ያሉ ተጋላጭነቶችን መከላከልና መፍታት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጂኦስፓሻል መረጃን እንኳን ብንመለከት ከዚህ በፊት ሀገራዊ አቅም ባለመኖሩ ምክንያት የሀገራችንን የጂኦስፓሻል መረጃ የሚሰበስቡት የውጭ ሀገር ካምፓኒዎች ነበሩ፤ እነዚህ ካምፓኒዎች ስለ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ መረጃ አላቸው፡፡ እነዚህ መረጃዎች ደግሞ ለተለያዩ ዓላማዎች፤ ለፖለቲካ አጀንዳ፣ ለወታደራዊ አገልግሎት ወ.ዘተ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚፈልግ አካል ይህንን መረጃ ሊጠቀም ይችላል፤ ምክንያቱም እነዚህ መረጃዎች የሚሸጡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ጂኦስፓሻል ስንል ጥሬ ትርጉሙ፤ ጂኦ ማለት ጂኦግራፊ ሲሆን፤ ስፓሻል ማለት ደግሞ ገጽታ (ከገጽታ በታች ያሉትንም መረጃዎች ጨምሮ) ማለት ነው፡፡ የጂኦስፓሻል መረጃ ደህንነት ሲባልም ከገጽታ በላይና በታች ያሉትን መረጃዎች የመሰብሰብ፣ የመተንተን፣ የማከማቸትና የማሰራጨት ብቃት ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የጂኦስፓሻል መረጃ ለሁለንተናዊ ልማት አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል፤ የግብርና ስራ ለማከናወን፣ የኤርፖርት መሰረተ-ልማት ለመዘርጋት፣ መንገድ ለመስራት፣ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ወ.ዘ.ተ የጂኦስፓሻል መረጃና ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የኢንፎርሜሽን ደህንነትን ማረጋገጥ የሚቻለው የቴክኖሎጂ ብቃት መገንባትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢመደኤ በዋናነት እየሰራው ያለው ስራ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ቴክኖሎጂ እና እውቀት እንዲኖራት ማድረግ ላይ ነው፡፡ በጂኦስፓሻል ዘርፍ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ የራሳችን የሆነ አውሮፕላን ወይም ድሮን፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው የካሜራ ሲስተም፣ ሶፍትዌር ፕሮሰሲንግ እና የፕሮሰሲንግ አቅም እንዲሁም ወደ ዲጂታል ማፕ የመቀየር ከዚያ ደግሞ የተለያዩ አይነት ማፖችን የማበልጸግ እና ማፑን ለመጠቀም የሚያስችሉ ስርአቶች ማበልጸግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ስራዎች ሙሉ በሙሉ በኢመደኤ ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ኢመደኤ በኮር ቴክኖሎጂው ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቅም ባልተፈጠረባቸውና ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች በመግባት ክፍተቶችን ይሸፍናል፡፡ ከዚህ አንጻር ኢመደኤ የመቆጣጠር ስራውን በስፋት የሚሰራበት ሲሆን፤ በቀጣይ ሀገራዊ አቅም መገንባት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የግል ዘርፉ በሳይበር ኢንዳስትሪው ላይ ለመሰማራት ያለው ቁርጠኝነት አነስተኛ በመሆኑ መንግስት ጣልቃ በመግባት አቅም የመፍጠር ስራውን እየሰራ ይገኛል፤ በአሁኑ ወቅት መረጃዎችን ከመሰብሰብ ጀምሮ እስከ ማሰራጨት ድረስ ያሉ ሂደቶች (ከተወሰኑና በጣም የተለዩ ቴክኖሎጂዎች በስተቀር፤ ለምሳሌ የባቡር ሃዲድ ለመስራት ፍፁም ትክክለኛነትን የሚጠይቅ ሊዳር የሚባል ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ እሱም ቢሆን በቅርቡ ይኖረናል የሚል እምነት አለ) ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሀገር አቅም እየተሰራበት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የተሟላ አቅም እየፈጠርን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፤ በሂደት ደግሞ የግል ካምፓኒዎች እዚህ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢመደኤም ቢሆን በዘላቂነት እዚህ ላይ የመቆየት ፍላጎት የለውም፤ ለግል ካምፓኒዎች እየለቀቀ የሚሄድበት ስትራቴጂ ነው ያለው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

