የኢትዮ ሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን የውል ስምምነት ተደረገ

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የተዘጋጀውን ብሔራዊ የጋራና የተቀናጀ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፍ (ኢትዮ ሳት) ተጠቃሚ ለመሆን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አ.ማ እና ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከኢመደኤ ጋር የውል ስምምነት ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም አደረጉ፡፡

ኢትዮ ሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፍ ከዚህ ቀደም ለሳተላይት ኪራይ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም በላይ የደህንነት ተጋላጭነትን በማስቀረት በኩል ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው የገለጹት የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ፤ ወደፊት ሀገራዊ የሳተላይት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ይህ ማዕቀፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮ ሳትን የመጠቀም ጉዳይ ሀገራዊ ነጻነትን የማስጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዱ ይመስል በበኩላቸው፤ በቴሌቪዠን ስርጭት ወቅት ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ የአገልግሎት መቆራረጥ ችግሮች እንዲሁም በቅርበት ድጋፍ ያለማግኘት ችግሮችን በማስቀረት በኩል ኢትዮ ሳት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ አቶ አማን ፍስሃጽዮን በበኩላቸው፤ ኢትዮ ሳት ኢትዮጵያዊ የሆነ እና ኢትዮጵያዊ በሆነ ተቋም የሚተዳደር የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፍ በመሆኑ ከደህንነት ስጋትም ሆነ ከወጪ ረገድ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የገለጹ ሲሆን፤ ይህን ፕላትፎርም በማንኛውም መልኩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡    

ኢትዮ ሳት ከሚያዚያ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የሙከራ ትግበራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