ግዙፍ የዓለማችን ድርጅቶች ፔቲያ በተሰኘ ራንሳምዌር ቫይረስ እየተጠቁ መሆኑን ተነገረ፡፡

ቫይረሱ ባለፈው ወር ተከስቶ ከነበረው ዋና ክራይ ራንሳም ዌር ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ መሆኑም ተነግሯል፡፡ፔቲያ ቫይረስ ከተከሰተበት ሰኔ 20  2009 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ዓለም በስፋት በመሰራጨት የበርካታ አገራት ድርጅቶችን ማጥቃቱን ቢቢሲ እና ሌሎች የዓለም መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዘግበዋል፡፡

መቀመጫቸውን በአውሮፓና በአሜሪካ ያደረጉ ትላልቅ አለም አቀፍ የንግድ ተቋማት በአሁኑ የኮምፒውተር ቫይረስ ጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡

ከእነዚህም መካከል ‹‹ሮስኔፍት›› የተባለ ግዙፉ የሩሲያ ነዳጅና ጋዝ አምራች፣ ‹‹ሜርስክ›› የተባለ የዴንማርክ ኩባንያ፣ ‹‹መርክ›› የተባለ የአሜሪካ መድሀኒት አምራችና ሌሎች በርካታ ድርጅቶች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል፡፡  

በቫይረስ ጥቃቱ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባት ዮክሬን በሀገሪቱ የሚገኙ ባንኮች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ባቡር ጣቢያዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አደጋ ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

አዲሱ ፔቲያ ቫይረስ በዋናነት የማይታወቁ ኢሜሎች ሲከፈቱ የሚሰራጭ ቫይረስ ነው፡፡

ቫይረሱ አንዴ ኮምፒተሮቻችንን ካጠቃ በኃላ በተመሳሳይ ኔትወርክ ላይ በተዘረጉ ኮምፒተሮች ላይ በፍጥነት ይሰራጫል፡፡

ከዚህ በፊት የሚሰራጩ ቫይረሶች መረጃዎችን ብቻ ለይተው ያጠቁ የነበረ ሲሆን የፔቲያ ቫይረስ ግን ኮምፒተሩን ሙሉ በሙሉ በማጥቃት ሃርድ ዲስኩን እንዳይሰራ የሚያደርግ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በዚህ ጊዜም ቫይረሱ ኮምፒተሩን እንደገና ሪስታርት በማድረግ መረጃዎችን ይመሰጥራል፡፡ በመቀጠልም ኮምፒውተሩ ውስጥ ያሉ መረጃዎችን በድጋሜ ለመጠቀም 300 የአሜሪካን ዶላር በቢቲኮን ኦንላይን የክፍያ ስርዓት እንዲከፈል የሚያስገድድ መልዕክትን በፅሁፍ ያስተላልፋል፡፡

የዘርፉ ተመራማሪዎችም ጥቃቱን ያደረሰውን የሶፍት ዌር ምንጭ ለማወቅ እየሰሩ ሲሆን እስካሁን ባለው ጊዜ ቫይረሱን ያሰራጨው አካል ማን እንደሆነ ለማወቅ እንዳልተቻለም ተገልጿል፡፡

ከማይታወቁ ግለሶበች የሚላኩ ኢሜሎችን አለመክፈት ፣ አፕልኬሽኖቻችሁን አፕዴት ማድረግ እንዲሁም አፕልኬሽኖችን ዳውንሎድ በምናደርግበት ወቅትም ከታማኝ ድረ-ገፆች ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

እየተሰራጨ ያለውን የፔቲያ ቫይረስ መከላከል ያስችላል የተባለውን ሙሉ መረጃን ለማግኘትም ethiocert.insa.gov.et/ ይጎብኙ፡፡