ከመሬት ልማትና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሲሰሩ ከነበሩ ስራዎች ውስጥ የአዲስ አበባ ካዳስተር ሲስተም ስርአት አንዱ ነበር፡፡ የከተማዋ ካዳስተር ስርአት ይሰራል የሚል ከሰባት አመት በፊት እቅድ ቢወጣም እስካሁን ድረስ ይፋ የሆነ ውጤት የለም፤ በሌላ በኩል የከተማዋ 10ኛ ማስተር ፕላን በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አገር አቀፍ የካዳስተር ልማት ስራዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? እነዚህ ስራዎች ላይ የኢመደኤ ድርሻ ምንድን ነው?  

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ካዳስተር ማለት በመሰረቱ የንብረት ባለቤትነት መብት ፈጠራ ማለት ነው፤ ከህጋዊ ካዳስተር አንጻር፡፡ ሌሎች የካዳስተር አይነቶችም፤ የግብር፣ የመሰረተ-ልማት ወ.ዘ.ተ አሉ፡፡ ስለዚህ ህጋዊ ካዳስተር ሲባል እያንዳንዱ ዜጋ ያለውን ቁራሽ መሬት (Parcel) ባለቤት ስለመሆኑ የማረጋገጥ፤ የመመዝገብ እና የማስተዳደር ስርአት ነው፡፡ ይህ ስርአት ከተፈጠረ በኋላ እያንዳንዱ ግለሰብ መሬቱ ላይ ያፈሰሰውን ሃብት ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ለሌላ ለማስተላለፍ ወ.ዘ.ተ ቀላል ይሆናል ማለት ነው፤ በጥቅሉ ቢዝነስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የካዳስተር ስርአት ዋና ዓላማም መሬትን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና እንቅስቃሴዎችንና መረቦችን ለማፍረስና ለመቆጣጠር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሬትን ፍትሃዊና ተደራሽ በሆነ መልኩ ለማስተዳደር የካዳስተር ስርአት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ በአዲስ አበባ ካዳስተር ስርአት ልማት ላይ የኢመደኤ ሚና የነበረው የአዲስ አበባን ኤሪያል ፎቶ ግራፍ የማንሳትና ፕሮሰስ የማድረግ ነበር፡፡ በመሰረቱ ይህንን ስራ እንዲሰራ የተሰጠው "ሃንሳ" የተባለ የጀርመን ካምፓኒ ነው፡፡ ኢመደኤ ይህንን ተቋም የመከታተል እና የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ ሚና ነበረው፡፡ አጠቃላይ ስራው ሦስት አመት የፈጀ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ኢመደኤ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ስራውን ሙሉ በሙሉ መስራት የሚችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ችሏል፤ ማለትም ሶፍትዌሮችን ማበልጸግ፣ ስፓሻል ዳታ ፕሮሰስ ማድረግ፣ ዲጂታል ማፕ መስራት ወ.ዘ.ተ፡፡ በቀጣይ የሆነውም የውጭ ካምፓኒው የሰራውን ስራ ሲስተሙን የማሻሻልና የመጠገን ስራ ኢመደኤ ኮንትራት ወስዶ እየሰራበት ያለበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል፡፡ ከቴክኖሎጂ ሽግግር አንጻር ይሄ እንደ አንድ ግብአት የሚወሰድ ነው፡፡ በሌላም በኩል በካዳስተር ስርአት ውስጥ የህግ ማእቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የተለያዩ ህጎች፣ ስታንዳርዶች፣ ፕሮሲጀሮች ወጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን የካዳስተር ስርአት በጣም ውስብስብ ስራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ውስብስብ የሆነበትም ምክንያት ስራው ቴክኖሎጂ ስላለ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ መሬት እንዴት እንደሚመዘገብ፣ እንዴት እንደሚረጋገጥ፣ እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ወ.ዘ.ተ መሰረት የሚጥሉ ህጎች፣ ፕሮሲጀሮችናና ፕሮሰሶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብቃት ያለው የሰው ሃይልም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢመደኤ ይህንን በመፍጠር ሂደት ላይ ይገመኛል፡፡ የካዳስተር ልማት ስራ ትራንስፎርሜሽን የሚጠይቅ ስራ ነው፤ በርካታ ተግዳሮቶችም አሉት፡፡ ከተግዳሮቶቹ መካከልም ይህንን ስራ የማይፈልጉ አካላት አዚህም እዚያም መኖራቸው፣ ከዘርፉ ኪራይ ለመስበሰብ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው፣ የማስተዳደር፣ የመምራት፣ የሰለጠነ የባለሙያ እጥረት ወ.ዘ.ተ መኖሩ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህንን ከመፍታት አንጻር ኢመደኤ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል፤ ለምሳሌ ከቴክኖሎጂ አንጻር (ቴክኖሎጂውን የማበልጸግ፣ የማቅረብ፣ የማስተዳደር ወ.ዘ.ተ አቅም) በተሻለ ደረጃ እንገኛለን፡፡ በአጠቃላይ ግን የካዳስተር ልማት ስርአት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በመገንዘብ በዘላቂነት የሚፈቱበትን አቅጣጫ ቀይሰን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡  

