የሃይቴክ ተጠቃሚነትና ፈጠራ ለኢትዮጵያ ህዳሴ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ተካሄደ

በአገሪቱ የሃይቴክ ኢንዱስትሪ ልማትን በማገዝ በዘርፉ ዕመርታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተጠቆመ፡፡

ይህ የተገለፀው "የሃይቴክ ተጠቃሚነትና ፈጠራ የኢትዮጵያን ህዳሴ ከማረጋገጥ አንፃር" በሚል ርዕስ በሸራተን አዲስ በተደረገ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት "የሃይቴክ ኢንዱስሪ አሁን ባለበት ደረጃ ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር እየተገነቡ ላሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች አስተዳደርና ጥበቃ እንዲሁም ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ ከዘርፉ ውስብስብ ባህሪ አንፃር የባለድርሻ አካላት ግልፅ አሰራር ውህደት ተጨማሪ ስራ የሚፈልግ ነው" ብለዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሁለት ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን የቀረበውን ጥናት መሰረት በማድረግም በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመስኩ የተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ባነሱት ሃሳብም በዘርፉ ያለው የሀገሪቱ ፍላጎት በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በውጪ ሀገር ግዥ የሚሸፈን ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በሃይቴክ ዘርፍ ጀማሪ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም የኢንዱስትሪውን ባህሪ ያገናዘበ ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በሰጡት አስተያየት ሁሌም ከውጭ በግዥ የሚገቡ የሃይቴክ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ያለው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚህም ከደህነነት ተጋላጭነት እስከ የባህል ተፅዕኖ ያለበት በመሆኑ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማበረታታት የውጭ ተፅዕኖ መቀነስ ይገባል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የሳይበር ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሃይቴክ ዘርፍ ሀገሪቱ በድርመሳዊ አካሄድ የማትጓዝ ካልሆነ በመስኩ አሁን ካለንበት የተገሪነት ደረጃ ተስፈንጥረን መውጣት አንችልም ብለዋል፡፡

ለዚህም በልዩ ተሰጥኦ (Talent) እና በእውቀት ላይ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ በዘላቂነት ከኋላ ቀርነት በመውጣት የኢትዮጵያን ህዳሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት በመሆኑ ይህንኑ ለማዳበር ቀጣይ ውይይቶች መካሄድ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