 

ENN ቴሌቪዥን

በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በምንመከትበት ጊዜ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ማህበረሰብ በገጠር የሚኖርበትና አብዛኞቹ የመንግስት አገልግሎቶችም አናሎግ በሆኑበት ሁኔታ ስለ ሳይበር ያለው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በአንድ በኩል የሳይበር መሰረተ-ልማትን የመጠቀም ተግዳሮት ይታያል፤ በሌላም በኩል በሳይበር ምህዳር ውስጥ ጥሩ ተዋናይ የመሆን ተግዳሮት ይታያል፤ ሁለቱ ችግሮች አብረው አይታዩም?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በመጀመሪያ ደረጃ ሳይበር ምንድን ነው የሚለውን በምንመለከትበት ጊዜ በአሁኑ ወቅት ከማናቸውም የኢኮኖሚ ሃብቶች (ከነዳጅ፣ ማእድናት ወ.ዘ.ተ) በላይ አቅምና ሃይል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የመልካም አስተዳደር ችግር ብለን ስናነሳ በዋናነት የኢንፎርሜሽን ግልጽነት አለመኖር ነው፡፡ አንድ ሰው ኢንፎርሜሽን ከሌለው በጨለማ ውስጥ እንደተቀመጠ ነው፤ ይህ ደግሞ የትኛውም አካል እንደፈለገው ሊያሽከረክረው ይችላል፡፡ መንግስት በጣም ብዙ ኢንፎርሜሽን አለው፤ ምክንያቱም ብዙ ሃብትን ይቆጣጠራል፤ ለምሳሌ መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው ሲባል በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው ማለት ነው፤ ከዛ ውጪ ግን በርካታ ሃብቶችን ያስተዳድራል፡፡ ይህ ሃብት ግን በመንግስት ቁጥጥር ስር ይሁን እንጂ የህዝብ ሃብት ነው፤ ስለዚህ የህዝብ ሃብት እስከሆነ ድረስ ፍትሃዊና ተደራሽ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ግልጽነት ያስፈልጋል፡፡ ግልጽ ለመሆን ደግሞ የኢንፎርሜሽን ልውውጥ ያስፈልጋል፤ መንግስትና ህዝብ በኢንፎርሜሽን መቀራረብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ መንግስትና ህዝብ በጣም በተራራቁ ቁጥር የኢንፎርሜሽን ክፍተት ይፈጠራል፤ ከዚህም በላይ ህዝቡ ስለ መንግስት አሰራር ለማወቅ በጣም ከባድ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ኢንፎርሜሽን ከመልካም አስተዳደር፣ ከኢኮኖሚ ወ.ዘ.ተ አኳያ ትልቅ ሃይል ነው፡፡ ይህ ሲባል ከኢንፎርሜሽን ውጪ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ግልጽ ነው፤ ለምሳሌ ያህል የግብርና ስራ ለመስራት እንኳን ስለ መሬቱ አይነት፣ ምን አይነት ማዳበሪያ መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ መቼ መዝራት፣ መሰብሰብ እንዳለበት ወ.ዘ.ተ መረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በተለምዷዊ መንገድ በመስራት ማደግ አይቻልም የግድ ኢንፎርሜሽን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከድህነት ለመውጣት ዋናው መሳሪያ እውቀት ነው፤  በኢንፎርሜሽን ላይ የተመሰረተ እውቀት፡፡ ይሄ ኢንፎርሜሽን ደግሞ በትክክል እንደ ትልቅ ሃብት ተቆጥሮ ለህዝብ ወይም ደግሞ ለሚመለከተው አካል ብቻ ተደራሽ በሆነ መልኩ ልናስተዳድረው፣ ልንፈጥረው፣ ልናሰራጨው፣ ልንለዋወጠው እና ልናከማቸው ይገባል፡፡ የሳይበር ዋና ጥቅምም ጎልቶ የሚታየው እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ህጻናትም ከልጅነት ጀምረው ሳይበርን የመጠቀም ባህላቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም ሳይበር እውቀት ለማግኘት፣ ለማስተላለፍ፣ ለመለዋወጥ ወ.ዘ.ተ የሚጠቅም ሃይል ስለሆነ፡፡ ትልቁ መፍትሄ የሚሆነውም አስተሳሰባችንን የመቀየር ጉዳይ ነው፤ ዋናው ሃብት መሬት ወይም ገንዘብ ሳይሆን እውቀት ወይም ሰው መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ለእውቀትና ለኢንፎርሜሽን የምንሰጠው ዋጋ ማደግ አለበት፡፡  

 

ENN ቴሌቪዥን

አሁንም ቢሆን በሀገራችን እየተሰሩ ያሉ በርካታ ስራዎች፤ የአይ.ሲ.ቲ መሰረተ ልማቶችም ይሁኑ የሳይበር መሰረተ-ልማቶች በውጭ ካምፓኒዎች እየተሰሩ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገር ውስጥ አቅም ውስንነት እንዳለ ሆኖ በሀገር ደረጃ የሳይበር ምንነትና አስፈላጊነት ዙሪያ የጠራ ግንዛቤው አለ? ከሌለ ምክንያቱ የኢመደኤ አቅም በደንብ አለመስፋቱ ነው ወይስ አገራዊ አቅም ስላልተገነባ ነው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በሳይበር ዓለም ውስጥ ተጋላጭነት ስንል በጣም በርካታ አይነት ነው፡፡ በተለይም ታዳጊ አገሮች በብዙ መንገድ ባደጉት አገሮች ላይ ጥገኞች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሀገራችንን ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ  የራሳችን የምንለው ሳተላይት የለንም፤ ስለዚህ መከራየት አለብን፤ ኪራዩ ደግሞ ባስፈለገ ጊዜ ሊቋረጥ ይችላል የኢንፎርሜሽንና ኢንተርኔት አገልግሎቶችም ችግር ውስጥ ይገባሉ ነው፡፡ በሌላም በኩል ስናየው የሳይበር መሰረተ-ልማት ለመዘርጋት የሚያስፈልጉ ፋይበሮችን (Fibers & Cables) ሙሉ በሙሉ ከውጭ ነው የምንገዛው ይሄም ለጂኦ-ፖለቲካል አደጋዎች የተጋለጠ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሳይበር ቴክኖሎጂ ልማት ካምፓኒዎች በሀገራችን ገና አላደጉም፡፡ ይህን ሁሉ አጠቃለን ስናየው የሳይበር ኢኮኖሚ ያለው ቀድመው ባደጉ አገሮች እና ፈጥነው እንደ አገር ነቅተው የሳይበር ጉዳይን በስትራቴጂና ፖሊሲ ደረጃ ቀርጸው በተንቀሳቀሱ አገሮች (ለምሳሌ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን ወ.ዘ.ተ) ላይ ነው፡፡ እነዚህ አገራት የሳይበር ኢኮኖሚውን መቆጣጠር የቻሉት የሳይበር ጉዳይን አገራዊ አጀንዳ አድርገው በመወሰን እና ህግና ፖሊሲ ቀርጸው መዋዕለ ንዋይ (Investment) ስላፈሰሱና ስለሰሩ ነው፡፡ የሳይበር አንዱ ባህሪው ደግሞ እንደ ሌሎች ሴክተሮች ከባድ የሆነ መዋዕለ-ንዋይ የሚጠይቅ ሳይሆን ዋናው መሰረቱ ሠውን ማልማትና እውቀት ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን የሳይበር ኢንዳስትሪው እንዲነቃቃ በዋናነት የሚያስፈልገው የሳይበር ኢንዳስትሪን የሚያነቃቁ ፖሊሲዎችን መተግበር ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ስርአቱን ማስተካከልም ሌላው እርምጃ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በፖሊሲ ደረጃ ስናየው በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የወጣ  የአይ.ሲ.ቲ ስትራቴጂ አለ፤ ነገር ግን የሳይበር ጉዳይ በዚህ ስትራቴጂ ብቻ የሚመለስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዋናነት መንግስት የሳይበር ጉዳይን በስትራቴጂ ደረጃ ተመልክቶ ሊያለማው ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪ ነው፤ ነገር ግን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪውም በከፍተኛ ደረጃ እንዲለማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ሳይበር አስቻይ የሆነ ሚናን ይጫወታል፡፡ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪም በተጨማሪ የሀገራችንን ግብርና ለማዘመንም ሳይበር ከፍተኛ የሆነ የአስቻይነት ሚናን ይጫወታል፡፡ በአጠቃላይ የሳይበር ቴክኖሎጂ ለሁሉም ሴክተሮች አስቻይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር ያለንበት ደረጃ ፍጹም ጥገኞች ነን ማለት ይቻላል፤ የተወሰኑ ማቃለል የጀመርናቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው፡፡ ስለዚህ ጥገኞች ነን ማለት ደግሞ በቅኝ ግዛት ውስጥ ነን ማለት ነው፤ በሳይበር ዓለም ድንበር የሚባለው ቴክኖሎጂውን የመፍጠርና የመጠቀም አቅም ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሁሉንም ነገር በራስ ብቻ መስራት አለብን ሳይሆን የራስን ነገር መሰረት አድርጎ ከሌሎች ጋር እሴት በሚፈጥር መልኩ መደመርና ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

የኢመደኤ መቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ብሔራዊ ጥቅምን እና የዜጎችን መብት ለማረጋገጥ ኢንፎርሜሽን እና ኮምፒውተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች ደህንነት ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል፤ በእርግጥ ይህ ፍላጎት (በሀገር፣ በተቋም እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ) አለ ማለት ይቻላል? ከግንዛቤው ባሻገር ፍላጎቱስ በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

እንደ ሀገር ፍላጎቱ አለ፡፡ ፍላጎቱ በመኖሩ ምክንያት መንግስት ኢመደኤን ሊያቋቁም ችሏል፡፡ መንግስት ኢመደኤን ያቋቋመበት ዋና ምክንያትም በሀገቱ ውስጥ ሳይበርን መሰረት አድርገው እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ መሰረተ-ልማቶችና ፕሮጀክቶች በመኖራቸው እና ወደ ማይቀረው የሳይበር ዓለም እየተሸጋገርን እንደሆነ በማወቅ ደህንነቱን ማስጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ በመገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ በሀገር ደረጃ ስለ ሳይበር ግንዛቤውና ፍላጎቱ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ መንግስት ዘርፉን ለማልማት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን፤ የትምህርት ስርአቱን በማስፋት በርካታ የተማረ የሰው ሃይል በመፍጠር፤ መሰረተ-ልማቶች በመዘርጋት ወ.ዘ.ተ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ሆኖም እነዚህ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆነው የሳይበር ጉዳይ እንደ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ ተይዞ ራሱን ችሎ በስትራቴጂና ፖሊሲ ደረጃ መመለስና መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ከድህነት ፈጥኖ ለመውጣት ሳይበር ትልቅ የማስፈንጠሪያ አቅም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሳይበር ጉዳይን እንደ አጀንዳ በማየት ረገድ የተወሰኑ መሻሻሎች ያሉ ቢሆንም ሁሉም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስትራቴጂክ ግንዛቤ ተፈጥሯል ማለት አይቻልም፡፡ ይህንን ለማድረግ ከባድ ስራ ይጠይቃል፤ ከዚህ በፊት የነበሩንን ባህላዊ አስተሳሰቦች መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከዚህ በፊት ሃብት የምንለውም የሚጨበጥ (መሬት ወይም መሬት ላይ ያለ ቤትና ንብረት ነው)፤ እውቀትን እንደ ሃብት አድርጎ ማሰብ ገና እየተፈጠረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ሳይበርን የማልማት ስራ ሂደት ነው፤ የባህል ለውጥም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጠኝነት ግን መንግስትም የሳይበርን ጉዳይ እንደ ትልቅ አጀንዳ ይወስደዋል፤ በሀገር ደረጃም አቅም እንፈጥራለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

በሀገራችን ሳይበርን መሰረት አድርገው የተዘረጉ መሰረተ-ልማቶች (የባንክ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባቡር ወ.ዘ.ተ) ደህንነታቸው ምን ያህል የተጠበቀ ነው? እዚህ ላይ የኢመደኤ ሚና እንዴት ይገለጻል?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ደህንነት ስንል በዋናነት ንቃተ-ህሊና እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ደህንነት ማለት ስትራቴጂክ እይታ ነው፤ ፖሊሲ፣ ስታንዳርድ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ አደረጃጀት፣ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅም፣ የማስተዳደር ወ.ዘ.ተ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ደህንነት በጣም ተለዋዋጭና በየደቂቃው የሚቀያየር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢመደኤ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ነድፎ ሁሉንም የመንግስትና የግል ተቋማት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡፤ በተለይም ደግሞ የፋይናንስ ሴክተሩን ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ፋይናንስ ሴክተር በሚል ፕሮግራም ቀርጾ ፋይናንስ ሴክተሩን የማዘመንና ደህንነቱን የማረጋገጥ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በመነቃቃት ደረጃም ከሌሎች ሴክተሮች ይልቅ ፋይናንስ ሴክተሩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ አለ፤ ምክንያቱም ሴክተሩ እያደገና ከፍተኛ ውድድር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ይህንን እድገት ተከትሎ የፋይናንስ ሴክተሩ የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታን የስትራቴጂ አካል አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል መሰረተ-ልማቶችን  በመዘርጋት ረገድ ስራዎችን እየሰራን ቢሆንም በርካታ የሚቀሩን ጉዳዮች አሉ፡፡ በየቦታው የተጀማመሩ ፕሮጀክቶች አሉ፤ እነሱን ለማቀናጀትም የተጀመሩ ስራዎች አሉ፤ በይበልጥ ትኩረት እየተሰጠው ያለው ግን መሰረተ-ልማቱን መዘርጋት ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ በተጨባጭ ሁኔታ አሁን የተሻለ የደህንነት አስተሳሰብና አካሄድ ያለው ፋይናንስ ሴክተሩ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በሀገር ደረጃ የሚከሰቱ የሳይበር ጥቃቶችን በመከታተል ረገድ ኢትዮ-ሰርት የሚባል ማእከል አደራጅተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ በኢመደኤ መቋቋሚያ አዋጅ ላይም አገራዊ የኮምፒውተር ድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጫ ማእከልን ማደራጀትና በበላይነት መምራት የሚል ሃላፊነት ለኤጀንሲው ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን በአመት ከ300 በላይ ዋና ዋና የሚባሉ የሳይበር ጥቃቶች የሚደርሱ ሲሆን፤ እነዚህን ጥቃቶች ማክሸፍ እና ጥቃቱ ለተሰነዘረበት አካል በማሳወቅ እንዲያስተካሉ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡  በአጠቃላይ  የተቀናጀ የመከላከል ስትራቴጂ እና ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር ሙከራ እየተደረገ ሲሆን፤ ዋናው ግን ሁሉም አካል የሳይበርን ጉዳይ የስትራቴጂው አካል አድርጎ እንዲመለከተው የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡  

 

ENN ቴሌቪዥን

በሠው ኃይል አቅም ረገድ ኢመደኤ ምን ያህል ተደራጅቷል ማለት ይቻላል? በተለይም ደግሞ በአገር ደረጃ መነሻ ሊሆን የሚችል የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ኢጀንሲው እያደረገው ያለው ሙከራ ምን ይመስላል?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

ኢመደኤ በመጀመሪያ ደረጃ የጥናትና ምርምር ተቋም ነው፡፡ ጥናትና ምርምር ስንል የህግ ማዕቀፍ ዝግጅትም ይጨምራል፤ የስታንዳር፣ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ ጥናቶችንም ያካትታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምርም አለ፡፡ ህጋዊ ማዕቀፍ በመፍጠር ረገድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የኮምፒውተር ወንጀል ህግ፣ ብሔራዊ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲ፣ የወሳኝ አቅም ሳይበር ደህንነት ስታንዳርድ ወጥተዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ንግድ (e-commerce) ለማካሄድ መሰረት የሚሆን የዲጂታል ፊርማ ህግ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቧል፤ ሌሎች በርካታ የህግ ማእቀፎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በሌላም በኩል ቁልፍ የሚባሉ የደህንነት አቅሞችን በመፍጠር ረገድ የተሻ ስራ ለመስራት ተችሏል፡፡ ቁልፍ የደህንነት አቅሞች የምንላቸው በዋናነት ቁልፍ የህዝብ ሃብቶች  (Public Key Infrastructure- PKI) የሚባለው ሲሆን ይህንን በራሳችን አቅም መስራት አለብን የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ሌላው ቁልፍ የደህንነት አቅም የምንለው ቴክኖሎጂ ኦፕሬቲንግ ሲስተምሲሆን፤ ይህም በዋናነት የሳይበር ጭንቅላት የምንለው ኦፕሬቲንግ ሲስተም ነው፡፡ ይህንን ከማልማት አንጻር  በራሳችን አቅም መሰረተ-ልማት እና ኔትዎርክ ላይ የሚሰራ ኦፕሬቲንግ ሲስተም አልምተን ጥቅም ላይ ማዋል ጀምረናል፡፡ ሌላው ደግሞ ገና እየተስፋፋ ያለው ዳጉ የሚባል የራሳችን የኢ-ሜይል ሲስተም አለ፤ ይህ  የኢ-ሜይል ሲስተም በአሁኑ ወቅት በኢመደኤ ደረጃ እየተጠቀምንበት እንገኛለን፤ አንዳንድ ተቋማትም መጠቀም ጀምረዋል፡፡ እነዚህን እና መሰል የሆኑ በርካታ ነገሮች አሉ፤ ከጂኦስፓሻልም አንጻርም በርካታ አቅሞች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ትላልቅ ፕሮጀክቶች፤ ለምሳሌ ያህል ሀገር አቀፍ የቴሌቪዥን ዲጂታላይዜሽን ስራ መሰረተ-ልማቱን የመዘርጋት ስራ በኢመደኤ በኩል እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ባሻገርም የራሳችን ሆስት ሳተላይትም (ETHIOSAT የተሰኘ) ለማግኘት ችለናል፡፡ በሌላም በኩል የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ለማምጠቅም ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት፡፡ በአጠቃላይ ኢመደኤ በርካታ ኢኒሼቲቮችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በሰው ሃይል ልማት ረገድ ተቋሙ እስካሁን ድረስ በርካታ ሰራተኞችን አሰልጥኗል፤ ብዙዎቹም ከተቋሙ ወጥተው የራሳቸውን ካምፓኒ እስከ መክፈት ደርሰዋል፤ ወደ ውጭ ሀገር ሄደውም እንደ ማይክሮሶፍት የመሳሰሉ ካምፓኒዎች የሚቀጠሩ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ተቋሙ ለሠው ኃይል ልማት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት አለው፡፡ ተቋሙ ውስጥ ብዙ ልምድና እውቀት ለመቅሰም የሚያስችሉ በርካታ እድሎችና ትላቅ ፕሮጀክቶች አሉ፤ በመሆኑም ሠራተኞች የተወሰነ ልምድና እውቀት ካካበቱ በኋላ የራሳቸውን ካምፓኒ የሚመሰርቱበት ሁኔታ አለ፤ ይህን ደግሞ ተቋሙ የሚደግፈውና የሚያበረታታው ጉዳይ ነው፡፡ በሌላም በኩል ተቋሙ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ቀጣይ ለሚፈጠረው የሳይበር ኢንዳሰትሪዎች እርሾ ነው የሚሆኑት፤ እንደ እርሾ የሚሆን ሃይልም (Critical Mass) እየፈጠርን ነው የምንገኘው፡፡  

የሳይበር ኢንዳስትሪ በሀገራችን የደረሰበትን ደረጃ በቀላል ምሳሌ ለማነጻጸር፤ እስራሌል ከ400 በላይ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን ብቻ የሚያመርቱ ካምፓኒዎች አሏት፤ ከዚህም በአመት ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ታገኛለች፤ የሀገራችን አጠቃላይ ኤክስፖርት በአመት ከ3.5 ቢሊዮን ብር አይዘልም፤ ይሄ ምሳሌ የሳይበር ኢንዳስትሪው ምን ያህል ኢኮኖሚ እንደሆነ ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ በሀገራችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማሩ የተወሰኑ ካምፓኒዎች አሉ፤ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ግን የለም ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይህንን መነሻ በማድረግ የሳይበር ኢንዳስትሪውን ለማነቃቃት የሚያስችል ትስስር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ሀገር በቀል ከሆኑ ካምፓኒዎች ወ.ዘ.ተ ጋር ፈጥረን እየሰራን እንገኛለን፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

ኢመደኤ ይህን ያህል ሀገራዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ ስራዎችን እየሰራበት ባለበት ሁኔታ አንዳንድ አካላት ተቋሙን ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በሌሎች ስራዎች ተጠምዶ የሚውል ነው የሚል አሉባልታዎችን ያሰማሉ፤ እንደነዚህ ያሉ አመለካከቶች ከምን የመነጩ ናቸው?

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

በመጀመሪያ ደረጃ ደህንነት የሚለው እይታ በሀገራችን ማህበረሰብ ዘንድ ያለው ትርጓሜ የተዛባ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ጊዜያት ከደህንነት ጋር የተያያዘ መጥፎ ታሪክ አለው፤ በደህንነት ስም ብዙ ሰው ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ስለሆነም ደህንነት የሚል ስም ኢትዮጵያ ውስጥ በጥሩ አይን አይታይም፡፡ ባለፉት 25 አመታት ደህንነት የሚባለው ነገር ሀገሪቱ የተረጋጋችና ሰላም እንድትሆን እያደረገ ያለ ስራ ነው፤ የደህንነት ተቋማት የሚባሉትም ስራቸው ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ ባለፉት 25 አመታት በደህንነት ላይ የነበረው አመለካከት ተቀይሯል ማለት ይቻላል ነገር ግን ጠባሳው እስካሁን ድረስም አለ፡፡ ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሲባል ደህንነት የምትለው ቃል ውስጧ ስላለች ብቻ እንደነዚህ አይነት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲፈጠሩ በር ሊከፍት ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ሳይበርን የማይጨበጥና ምናባዊ አድርጎ የመሳል ሁኔታ አለ፤ ነገር ግን ሳይበር የሚጨበጥ ነው፤ በእርግጥ ምናባዊ አካልም አለው፤ ስለዚህ ይሄም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ይሄንን ቀድሞ በደህንነት ላይ ያለ ጠባሳና ህመም ተጠቅመው የጥፋት ስራ የሚሰሩ ሃይሎች አሉ፤ ስለዚህ እነዚህ ሃይሎች ሆን ብለው የውሸት ወሬዎችን እየፈጠሩ የተቋሙን ስም ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ በሌላም በኩል ሆን ተብሎ በተቋሙ ስምና ዝና ላይ የሚካሄድ ዘመቻም አለ፤ ዘመቻውን የሚያካሂዱት የሀገራችንን ልማት የማይፈልጉ ሃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ነን የሚሉትም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ የእነዚህ ሃይሎች ዋና እሳቤ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ስርአት መሰረቱና ምርኩዙ የደህንነት ሃይሉ ነው የሚል ነው፤ ይሄ ግን በመሰረቱ የተሳሳተ እሳቤ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ስርአት ዋና መሰረቱ ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ሁሉ ተጠቃለው ነው በተቋሙ ላይ የሚነሱ የተዛቡ አመለካከቶች እዚህም እዚያም ሊንጸባረቁ የሚችሉት፡፡ ተቋሙ በመሰረቱ የዜጎችን ስልክም ሆነ ኢ-ሜይል ሲጠልፍ የሚውልበት ምንም አይነት ምክንያት የለውም፤ ህጉም አይፈቅድለትም፤ ይህንንም በማድረግ የሚያተርፈው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ድንበር ዘለል የሆኑ መረጃዎችን ይሰበስባል፤ ይህም ለሳይበር ኢንተሊጀንሲ ግብአት የሚሆን ነው፡፡ በሳይበር ዓለም ውስጥ ዋናው የመከላከል አቅም ኢንፎርሜሽን ነው፡፡

 

ENN ቴሌቪዥን

ስለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ!

ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ

እኔም አመሰግናለሁ!